የስበት ሕግ ምንድነው? (what is the law of attraction?)

የስበት ሕግ ምንድነው? (what is the law of attraction?)

ናዝራዊ Tube Telegram channel


ከመታለል መንቃት ( Wake up from deception!) 



የስበት - ሕግ ምንድነው? ( What is the law of attraction?)፦

           

              ክፍል አንድ

አጭር ዳሰሳ፦  በነቢዩ ኢሳይያስ ተክሌ



የስበት ሕግ ( law of attraction) ወንጌላዊ አማኝ በሆነውም - ባልሆነውም ።  የመጽሓፍ ቅዱስ ሰባኪ በሆነውም -  በአነቃቂ ተናጋሪም ( motivational speakers) ።   እንደገናም በእግዚአብሔር ሕልውና በሚያምነውም ፣በዩንቨርስ ልዕለ- ተፈጥሮአዊ ኅይል( “universal energy force,)  በሚደገፈውና እምነቱን  በእርሱ ላይ በጣለውም  ሰው ዘንድ፣ ሌት ከቀን የሚያውጠነጠን፣ አዲስ ራስ -ተኮር  ግለ ኅይማኖታዊ ልምምድ ውስጥ የተገባበት፣ ከመጽሓፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር እየተጎናጎነ እንግዳ ትምህርት እና አነቃቂ ንግግር የሚሰጥበት ይህ የስበት ሕግ (law of attraction ) በእውነት ምንድነው?



በአሁኑ ወቅት በአገራችን  ያሉ አንዳንድ የአገር መሪዎች እንኳ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብና ልምምዱ ያላቸው  መስለው የታዩበት አጋጣሚዎች ተስተውለዋል። “የጥቁሩን ነጭ ነው ብለህ”  እመን ፣ እየራበን አልተቸገርንም ፣ እጅጉን ባሽቆለቆለ ኢኮኖሚና ድህነት ውስጥ የልጽገናል አስተሳሰብ በአገሪቱ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ አለ ብለው ትችት የሚያቀርቡም ሰዎች አሉ። ፍልስፍናው የፓለቲካንም ሆነ የኅይማኖትን  ሰዎች ጨምሮ ( በተለይም የፕሮቴስታንቱን ማለት ይቻላል) ፣ በሁሉም ዓይነት ሰዎች አስተሳሰብ ውስጥ ተገኝቷል። በአገራችን የአስተሳሰቡና የልምምዱ መስፋፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ በተደራራቢ የሥራ ኅላፊነት እና  በመጠነኛ የጤና እክል ተያዝሁ እንጂ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ለሁሉም ሰው በተከታታይ ጽሑፍ  ሊደርስ የሚችል አንድ ወጥ የምርምር ጥናት ጀምሬአለሁ፤ ይሁን እንጂ አሁን እንደ አገር ባለነበት የኢኮኖሚ ፣ የፓለቲካና ማህበራዊ ሁኔታ ከችግሮች እንደ ልዩ የማምለጫ መንገድ ተወስዶ ብልጦች እየነገዱበት፣  ብዙዎች እየተወሰዱበት ስለመጣ በዚህ ጹሑፌ ስለ ስበት ሕግ ( law of attraction) ምንነት ትንሽ ለማለት አሰብሁ። ከወዲሁ ግን ይቅርታ የምጠይቃችሁ  እንዲህ ዓይነት ርዕሰ ጉዳይ በባህሪው  ዘለግ ስለሚል ትረዱኝ ዘንድ ጹሑፌን  ጨርሳችሁ እንድታነቡት ነው።  በትጋት አንባቢ መሆን እና ንባብን እንደ ባህል መያዝ ሙሉ ሰው ያረጋል ይባል የለ?።



ከዛሬ አሥራ አምስት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ሳልወጣ   ብዙ የምዕራባውያን እና   የሩቅ ምሥራቅ ኅይማኖታዊ ልምምድንና ፍልስፍናን የያዙ መጽሓፎች ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ እየተተረጎሙ ለአንባቢያን  የቀረቡበት ጊዜ እንደ ነበር አስታውሳለሁ ። በእነዚህ ጊዜያቶች ለአንባቢያን ተተርጉመው ከቀረበት መጽሓፎቶች አንዱ ምስጢሩ ( The Secret) የሚለው መጽሓፍ ነው። “ምስጢሩ” በአውስትራሊያዊቷ ደራሲ በሮንዳ ባይርን ( Rhonda Byrne) ለተለቀቀ የመጽሐፍ እና የዲቪዲ ሥራ የተሰጠ ስያሜ ነው።  እንደ ባይርን አባባል  በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጣር በ2004 ዓ.ም  ሕይወቷ   በከፍተኛ  ሁኔታ እየፈራረሰ  እና ውጥንቅጥ  ውስጥ የነበረበት ጊዜ ነበር። በዚህ ወቅት የባይረን ሴት ልጅ በ1910 ዓ. ም በዋላስ ዲ . ዋትልስ የተጻፈውን “The Science of Getting Rich” የተባለውን መጽሐፍ  እንድታነበው ሰጠቻት። ከዚያም ሮንዳ ባይርን  መጽሓፉን ማንበብ በጀመረችበት ጊዜ ስለ ነበራት ስሜት ስትናገር  “ መጽሓፉን በማነብበት ወቅት በውስጤ የሆነ የማላውቀው ኅይል ገጾቹን አንድ በአንድ እንድገልጥ ያረገኝና ይገፋፋኝ ነበር፣  እያነበብኩትም ሳለ ድንገት እንባዬ  ዱብ... ዱብ... ዱብ ..እያለ ገጾቹን  ሲመታ  አስታውሳለሁ። በዚያን ወቅት የምስጢሩን ፍንጭ ተቀበልኩት ። ሚስጥሩን በተቀበልኩበት ወቅት የሚስጥሩ ኅይል በልቤ ውስጥ እንደ ነበልባል እሳት  ይነድ ነበር። ይህ ነበልባላማ እሳት  በየአንዳንዲቷ  ቀን እያደገ እያደገ  መጥቶ በመጨረሻም  ለዓለም ሁሉ የሚካፈለው ወይም የማጋራው ትልቅ ምስጢራዊ ብርሃናማ እሳት ሆነ”  ትላለች ። ሮንዳ ባይረን ይህንን ምስጢር የምትለውን በመጽሓፏ  ውስጥ “የመሳብ ሕግ”  (Law of attraction) ብላ በተለዋጭ ጠራችው።



ባይረን የምታምነው “ማንም ሰው በሕይወቱ የሚሆነው ወይም የሚከሰተው ነገር ፣ ወደ ራሱ ሕይወት በንግግር ወይም በሓሳብ  በአሉታዊም ይሁን በአዎንታዊ መልኩ የሳበው ነገር ነው” ብላ ነው ።  እንደ ሴትዬዋ አገላለጽ ሰው በሓሳቡ አይቶታ  ( visualization) የሚስላቸው ማናቸውም ነገሮች  ከዩንቨርሱ ውስጥ ወደ እርሱ  ተስበው የመምጣት አቅም አላቸው። ስለዚህ የምትሆነውና በሕይወትህ የሚሆነው  ያሰብከው ነገር ነው እንጂ ሌላ ምንም ታዕምር የለም ። በአእምሮህ ውስጥ የሆነ ነገር  ስታስብ ወደ አንተ እየሳበህ ነው፣ ቁም ነገሩ ምን እንደምታስብ ማወቅ ነው” ትላለች።



ባይረን የምስጢሩ ጠባቂዎች ( guardians) ለምትላቸው  2006 ዓ.ም የመጻሕፏን ጭብጥ የሚተርክ ፊልም  ለቃለች። ይህ ዶክሜንተሪ ፊልም የኳንተም ፊዚክስ ልዩ ትርጓሜ ላይ በመመስረት ሁሉንም ዓይነት የሜታፊዚካል የይገባኛል ( Claims) ጥያቄዎችን የሚያቀርብ ነው።  ቀደም ብየ እንደገለጽሁት እንደ ሴትየዋ  አባባል የምስጢሩ ቁልፍ አካል “የመሳብ ሕግ ( Law of attraction) ” ተብሎ የሚጠራው ነው ፣ ይህንንም የስበት ሕግ  “ሀሳቦች ነገሮች ይሆናሉ “ በሚል ሦስት ቃላት አጠቃለዋለች።  በሌላ አነጋገር  ለመጽሓፎቿ  አንባቢዎች የምትላቸው  “ስለ አንድ ነገር በበቂ ሁኔታ ካሰባችሁ ይከናወናል” ነው። ትምህርቷ አዎንታዊ  ሀሳቦችን ካሰባችሁ ጥሩ ነገር ታጭዳላችሁ ። በአንጻሩ ደግሞ አሉታዊ ሀሳቦችን የምታስቡ ከሆነ፣ መጥፎ ነገሮች ይደርሱይባችኋል የሚል ነው። አክላም ማንም ሰው የራሱን  ሁኔታዎች መፍጠር ይችላል፤ ይሁን  እንጂ ማንም ሰው በሓሳቡ  እነዚያን ሁኔታዎች መቀየር ይችላሉ ትላለች።



በእሷ አገላለጽ  "የመሳብ ሕግ ( “The Law of Attraction”)" ማእከላዊ ትምህርት፣ አንድ ሰው የሚፈልጋቸውን የትኛውንም ነገሮች  በሃሳብ  በአዎንታዊ መልኩ  በቋሚነት  ወደ ራሱ ካልጠራ በቀር ፣ ወደ ልምዱ ምንም ነገር ሊመጣ እንደማይችል ነው፤  ስለዚህ፣ “ አሁን በዙሪያህ ያለው ነገር ሁሉ (ጥሩም ሆነ መጥፎው) ወደ እናንተ ይሳባል።  በፈለከው ነገር ላይ ስታተኩር  የዚያን ነገር አተሞች ንዝረት እየቀየርኸው ነው ማለት ነው።  ስለዚህ በምትፈልገው ነገር ላይ በዐይነ ሕሊናህ አይቶታ ( visualization) አተኩር። እያተኮርህ ስትመጣ  የአተሙ ንዝረት ወደ አንተ መንቀጥቀጥ ይጀምራል  :: ሀብትን፣ ጤናን እና እርካታን በተሻለ መንገድ የምታገኝበትን የድግግሞሽ ንዝረት የምትወስነው አንተ  ብቻ ነህ፤ ። .ሓሳብህ በዩንቨርስ ውስጥ ካለው ኅይል ጋር  የተስተካከለ ( aligned) ስታደርገው  ያን በአዎንታዊ መልኩ ያሰብከውን  ነገር የአጽናፈ ዓለሙ ጉልበት ወይም ኅይል (universal energy force) ወደ አንተ ይለቀዋል” ትላለች።  





ይህን ሃሳብ ከመጨረሴ በፊት እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ በሉ።  አጽናፈ ዓለሙ ( The universe) በእግዚአብሔር ተፈጠረ እንጂ አጽናፈ ዓለም በእግዚአብሔር ቦታ ራሱን ተክቶ ለሰው ልጅ የሚያደርገውን ሆነ የሚሰጠው ምንም ነገር የለም።  ቃሉ የሚለን ግን “ በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ነው ( ያዕ 1፣ 17)።



ይቀጥላል ........

ናዝራዊ Tube

Report Page