⛪️ ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ⛪️

⛪️ ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ⛪️

http://debregelila.org/?p=1214

የክርስቶስን መከራና ሕመም ኬርኤላይሶን ብለን ያሰብንበት ዕለተ ስቀለት ካለፈ አንድ ሳምንት ሞላው። በስግደትና በሐዘን ያሰብነው ሕማሙ መዳረሻው ለእኛ ካጠላብን የሐዘን ቀንበር ነፃ መሆን ነውና የከፈለልንን ፍፁም ፍቅር ለማሰብ ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰሙነ ትንሳዔውን የመጀመሪያ አርብ ቅድስት ቤተክርስቲያን ብላ ትሰይመዋለች።

ዕለተ አርብ ቤተክርስቲያን ተብሎ የመሰየሙ ምስጢር መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ የተቀበለውን መከራ ለማን ብሎ ነው የተቀበለው ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ነው። ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም መፍሰስ የዘመናዊው ዓለም ምዕራባዊ ክርስትና እንደሚያስበው እያንዳንዱን በነጠላ በግል ለማዳን ሳይሆን እያንዳንዱን በቃሉና በደሙ በመሰረታት ሕብረት በኩል የራሱ አካል ለማድረግ ነውና።

የመጽሐፈ ሰዓታቱ ሊቅ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመሐረነ አብ ጸሎቱ መግቢያ ሃሌ ሉያ ብሎ ይጀምርና ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ተጸፋእከ በውስተ ዓውድ ከመትቀድሳ በደምከ ክቡር ዘበእንቲአሃ ዝግሃታተ መዋቅሕት ጾረ ወተአገሰ ምራቀ ርኩሰ እንዘ አልቦ ዘአበሰ አምላክ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሰቅለ /በክቡር ደምህ ትቀድሳት ዘንድ ስለቤተክርስቲያን በአደባባይ በጥፊ ተመታክ፤ ስለ እርሷ ሲል ታስሮ ተጎተተ፣ እርኩስ ምራቅን ታገሰ ያለበደል አምላክ በመስቀል ላይ ተሰቀለ ሲል የክርስቶስ ዋጋ መክፈል ለቤተክርስቲያን መሆኑን ይናገራል።

ለመሆኑ ይህች ቤተክርስቲያን ማናት? ብዙዎቻችን ስለቤተክርስቲያን ስናስብ አእምሯችን ላይ የሚመጣው ህንፃው ወይም ተቋም ነው። በእርግጥ ህንፃ ቤተክርስቲያን ከቤተክርስቲያን ሦስቱ ትርጉሞች አንዱ ቢሆንምና ለአስተዳደር እንዲመች ሲባል ቤተክርስቲያን በተቋማዊ መልክ ብትገለጽም ቤተክርስቲያንን እንደ አንድ ድርጅት መረዳት ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችና ፈራሽ ተቋማት ጋር የምትነፃፀር አድርጎ መረዳትን ፈጥሮብናል።

ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል መነሻ አቅሌሲያ /ἐκκλησία/ ሲሆን ትርጉሙም ጉባዔ፣ አንድነት፣ ሕብረት ማለት ሲሆን የጉባዔው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ቤተክርስቲያን ጉባኤ እግዚአብሔር ተብላ ትጠራለች። (ማቴ 16:18)

ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነትን በሚገልፅ መሠረተ እምነት ላይ ነው። ለዚህም ነው ክርስቶስ ጴጥሮስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ሲመሰክር አንተ አለት (በግሪኩ Πέτρος – ጴጥሮስ) ትባላለህ ካለው በኋላ ምስክርነቱን በሴት አንቀጽ በዚህችም አለት (በግሪኩ πέτρα – ጴጥራ ) ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሰርታለሁ የሲኦል ደጆችም አያናውጧትም በማለት የተመሠረተችው በሥጋና ደም ሳይሆን ከእግዚአብሔር በተገኘ ቃል መሠረት መሆኑን ይነግረናል (ማቴ 16: 15-18)።

ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል ተመስርታለች ስንል ምን ማለታችን ነው የሚል ካለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይለናል “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” ኤፌሶን 2፥20 በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚናገሩ የነቢያትና የሐዋርያት የመጻሕፍትም ሆነ የትውፊት ትምህርቶች የቤተክርስቲያን መሰረት መሆናቸውን ይናገርና የማዕዘኑ ራስ እርሱ ጌታችን መሆኑን ይናገራል።

መምህረ ዓለም ጳውሎስ ከሌሎች ሐዋርያት አብልጦ ስለቤተክርስቲያን አምልቶ በመናገር የሚታወቅ ሐዋርያ ነው ይህ ሐዋርያ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ በምን ያህል መጠን እንደተወደደች ለባሎች በሚሰጠው ምክር ላይ ያነሳዋል።


“ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ኤፌ 5:25-27

ቤተክርስቲያን ድካምና እድፈት እንዳይኖርባት አድርጎ ምን ያህል እንደ ወደዳት እናስተውል። እርሷ ከዳግማዊው አዳም በዐለተ አርብ ከጎኑ ተገኝታለችና ዳግማዊት ሔዋን ናት። ሔዋን የሚለው ቃል የሕያዋን እናት እንደ መሆኑ የስሙ ትርጓሜም ልክ የሚመጣው በክርስቶስ አባትነት ሕያዋንን ለምታፈራው ለቤተክርስቲያን ነው። በዚህች ቤተክርስቲያን በኩል ካልሆነ ማንም ሕይወት እኔ ነኝ ካለን ከክርስቶስ ጋር አይገናኝምና ከሷ ውጭ ያሉ ሁሉ ሙታን ናቸው።

የቤተክርስቲያን ክብር ይህን ያህል ነው ምክንያቱ ደግሞ ራሷ ክርስቶስ ስለሆነ ነው። ከዚህም ባሻገር ቤተክርስቲያን ወሰን አልባ ናት። ከቀደመው ሰው መፈጠር አስቀድሞ በዓለመ መላእክት የነበረች ጉባዔ ናት። ይህችው ጉባዔም በምድር በብሉይ ኪዳን አበው ዘንድ ነበረች። በነዳዊት አንደበትም ይህቺ ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት ብሎ ያናገረው እርሱ እግዚአብሔር ነው መዝ 132:14። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ በነቢያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ብሎ የተናገረው።

እርሱ ክርስቶስ ይህቺኑ ቤተክርስቲያንን ያፀና ዘንድ በውስጧ ባሉ ሰውና መላእክት መሐል ያለውን የጥል ግድግዳ ያጠፋ ዘንድ ሰው ሆነ። በሐዲስ ኪዳን አዳምን ያከብረው ዘንድ መልዕልተ መስቀል እንቅልፍ በተባለ ሞት ውስጥ ሆኖ ከጎኑ በፈሰሰ ውሃና ደም የማትሞተዋን ሔዋንን ሰራልን። በዚህች ቤተክርስቲያን በኩል ብቻ ከክርስቶስ ጋር ህብረት መፍጠር እንድንችል ዘንድ የሚያዛምዱንን ምሥጢራት ሰራልን በጥምቀት ከአንድ ማህፀን በመወለዳችን ወንድምና እህት አደረገን። እራሱን የከበረ ማዕድ በማድረግ በቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ አፋቀረን። በሜሮን መንፈስ ቅዱስን አሳደረብን። ከክርስቶስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ ራስ በመሆን አካሉ እንሆን ዘንድ ፈቀደ።


አንድ የሰውነት አካል ብቻውን ሕያው እንደማይሆን አንድ ክርስቲያንም ያለ ቤተክርስቲያን ሕብረት በክርስቶስ ሕያው መሆን አይችልም በመሆኑም ከክርስቶስ ጋር ይጣበቅ ዘንድ ከቤተክርስቲያን ጋር አንድ መሆን ይኖርበታል።

ቤተክርስቲያን ራሷ በሆነው ክርስቶስ አማካኝነት ሕልውናዋም ዘላለማዊ ነው። በምድር የምትጋደል ቤተክርስቲያን እንዳለች ሁሉ በሰማይም አሸናፊት ቤተክርስቲያን አለችና የአማኞች ሞት ከተጋድሎዋ ቤተክርስቲያን ወደ አሸናፊቷ ቤተክርስቲያን መሸጋገሪያ ነው። በመሆኑም በአሸናፊዋ ቤተክርስቲያን የሚገኙ ምዕመናን ከተጋዳይዋ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ጋር ይነጋገራሉ፣ ይፀልያሉ በማይቋረጥ ሕብረት ይኖራሉ። ዕብ 12:1።

ይህንን ሁሉ ክብር ያለብሳት ዘንድ እናትም ትሆነን ዘንድ በመከራ መስቀል ቤተክርስቲያንን የዋጃት የአምላካችን ክርስቶስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

ክርስቶስ ተንስአ እም ሙታን – ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ።

Report Page