ይድረስ ለኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክት እና ቤተሰብ ተቃዋሚዎችና ተቺዎች እንዲሁም አሳዳጆች በሙሉ!

ይድረስ ለኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክት እና ቤተሰብ ተቃዋሚዎችና ተቺዎች እንዲሁም አሳዳጆች በሙሉ!

በተክለኪዳን

ጥቅምት12፥2014 ዓ.ም

ይድረስ ለኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክት እና ቤተሰብ ተቃዋሚዎችና ተቺዎች እንዲሁም አሳዳጆች በሙሉ!

ዓመጻ፣ ክህደት፣ ርኩሰት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ሐሰተኝነት፣ ግፍ፣ ጭከና…ወዘተ በነገሠበት ዘመን፤ እንዲሁም እናት አገራችን ኢትዮጵያ በሚያሳዝን ፈተናና መከራ ዉስጥ ባለችበት በአሁን ወቅት፤ በተለያየ ቦታ ግፍና መከራ እየደረሰባቸዉ ስላሉት ምስኪኖች፣ ደማቸዉ በከንቱ ስለሚፈሰዉ ወገኖች፣ ስለ ቅኖችና እዉነተኞች ሲል፤ እግዚአብሔር የመከራዉንና የፍርዱን ዘመን እጅግ አሳጥሮልንና በቃችሁ ብሎን መልካሙን ዘመን እንዲያመጣልን ከመቼዉም በላይ ወደ ፈጣሪ አምላክ ማንባትና መጸለይ እንዲሁም በእዉነተኛ ንስሐ መመለስ በሚገባበት ወቅት፤ በአምላካቸዉ ከመተማመንና ከእርሱ የሆነዉን ከመጠበቅ ዉጭ አንዳች ሥጋዊ ኃይል የሌላቸዉን፣ ትምክህታቸዉ አንዱ እግዚአብሔር እንጂ ግለሰብ ሆነ ቡድን እንዲሁም ተቋምና መንግሥት ያልሆነ፤ በሰዉ ዐይን ሲታዩ እዚህ ግቡ የሚይባሉ ምስኪን ኢትዮጵያዉያን፣ የአንዲቷ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት አማኝና ተከታይ የሆኑ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆችን፣ እዉነተኛዉን የኢትዮጵያ ትንሣኤ በተለየ ሁኔታ የሚጠብቁትን የኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን ቤተሰብ ላይና የኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክት ላይ፤ "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ነን" በሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በተለያየ መልኩ የማጥላላትና የማጥቃት ዘመቻ መሰለፉ፤ በእዉኑ እግዚአብሔርን፣ ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን ለማስደሰት ነዉ ወይስ የጨለማዉ ገዥ ዲያብሎስንና የእርሱን አገልጋዮችን?!  

መቼስ የእዉነተኞች ማንነት መለያዉ ፈተና ሲመጣ ነዉና ከ2013 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክትና በመልእክት አድራሾቹ ላይ እንዲሁም ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን ቤተሰብ ላይ የተለያየ የማጥላላትና የማጥቃት ዘመቻ በአራቱም ማእዘን መከፈቱ ይታወቃል፡፡ እንደ ጸሐፍት ፈሪሳዉያንና አይሁድ ካህናት፤ በጸጋ እግዚአብሔር ሳይሆን በእዉቀታቸዉ ብቻ በሚያገለግሉ ዘንድ ይህ ቢፈጸም የሚጠበቅ ነዉ፡፡ ለእነሱ መሪያቸዉ እዉቀታቸዉ እንጂ መንፈስ ቅዱስ ስላልሆነ በእነሱ እዉቀትና አስተሳሰብ ደረጃ መልእክቱና አገልግሎቱ ተገምግሞ ተቀባይነት አለማግኘት አይደለም ሌላም ነገር ቢፈጽሙ የሚጠበቅ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ፍጡራን በሆኑትና እንደ ሥጋ ለባሽነታቸዉ ጉድለት ሊገኝባቸዉ በሚችሉት በእግዚአብሔር አገልጋዮችና መልእክተኞች ላይ ተቃዉሞና ጥቃት መፈጸም አይደለም፤ እርሱ የፈለገዉን በፈለገዉ መንገድና ጊዜ ማከናወን በሚችለዉ፣ የእያንዳንዱን ዉጫዊዉን ማንነት ብቻ አይደለም ዉስጣዊዉን ማንነት ጭምር የሚያዉቀዉ፣ አንዳች ጉድለት በሌለዉ ፍጹም በሆነዉ ፈጣሪ አምላክ በእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተቃዉሞና ትችት ብቻ አይደለም የእዉቀትና የልማድ አገልጋዮችና አማኞች ከሕሊና በላይ መከራና ስቃይ አድርሰዉበታለም፡፡ ከዚህ አንጻር በእግዚአብሔር እዉነተኛ አገልጋዮችና መልእክተኞች ላይ እየደረሰ ያለዉ ተቃዉሞና ማጥላላት እንዲሁም ጥቃት እጅግ አነስተኛ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ 

ምንም እንኳን እንደ ሥጋ ለባሽነታችን የሐሰትና የክፋት ድርጊቶችና ዉንጀላዎች እንዲሁም ፍረጃዎች የሚያሳዝኑና የሚያስተዛዝቡ ቢሆንም፤ ለሁሉ ጊዜ ገደብ አለዉና በቅርቡ በእግዚአብሔር ቀን በመልካሙ ዘመን በኢትዮጰያ ትንሣኤ፤ "ማነዉ እዉነተኛዉ፣ ማነዉ ሐሰተኛዉ" ለሚለዉ በግልጽ ምላሽ መገኘቱ አይቀርምና፤ ሁሉን በትእግሥትና በጽናት እንዲሁም በተጋድሎ ማሳለፍ ከእያንዳንዱ እዉነተኛ አገልጋይና አማኝ ይጠበቃል፡፡ ለእኔ እጅጉን የሚገርመኝና የሚያሳዝነኝ፤ "ከእግዚአብሔር ጋር፣ ከእመ አምላክ ድንግል ማርያም ጋር፣ ከቅዱሳን ጋር የተለየ ግንኙነት አለን" በማለት አገልግሎትና ምስክርነት የሚሰጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን፤ የኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክትን በአግባቡ ሳይመረምሩ በድፍረትና በትዕቢት ሲቃወሙ፣ ሲያጥላሉ፣ ሲተቹ እና በማይሆን መንገድ ሲፈርጁ ነዉ፡፡ ለእኔ እነዚህ ሰዎች በጸጋ እግዚአብሔር እንደማያገለግሉ እና የእዉቀትና የልማድ አገልጋዮች ወይም በአታላዩ መንፈስ የሚመሩ እንደሆኑ ነዉ የሚያረጋግጥልኝ፡፡ ከእግዚአብሔር የሆኑ እዉነተኞች ቢሆኑ ኖሮ፤ "እግዚአብሔር፣ ድንግል ማርያም፣ ቅዱሳን ተገልጸዉ እንዲህ እንዲያ ብለዉኛልና፤ ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክትና መልእክት አድራሾቹ ሐሰተኞች ናቸዉ" በማለት ምስክርነት ይሰጡ ነበር እንጂ፤ "እንዲህ ይላሉ፣ እንዲህ መሰለኝ..ወዘተ" እያሉ በአግባቡ መልእክቱን ሳይመረምሩ በስማ በለዉ ብቻ በድፍረትና በትዕቢት ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክትንና ቤተሰብን አይቃወሙም፣ አያጥላሉም፣ በሐሰት አይፈርጁም ነበር፡፡ እነዚህ አስመሳይ አገልጋዮች ከራሳቸዉ አልፎ ለሌላዉ ነፍስ መሰናከል ምክንያት ሆነዋልና በሥጋም በነፍስም የባሰዉ ፍርድ እንደሚጠብቃቸዉ በእምነት ዉስጥ ላለ ሰዉ ይታወቀዋል፡፡

እኔ በግሌ ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክትን ከነሐሴ 2002 ዓ.ም ጀምሮ ከቁጥር 1 እስከ 3 ያሉትን መልእክቶች በአግባቡ ያነበብኩና ምንም እንኳን የዓለም ዋና ኃጢአተኛ፣ ደካማና መሃይም ሰዉ ብሆንም፤ እንደ ኃጢአቴና ስንፍናዬ ያልተመለከተኝ አምላክ፤ በቸርነቱና በምሕረቱ መልእክቶቹ ፍጹም ከእርሱ እንደሆነና መልእክት ጸሐፊዉም በእግዚአብሔር የተመረጠና የተቀባ መሆኑን ከሁሉ ፈጣሪ አምላክ ከኢየሱስ ክርስቶስ በመስከረም 2003 ዓ.ም ማረጋገጫ አግኝቻለሁና አሁንም ወደፊትም "መሰለኝ፣ እንዲህ ይባላል…ወዘተ" ሳልል፤ በግልጽና በእዉነት የእግዚአብሔርና የእመ አምላክ ድንግል ማርያም እዉነተኛ ባለሟልና እንደራሴ እንደሆኑ ምስክርነትን እሰጣለሁ፡፡ ሐሰተኛ ከሆንኩ ደግሞ እኔም ሆንኩ የምመሰክርላቸዉ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያጋልጠንና እንዲያዋርደን ጸሎቴ እንደሆነ በዚሁ አጋጣሚ አሳዉቃለሁ፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔርንና ከእግዚአብሔር የሆነዉን እዉነት ብቻ የምፈልግ ሰዉ ነኝ እንጂ የራሴን ክብር፣ ዝና፣ የምፈልግ አይደለሁም፡፡ 

እንዲሁም የግሌ የሥጋና ደም ስሜት ስዉር ዓላማና ግብ የለኝም፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ መፈጸምና ማስፈጸም ነዉ ዓላማዬም፣ ግቤም እንጂ የግለሰቦችን ሆነ የቡድኖችን እንዲሁም የዲያብሎስን ዓለማና ግብ ማስፈጸም አይደለም፡፡ በፊትም አሁንም ወደፊትም የዲያብሎስ መሳሪያና አገልጋይ እንዳልሆን ሁል ጊዜ ፈጣሪዬን በጸሎት የምማጸን ሰዉ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ተስፋዬ የዐይን ቅድበት እድሜ የምኖርባት ጎስቋላዋ ምድር ሳትሆን፤ ለሕያዉነት ዘመን የምኖርባት የማታልፈዉ ሰማያዊ መንግሥት ናትና፡፡ እንዲሁም የ7513 ዓመት ሰዎችን ተመሳስሎ የማሰናከልና የማሳሳት ልምድ ያለዉ ዲያብሎስ ስንቶቹን የተመረጡና ከፍታ ቦታ ላይ የደረሱትን ሳይቀር በትንሽ ክፍተታቸዉና የሥጋና ደም ፍልስፍናቸዉ በመግባት አሰናክሏቸዋል፣ አሳስቷቸዋልና፡፡ እኔ ደግሞ ከሁሉ በላይ ደካማና ኃጢአተኛ ነኝና ተመሳስሎ እጅግ ሊያሰናክለኝና ሊያሳስተኝ ይችላልና፡፡

በስተመጨረሻ ለኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን ቤተሰቦች የማስተላልፈዉ ወንድማዊ ምክሬ፤ " እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ ብርሃናችሁ በሰዉ ፊት ይብራ" እንደተባለዉ፤ መገለጫችን ሊሆን የሚገባዉ በእዉነተኛነት፣ በትህትና፣ በትዕግሥት፣ በፍቅር፣ በቅንነት፣ በታማኝነት፣ በንስሐ ሕይወት መኖር ነዉ እንጂ፤ የሥጋ ትምክህት፣ የሥጋና ደም አካሄድ፣ ክፋትና ተንኮል፣ ጥላቻና በቀል፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት የመሳሰሉት እንኳን ለነፍሳችን አይደለ ለሥጋችንም የማይጠቅሙን ናቸዉና፤ ከእነዚህ ባሕርያትና ጠባያት ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ልንለይ ይገባል፡፡ ሌላዉ ደግሞ ተዋሕዶ እምነታችንንና ቅድስት ቤተክርስቲያንን በልማድ ሳይሆን በሚገባ አዉቀን የምንኖርበት፤ ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክትንም በሚገባ አንብበን ወይንም አዳምጠን ይዘቱን፣ ዓላማዉን፣ መልእክቱን መረዳት ይኖርብናል እንጂ በስማ በለዉ መከተል የለብንም፡፡ ምክንያቱም መልእክቱን በሚገባ ከተረዳንና ካስተዋልን ከኅዳር 1998 ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 2013 ዓ.ም የተላለፉት ስምንት መልእክታት በኢትዮጵያ ሆነ በዓለም እየተፈጸመ ስላለዉ ነገር አስቀድሞ የገለጸዉን እየተመለከትንና ወደፊትም የሚፈጸመዉን በሚገባ የምናዉቅበት ነዉ፡፡ እንዲሁም በዓመፃ ሰዎች ክፋትና ተንኮል ተግባርና ንግግር እንዲሁም የሐሰት ወሬና ፍረጃ አንሰናከልም፡፡ 

የኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን መልእክት ስለ አንዲቷ የሕይወት መንገድ ስለሆነችዉ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትና ቅድስት ቤተክርስቲያን የሚመሰክር፤ በመልካሙ ዘመን እንኳን ለኢትዮጵያዉያን ብቻ አይደለም ለዓለም እንደምትተርፍና ኢትዮጵያም ከወደቀችበት ተነሥታ የዓለም መሪ እንደምትሆን፣ ስለ አንዲቷ አረንጋዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማዋ የሚመሰክር፣ ትዉልዱ ራሱን ለእዉነተኛ ንስሐ እንዲያበቃና የእግዚአብሔርን እዉነት እንዲቀበል ጥሪ የሚያቀርብ፣ አገልጋዮች ሆኑ አማኞች ድኅነትን እንዲያገኙ እምነትን ከምግባር ጋር አዋሕደዉ እንዲይዙ የሚያሳስብ፤ ስለ ተዋሕዶ እምነትና ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተጋድሎ እንዲደረግ የሚገልጽ፣ ትዉልዱ ስለ ሃይማኖቱ ሆነ ስለ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ መንፈሳዊ ቅናት እንዲያድርበት የሚያደርግ እንጂ፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት፣ ሥርዓት፣ እግዚአብሔራዊ አስተምህሮና ትዉፊት የሚያወጣና የሚለይ አይደለም፡፡ ይልቁኑ ትዉልዱ የቀደሙት የቅዱሳን አባቶችና እናቶች ሕይወት ይዞ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት አክብሮ እንዲኖር የሚመሰክር ነዉ እንጂ፤ "ንስሐ አትግቡ፣ ቅዱስ ሥጋዉና ክቡር ደሙ አትቀበሉ፣ ወደ ቤተክርስቲያን አትሂዱ" የሚል አይደለም፡፡

 እንዲሁም አምላካችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በእዉነትና በመንፈስ እንዲመለክና እንዲመሰገን፤ እመ አምላክ ድንግል ማርያም፣ ቅዱሳን መላእክት፣ ጻድቃን ሰማዕታት በሚገባ እንዲከበሩና እንዲፈቀሩ የሚመሰክር ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዓመፃና የክህደት ተግባር ከሚፈጽሙ አስመሳይ አገልጋዮች ጋር "አንድነትና ሕብረት አትፍጠሩ፣ የዓመፃቸዉና የክህደታቸዉ ተባባሪ አትሁኑ" ብሎ የሚመክር፤ ያ ብቻ አይደለም በሥጋዊ ሆነ በመንፈሳዊ ወንበር ላይ የተቀመጡት የአስመሳይ አገልጋዮች የዓመፃ፣ የክህደት፣ የርኩሰት ተግባር ያሳወቀና እጣ ፈንታቸዉን ጭምር የሚገልጽ ነዉ፡፡ 

እኔም ቀደም ሲል የነበረኝን እምነት ያጠናከረልኝ፤ የአገር፣ የወገን፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትና የቅድስት ቤተክርስቲያን ፍቅር የበለጠ እንዲያድርብኝና መንፈሳዊ ቅናት እንድላበስ ያደረገ ነዉ እንጂ፤ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት፣ ከተዋሕዶ እምነትና ከቅድስት ቤተክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓት፣ እግዚአብሔራዊ አስተምህሮና ትዉፊት የሚለየኝ ቢሆን ኖሮ፤ የመጀመሪያዉ ተቃዋሚና ራሴን ከዚህ ቤተሰብ የምለይ ነበር፡፡ አሁንም ወደፊትም እግዚአብሔር በመሰከረላት በአንዲቷ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ዉስጥ ያለሁ፤ በገጠርም፣ በከተማም፣ በዋሻም፣ በገዳምም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ቅዱስ ሥጋዉና ክቡር ደሙ በብቸኝነት ከሚሰዋባት ከአንዲቷ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሕይወት ያልተለየሁ፣ እምነቷንና ሥርዓቷን እስከመጨረሻዉ አክብሬ የምኖርና ሌላዉም አክብሮ እንዲኖር የምመክር፤ ምስክርነቴም ከእግዚአብሔር ለሆነዉ እዉነታ ብቻ የሆነ፤ ሁሌም ኃጢአቴንና ዓመጸኛነቴን የማምንና እንባዬንም ወደ ፈጣሪ የማፈስ ሰዉ ነኝ፡፡ ይላል እጅግ በቅርቡ (ጊዜዉ ማለትም ከቀናት በኋላ ይሁን ከሳምንታት፣ ከወራት በኋላ ይሁን ከዓመታት በኋላ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚታወቅ)፤ ከሚመጣዉ ከመደምደሚያዉ የእግዚአብሔር ቁጣና ጠረጋ በኋላ የሚመጣዉን መልካሙን ዘመን እዉነተኛዉን የኢትዮጵያ ትንሣኤ በታላቅ ተስፋ የሚጠብቀዉ ወንድማችሁ ከእግዚአብሔር ዉዳቂ ባሪያ አንዱ፡፡

ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር!

ኢትዮጵያ የሥላሴ የክብራቸዉ መገለጫና መመስገኛ ምድር!

ኢትዮጵያ ርስተ ድንግል ማርያም!

ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን!

ኢትዮጵያ የዓለሙ ገዥ!

ከሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ

፲፪፥፪፥፳፻፲፬

Report Page