✨ጻድቅወሰማዕት አባ በአሚን✨

✨ጻድቅወሰማዕት አባ በአሚን✨

ወ/ዩ/ግ/ጉ

✨አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታህሳስ ፱ በዚች ቀን ያለ ደም መፍሰስ ታማኝ የሆነ ቅዱስ አባት አባ በአሚን በሰማዕትነት አረፈ።✨


አባ በአሚን በደቡብ ግብፅ በእስሙናይን አውራጃ ለሀገረ ቴርሳ አቅራብያ ከሆኑ ከሐፂብ ተወላጆች ወገን ነው። በዘመኑም ከቅንነቱ የተነሳ "መታመንስ እንደ በአሚን" ይባል ነበር:: ቅንነቱን የወደዱ ሁሉ ይሹት ነበር:: በከተማው ውስጥ እጅግ ብዙ ሃብት የነበራቸው ባል እና ሚስትም ወደ ቤታቸው ወስደው መጋቢ (ተቆጣጣሪ) አደረጉት::


እርሱ ግን የዚህን አለም ፍፃሜ አሰበ የባለ ፀጋውንም አገልግሎት ትቶ ወደ ገዳም ሄዶ መነኮሰ።


ባለፀጋውም መሄዱን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ሚስቱንም ይዞ አባ በአሚን ወዳሉበት በአንድነት ሄዱ ውድ እርሳቸውም እንዲመለሱ ለመኑት እንዲህም አሉት ከአንተ እንለይ ዘንድ ከቶ አንችልም ስለዚህ አንተውህም አሉት።


አባ በአሚንም እኔ ራሴን ብፅእት አድርጌ ለእግዚአብሔር ሰጥቻለው እኮን አላቸው ይህንንም ሲሰሙ ከእርሱ በመለየታቸው እጅግ እያዘኑ ትተውት ሄዱ።


ከዚህም በኃላ በታላቅ ተጋድሎ ብዙ ዘመናትን እግዚአብሔርን አገለገለ። ዜና ሰማዕታትም ቀስ እያለ ቅዱሱ ወዳለበት ገዳም ደረሰ::


ነገሩን ሲሰማ ደስ አለው:: እርሱ ስለ ክርስቶስ ሲሉ ደምን ማፍሰስና መከራን መቀበል ከሁሉም ነገር የተሻለ እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና:: ቀጥሎም ወደ ከተማ ሒዶ ደሙን ለማፍሰስ በቁርጥ ወስኖ ዘለቀ::


በዚያም የንጉሥ ወታደሮች አግኝተውት ለጣዖት ይሰዋ ዘንድ ታዘዘ:: ቅዱስ በአሚን ግን "መስዋዕት የሚገባው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ነው:: ለፍጡር አልሰዋም" ሲል መለሰላቸው:: በዚህም ምክንያት ወታደሮች እየተፈራረቁ ደበደቡት::


ደሙንም አፈሰሱት:: ምንም እንዳልተለወጠ ሲያውቁ ወደ እስር ቤት ጨመሩት:: ከዚያም በቀን በቀን እያወጡ ይደበድቡት: በእሳት ያቃጥሉት: በተለያዩ ማሰቃያዎች በመከራ ያውሉት ነበር:: እርሱ ግን ክርስቶስን ከመቀደስ በቀር አንዳች አይመልስላቸውም ነበር::


በብዙ አሰቃይተው እንቢ ቢላቸው ወስደው በጨለማ ቤት ዘጉበት:: በዚያም ጥለውት ዓመታት አለፉ:: ሁሉንም በጊዜው የሚሠራ ጌታ ግን እነዚያን የመከራ ዘመናት አሳልፎ ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስን አጠፋቸው::


እነዚህ አበው ቅዱሱን ንጉሥ ባርከውት ሲመለሱ ቅዱስ በአሚን ወደ እስሙናይን ተጉዞ በበዓቱ ተቀመጠ:: በዚያም ደቀ መዛሙርት በዝተውለት እንደ ገና ገዳማዊ ሕይወቱን ቀጠለ:: በበዚያም ሳለ ብዙ ተአምራትን ሠራ::


ድውያንን ፈወሰ:: መናፍቃንንም በጸሎቱ ከአካባቢው አራቀ:: አንድ ቀንም የሮም ንጉሠ ነገሥት ሚስት ወደ እርሱ ዘንድ መምጣቷን ሰማ:: ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ገብተው "አባ! ንግሥቲቱ ትፈልግሃለች" አሉት::


እርሱ ግን "እኔ ከምድራዊ ንግሥት ዘንድ ምን አለኝ! አልወጣም" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱ ግን መልሰው "አባ! እዘንላት: በመከራ ውስጥ ናት" ሲሉት "እሺ" ብሎ ወጣ::


ንግሥቲቱ ምንም ብዙ ሠራዊት ብታስከትል አንጀቷ ታጥፎ ተጐንብሳ ነበር የምትሔደው:: እርሱም በጀሮዋ ጠጋ ብሎ የሕመሟን ምሥጢር ሲነግራት ተገርማ እግሩ ሥር ወድቃ ተማጸነችው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-


ከ15 ዓመታት በፊት አንድ የተባረከ ዲያቆን በቤተ መንግስቷ አካባቢ ይኖር ነበር:: እርሱም (ዮሐንስ ይባላል) የዮሐንስን ራዕይ ቁሞ ዘወትር ያነብላታል:: በዚህ የቀኑ የንጉሡ ባለሟሎች በሃሰት "ሚስትህን ዲያቆኑ እያማገጠ ነው" ሲሉ ለንጉሡ ነገሩት::


ንጉሡም ነገሩ እውነት ስለ መሰለው ወታደሮቹን ዮሐንስን ከነ ሕይወቱ ባሕር እንዲያሰጥሙት አዘዘ:: ይሕንን የሰማችው ንግስት ለቀናት ስታለቅስ አንጀቷ በመቃጠሉ ታመመች:: እየቆየም ሆዷ ታጠፈ:: ለ15 ዓመትም የሚያድናት አጥታ ተንከራተተች::


በሁዋላ ግን ሰዎች ስለ ቅዱስ በአሚን ቅድስና ሲናገሩ ሰምታ መጣች:: ለዛ ነው ቅዱስ በአሚን ምሥጢሯን ሹክ ያላት:: ቀጥሎም 2 በጐ ነገርን ፈጸላት:: መጀመሪያ ጸሎት አድርጐ ሆዷን ቢዳስሳት በቅጽበት ድና ቀና አለች::


2ኛው ግን "ያ የምትወጂው የተባረከ ዲያቆን ዮሐንስ አልሞተም:: መላዕእክት ከባሕር አውጥተው እገሌ በሚባል ደሴት አኑረውታል" አላት:: እርሷም ተመልሳ በደስታ ለባሏ ነገረችው::


ንጉሡም ተጸጽቶ ዮሐንስን ካለበት አስመጣው:: አበውም የሮሜ ሊቀ ዻዻሳት አድርገውት ብዙ መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ቅዱስ በአሚን ግን በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፎ በዝማሬ ተቀብሯል::


እግዚአብሔር አምላክ በቅዱስ በአሚን በጸሎቱ ይማረን:: ከትእግስቱ ይክፈለን:: ከበረከቱም ያሳትፈን::

1.ቅዱሳን 318ቱ ሊቃውንት

4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን

=>+"+ አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ክፉውን አሸንፋቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ልጆች ሆይ! አብን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ብርቱ ስለ ሆናችሁ: የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር: ክፉውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላቹሃለሁ:: +"+ (1ዮሐ. 2:13)


<<<ወለወላዲቱ ድንግል>>>


<<<ወለመስቀሉ ክቡር>>>


✞ይቆየን✞


Report Page