32) ሱረቱ አል-ሰጅዳህ (የስግደት ምዕራፍ)

32) ሱረቱ አል-ሰጅዳህ (የስግደት ምዕራፍ)

📖 የክቡር ቁርዓን ትርጉም 🌹


በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በኾነው፡፡

32:1 - አ.ለ.መ (አሊፍ ላም ሚም)፡፡

32:2 - የመጽሐፉ መወረድ ጥርጥር የለበትም፡፡ ከዓለማት ጌታ ነው፡፡

32:3 - ይልቁንም «ቀጠፈው» ይላሉን? አይደለም፡፡ እርሱ ከጌታህ ዘንድ የሆነ እውነት ነው፡፡ በእርሱ ከአንተ በፊት ከአስፈራሪ (ነቢይ) ያልመጣባቸውን ሕዝቦች ልታስፈራራበት (ያወረደልህ ነው)፡፡ እነርሱ ሊምመሩ ይከጀላልና፡፡

32:4 - አላህ ያ ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸውም ያለውን ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ ከዚያም በዐርሹ ላይ (ስልጣኑ) የተደላደለ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ረዳትም አማላጅም ምንም የላችሁም፤ አትገሰጹምን?

32:5 - ነገሩን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም ከምትቆጥሩት (ዘመን) ልኩ ሺህ ዓመት በሆነ ቀን ውስጥ ወደርሱ ይወጣል (ይመለሳል)፡፡

32:6 - ይህ (ይህንን የሠራው) ሩቁንም ቅርቡንም ሁሉ ዐዋቂው አሸናፊው፣ አዛኙ (ጌታ) ነው፡፡

32:7 - ያ የፈጠረውን ነገር ሁሉ ያሳመረው የሰውንም ፍጥረት ከጭቃ የጀመረው ነው፡፡

32:8 - ከዚያም ዘሮቹን ከተንጣለለ፣ ከደካማ ውሃ ያደረገ ነው፡፡

32:9 - ከዚያም (ቅርጹን) አስተካከለው፡፡ በእርሱ ውስጥም ከመንፈሱ ነፋበት፤ (ነፍስ ዘራበት)፡፡ ለእናንተም ጆሮዎችን፣ ዓይኖችንና ልቦችንም አደረገላችሁ፡፡ በጣም ጥቂትን ብቻ ታመሰግናላችሁ፡፡

32:10 - «በምድርም ውስጥ (በስብሰን) በጠፋን ጊዜ እኛ በአዲስ መፈጠር ውስጥ እንሆናለን?» አሉ፡፡ በእውነቱ እነርሱ በጌታቸው መገናኘት ከሓዲዎች ናቸው፡፡

32:11 - «በእናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችኋል፡፡ ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ» በላቸው፡፡

32:12 - አመጸኞችም በጌታቸው ዘንድ ራሶቻቸውን ያቀረቀሩ ሆነው «ጌታችን ሆይ! አየን፣ ሰማንም፡፡ መልካምን እንሠራለንና (ወደ ምድረ ዓለም) መልሰን፡፡ እኛ አረጋጋጮች ነን፡፡» (የሚሉ ሲሆኑ) ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ታይ ነበር)፡፡

32:13 - በሻንም ኖሮ ነፍስን ሁሉ ቅንነቷን (እምነቷን) በሰጠናት ነበር፡፡ ግን ገሀነምን ከአጋንንትና ከሰዎች የተሰበሰቡ ሆነው በእርግጥ እሞላለሁ ማለት ቃሉ ከእኔ ተረጋግጧል፡፡

32:14 - ይህንንም ቀናችሁን መገናኘትን በመርሳታችሁ ምክንያት (ቅጣትን) ቅመሱ! እኛ ተውናችሁ፡፡ ትሠሩት በነበራችሁትም ጥፋት ዘውታሪን ቅጣት ቅመሱ (ይባላሉ)፡፡

32:15 - በአንቀጾቻችን የሚያምኑት እነዚያ በእርሷ በተገሰጹ ጊዜ ሰጋጆች ሆነው የሚወድቁትና እነርሱም የማይኮሩ ሆነው በጌታቸው ምስጋና (ተጎናጽፈው) የሚያወድሱት ብቻ ናቸው፡፡

32:16 - ጌታቸውን ለመፍራትና ለመከጀል የሚጠሩት ሆነው ጎኖቻቸው ከመጋደሚያ ስፍራዎች ይራራቃሉ፡፡ ከሰጠናቸውም (ጸጋ) ይለገሳሉ፡፡

32:17 - ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ) ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም፡፡

32:18 - አማኝ የሆነ ሰው አመጸኛ እንደ ሆነ ሰው ነውን? አይስተካከሉም፡፡

32:19 - እነዚያ ያመኑና መልካሞችን የሰሩማ ለእነርሱ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት መስተንግዶ ሲሆኑ መኖሪያ ገነቶች አሏቸው፡፡

32:20 - እነዚያ ያመጹትማ፤ መኖሪያቸው እሳት ናት፡፡ ከእርሷ መውጣትን በፈለጉ ቁጥር በእርሷ ውስጥ ይመለሳሉ፡፡ ለእነርሱም «ያንን በእርሱ ታስተባብሉበት የነበራችሁትን የእሳት ቅጣት ቅመሱ» ይባላሉ፡፡

32:21 - ይመለሱ ዘንድም ከትልቁ ቅጣት በፊት (በዚህ ዓለም) ከትንሹ ቅጣት በእርግጥ እናቀምሳቸዋለን፡፡

32:22 - በጌታውም አንቀጾች ከተገሰጸና ከዚያም ከተዋት ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው? (የለም)፤ እኛ ከተንኮለኞቹ ተበቃዮች ነን፡፡

32:23 - ሙሳንም መጽሐፍን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ እርሱን ከመገናኘትህም በመጠራጠር ውስጥ አትሁን፡፡ ለእስራኤል ልጆችም መሪ አደረግነው፡፡

32:24 - በታገሱና በተዓምራቶቻችን የሚያረጋግጡ በሆኑም ጊዜ ከእነርሱ በትዕዛዛችን የሚመሩ መሪዎች አደረግን፡፡

32:25 - ጌታህ እርሱ በዚያ በእርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው (በፍርድ) ይለያል፡፡

32:26 - ከክፍለ ዘመናት ሰዎች ብዙዎችን ያጠፋን መሆናችን በመኖሪያዎቻቸው የሚሄዱ ሲሆኑ ለእነርሱ አልተገለፀላቸውምን? በዚህ ውስጥ ምልክቶች አሉት፤ አይሰሙምን?

32:27 - እኛ ውሃን ወደ ደረቅ ምድር የምንነዳ እንስሶቻቸውና ነፍሶቻቸው ከእርሱ የሚበሉለትንም አዝመራ በእርሱ የምናወጣ መኾናችንን አያዩምን? አይመለከቱምን?

32:28 - «ከእውነተኞችም እንደሆናችሁ ይህ ፍርድ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡

32:29 - «በፍርድ ቀን እነዚያን የካዱትን ሰዎች እምነታቸው አይጠቅማቸውም፡፡ እነርሱም ጊዜን አይሰጡም፤» በላቸው፡፡

32:30 - እነርሱንም ተዋቸው፡፡ ተጠባበቅም፤ እነርሱ ተጠባባቂዎች ናቸውና፡፡

🔝Go to First Ayah 🔝


↩️ ወደ ዋናው ማውጫ ተመለስ

Report Page