ፍርሃትን የሚጥል ፍፁም ፍቅር

ፍርሃትን የሚጥል ፍፁም ፍቅር

http://debregelila.org/?p=1221

በሌሊት ማለፍና በፀሐይ መውጣት መካከል ገና ጨለማ ሳለ ሁለቱ ማርያሞች ማርያም መግደላዊትና የያዕቆብ እናት ማርያም ከሰሎሜ ጋር ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ ሄዱ። በዚህ ግርማ ሌሊቱ ባልተለየው ድምፀ አራዊቱ በሚሰማበት ሌሊት የአይሁዳውያን ዛቻና የኃያላኑን የሮማ ወታደሮች ቁጣ ተጋፍጠው የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ሽቶ ይቀቡ ዘንድ ወደ መቃብሩ ገሰገሱ። እነኚህ ሴቶች የክርስቶስን ሞት ሰምተው መቃብሩን ሊያዩ ከሩቅ የመጡ እንግዶች አልነበሩም ይልቁንም በዕለተ አርብ እየተላጋ ሲወሰድ፣ በየመንገዱ ሲጎተትና መስቀል ተሸክሞ ሲሄድ እያለቀሱ በደም የተዋበ የመስቀሉን መንገድ በእንባ ያጠቡ ሴቶች ናቸው።

ሐዋርያቱ ሸሽተው በሄዱበት አሁን አድን ያሉት የኢየሩሳሌም ሰዎች አሁን አጥፋው ብለው ጲላጦስን በሚማፀኑበት ወቅት ከእግረ መስቀሉ ሥር የነበሩ ሴቶች ናቸው። ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በአዲስ መቃብር ሲቀብሩት ከሩቅ ሆነው ያዩት ሴቶች ናቸው። ጌታቸውን በመቃብር ትተው እንቅልፍ አልወስድ ቢላቸው በሌሊት ተነስተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ሁለቱ ሴቶችን በስም ሲጠራ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ በትንሳኤው ዘርዘር ያለ መገለጥን ያየችው ቅድስት ማርያም መግደላዊት ላይ ዋናውን ትኩረቱን ያደርጋል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ግን የሦስቱንም ስም ዘግቦ እናገኘዋለን። ይሄ አዘጋገብ የታሪክ ልዩነት ሳይሆን የወንጌላውያኑን የትኩረት ነጥብ የሚያሳይ ነው።

እነዚህ ሴቶች ማልደው ወደ መቃብሩ ሲደርሱ ድንጋዩን ማን እንደሚያንከባልልላቸው ተጨንቀው ነበር።
ራሔልና ሴቶቹ የውሐውን ምንጭ መዝጊያ ድንጊያ የሚያንከባልልላቸው አጥተው እስከ ቀትር እንጠብቃለን? ብለው እንደተጨነቁት ማየ ሕይወት ክርስቶስ ያለበትን በጲላጦስ ማህተም ታትሞ በሮማ ወታደሮች የሚጠበቀው የመቃብር ድንጋይን ሚያንከባልላቸው ሰው እያሳሰባቸው ነበር። ሲደርሱ ግን የገጠማቸው ፍፁም ተቃራኒ ነበር። እንደ ያዕቆብ ሆኖ የመቃብሩን ድንጋይ የሚያንከባልል መልአክን እግዚአብሔር ልኮላቸው ነበር። /ዘፍ 29:8-10/

የእስክንድርያው ቅዱስ ቄርሎስ በልደቱ ሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እረኞች አትፍሩ ያሉ መላእክት (ሉቃ 2:10) ዛሬም እጅግ ጨለማ በነበረው ፀሐይ አልባ የማለዳ ጠዋት የመጡትን ሴቶች አትፍሩ አሏቸው እያለ በልደቱ የተሰበከውን የምስራች በትንሳኤው ሌሊት ስለመደገሙ ይደነቃል።

መላእክቱ የተናገሩት ቃል እጅግ የሚያረጋጋ ነበር። የሚፈልጉትን አስቀድመው ያውቁ ነበርና ከሕማማቱ በፊት የነገራቸውን አስታውሰው እንደ ተናገረው ተነስቷል ብለው አወጁላቸው። ይሄንን ዜና የሰሙት አንስት ለሐዋርያት ለመናገር ተፋጠኑ። ቅዱስ ቄርሎስ የቅዱስ ጳውሎስንና የኢሳያስን ቃል ተውሶ ትንሳኤውን ሊያውጁ የተነሱትን እግሮችን መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ሲል ያወድሳል። ሮሜ 10:15፣ ኢሳ 52:7

መነሳቱን ግን በመላእክት ብቻ ሰምተው እንዳይቀሩ እርሱ ራሱም በፊታቸው ታየላቸው። አስቀድመው መላእክት አትፍሩ የተባሉ ቅዱሳን አንስት ከክርስቶስም አንደበት የሚያረጋጋውን ቃል ሰሙ “እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና፦ ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው።” ማቴ 28:9-10

ወንጌላዊው ዮሐንስ ደግሞ ሌላም ቃል ይነግረናል። ሴቶቹ ለደቀመዛሙርቱ ከተናገሩ በኋላ ሐዋርያት ወደ ቦታው መጥተው መቃብሩ ባዶ መሆኑን አይተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ማርያም መግደላዊት ግን ከመቃብሩ አጠገብ ቀረች። ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ነገር ይደመማል። ቅዱስ ጴጥሮስ መቃብሩን አይቶ ተመለሰ ማርያም መግደላዊት ግን እዛው መቅረቷን ከሴትነት ልባዊ ፍቅርና ርህራሄ ጋር ያገናኘዋል። በእውነትም ሴት ያላትን የፍቅር ጥግ አስቀድሞ በመስቀል ኋላም በትንሳኤው ተገለጠልን። የዩሐንስ አፈወርቅን እይታ ገታ አድርገን የወንጌላዊውን ትረካ እንከተል። በጌታ መቃብር ቀኝና ግራ የተቀመጡ መላእክት ምን ትፈልጊያለሽ ብለው ጠየቋት። እርሷም ጌታን ወስደውታል የትም እንዳረጉት አላውቅም። ብላቸው ወደ ኋላ ዘወር ስትል ክርስቶስን አየችው። ታሪኩን ከወንጌላዊው አፍ እናዳምጥ:-

“ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሏት፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት። መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።” ዩሐ 20:14-18

ቅዱስ ቄርሎስ ይሄንን ተመልክቶ እንዲህ ይላል ሞት በሷ በኩል የመጣባት ሔዋን በገነት የአትክልት ስፍራ የሞትን ቃል እንደሰማች ሁሉ (ዘፍ 3:1) ማርያም መግደላዊትም በአትክልቱ ስፍራ ለሞት ሞት የሆነውን ትንሳኤውን ሰማች። ይለናል።

ምናልባት በዚህ ንግግር ውስጥ ክርስቶስ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አላረግኩም የሚለው ቃል ጥያቄ ያስነሳ ይሆናል ። ሊቁ ጠርጡለስ ክርስቶስ ሌላ አምላክ እየጠራ አይመሰላችሁ ይለናል። ይልቁንም ፈጣሪ ያለውን የፍጡር ሥጋን ይዞ እንደተነሳ ሊያመላክት እንጂ እርሱ ፍጡር ሆኖ ሌላ ፈጣሪ ኖሮት አይደለም ይላል በዚህ ሀሳብ ቅዱስ ቄርሎስና አፈወርቅ ዮሐንስም ይስማማሉ ፍጡር ሥጋን ገንዘብ ስላደረገ ተናገረ እንጂ። እግዚአብሔር አብ የእርሱ አባትና አምላክ የሚሆንበት አገባብ ከኛ ይለያልና ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አለ እንጂ ወደ አባታችንና አምላካችን አለማለቱን ቅድስት ቤተክርስቲያን ታስተምራለች።

ወደ ቅዱሳት እናቶቻችን እንመለስ ጌታ እስከመስቀል ላልተለየው ሐዋርያ ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሰጠው ሁሉ እስከመስቀል ለታመኑለት ቅዱሳት የከበረች ትንሳኤውን አስቀድሞ ገለጠላቸው። ባገለገሉት ልክ በወደዱትም መጠን አከበራቸው ቅዱስ ዮሐንስ አፈ በረከት እንዳለው የትንሳኤውን ወንጌል ለሐዋርያት ይሰብኩ ዘንድ የተገቡ አደረጋቸው።

ቤተክርስቲያንም ለዚህ መታሰቢያ የትንሳኤን ስድስተኛ ቀን ቅዱሳት አንስት ብላ ታከብረዋለች።

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ

Report Page