ዳንሰኛው ወንድሜ

ዳንሰኛው ወንድሜ

ለማንኛውም አስተያየት👉🏾ሶፊ#27(ጌራ ኢትኤል)


ሰባራ ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ ወንድሜን በመጠባበቅ ላይ ነኝ። ዳንስ ወደ ሚሰለጥንበት አዳራሽ ከገባ ጥቂት ደቂቃዎች አልፈዋል...ቢያንስ ከሁለት ሰዓት በላይ እንደሚቆይ አውቃለሁ...ዛሬ ያለወትሮዬ ወንድሜን ዳንስ የሚሰለጥንበት አዳራሽ በሩ ላይ ቁጭ ብዬ የምጠብቀው ሊጋብዘኝ ነው...ተውረግርጎ (ደንሶ) አሸንፏል።

እስከዛ ምን ልስራ ? ስልኬን እየጎረጎርኩ ለመጠበቅ ወሰንኩ...ውይ ስልኬ ለካ ቻርጅ ዘግቷል...ታዲያ ምን ልስራ? የስልኬ ነገር አይሆንልኝም...ለነገሩ አብዛኛው ሰው ከስልኩ ውጪ ሌላ ጊዜ የሚያሳልፍበት ነገር ያለው አይመስለውም ሱስ ሆኖብናል...ትንሽ ትልቁ ሁሉም ቀና ብሎ እየሆነ ያለውን አያስተውልም ስልኩ ውስጥ በፈጠረው ምናባዊ አለም ሲንቀዋለል ይውላል...ፓለቲካው፤ብልግናው፣የእገሌ ቅሌት፣ኳሱ፣ውሸቱ፣እውነቱ፣ፎቶው፣ጥላቻው፣ፍቅሩ...ሁሉም በአንድ ላይ ተደባልቀው በማያገባን ስንገባ እንውላለን...እንደውም ከአንድ ዶክተር ጋር ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስንጫወት ያለኝን አልረሳውም...
<<አለም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነች...ቅርብ ጊዜ የኒውሮ ሳይንቲስቶች (Neuro scientists) "Smart phone addiction" የሚባል በሽታ ለይተዋል...በሽታው ልክ እንደ " cocaine addition" ለመላቀቅ የሚከብድ ነው...የበሽታውን ስም "nomophobia" (no mobile phobia ) ብለውታል...አስተውለህ ከሆነ ስልክህን አታምነውም...አስበኧውም ሆነ ሳታስበው ስልክህ እጅህ ላይ ነው...>> ነበር ያለኝ።እኔም የዚህ በሽታ ተጠቂ ሳልሆን አልቀርም።
የምሰራው ስራ ስላጣው ወንድሜ አሸክሞኝ የሄደውን ደብተር ጊዜውን ለመግደል ማገላበጥ ጀመርኩ (ጊዜም ይሞታል? አዎ እሱም አንድ የእግዚአብሔር ፍጥረት ነው ለማይጠቅም ነገር ስናባክነው ይሞታል...ለዛ መሰለኝ አንዳንድ ሰዎችን በተለምዶ ስራ ይዘሃል ስትላቸው አይ ዝም ብዬ ጊዜ ለመግደል ነው ይሉሃል...ነብሰ ገዳዮች!)
...ከተመረኩ መንፈቅ አልፌኛል ስራ አላገኘውም...ማማረር ግን ገና አልጀመርኩም አንዳንዴ ወረቀት እራሱ ሳይ እበሳጫለሁ መማሬ ያበሳጨኛል...ያሁሉ ገንዘብ ጊዜ አልባሌ ቦታ ስላዋልኩት ያንገበግብኛል...በዛ ሰሞን ለእኔ አልባሌ ቦታ የሚመስለኝ ትምህርት ቤት ነው...ወደ ቀልቤ ስመለስ ግን ማወቄን መኮነን ማቆም እንዳለብኝ ተገነዘብኩ...<<ለሚያማርር ሰው አጋጣሚዎች አይታዩትም።>> የሚለውን የእናቴን አባባል በልቤ አኑሬ...ወይ አጋጣሚ ለማግኘት ወይም አጋጣሚውን ለመፍጠር ጊዜን እየተጠባበኩ ነው...
የወንድሜን ደብተር ሳገላብጥ የተረዳሁት ነገር ቢኖር አንድ ገፅ በገጥኩ ቁጥር የእኔም አለማወቅ እየተገለጠ እንደሆነ ነው...ትምህርት ግን በቃኝ ልደድብ ካላሉ አያልቅም አይደል? ሁሌ የማናውቀው ነገር አለ...ለዛ ይመስለኛል ምሁራን ነን ባዮች መፍትሔ ሳይሆን ችግሮችን የሚፈጥሩልን...የበለጠ ያወቁ ሲመስላቸው ወደ ትላንት ይራመዱና ክፋ ነገር ያገኙ ዘንድ ይቆፍራሉ...ከሌለ እራሳቸው ይፈጥራሉ...አዲስ ነገር መመራመር ስለተሳናቸው የተሰራውን ያፈርሳሉ...ያስተማራቸው ህብረተሰብ አያሳዝናቸውም ያስመርሩታል...ለዚህ ምስኪን ህብረተሰብ የሌለውን ነገር አይሰጡትም ያለውን ይነጥቁታል...አባቴ የሰው ልጅ ፍቅር ማጣቱን ሰበር ዜና መብዛቱን...የእኔን ቤት ተቀምጦ መተከዝ ጥቂት ቀን ካስተዋለ በኋላ...እንዲህ አለ <<ለሚቀጥለው ትውልድ ማሰቡ ይቅር ምናለ ያለውን ትውልድ ተስፋ ባያስቆርጡት...? >>

ወንድሜ ከገባበት አዳራሽ ውስጥ የዳዊት ፅጌ ዘፈን ይሰማል...<<ምን ልሁን?>>

አትረበሽብኝ አትከፋ ሆዴ
የፈጠራት ጌታ ዝም ይላታል እንዴ?
.
.
.
ኑሪልኝ እናት ኢትዮጵያ
.
.
.
የቃኪዳን ቤትሽ የዌራው ምሰሶ
የከፍታሽ ጣሪያው ያልታያቸው አንሰው
ይሰቃያሉ እንጂ መች ሊያወርዱሽ ደርሰው
ከላይ መሆንሽን ያልተረዱት ከሰው

በዚህ ሙዚቃ ምን አይነት ጭፈራ ይሆን የሚጨፍሩበት? ወንድሜ ወደ ዘመናዊ ሙዚቃ እንደሚያደላ አውቃለሁ...ይሄ እኮ ነው ችግራችን ቁጭ ብለን መስማት የሚገባንን ሙዚቃ እየጨፈርንበት...አሁን ላይ እንደሁም ስለኢትዮጵያነት የተዜሙ ሙዚቃዎች በሙሉ ፋርማሲ ውስጥ ነው መሸጥ ያለባቸው...ብዙ ሰው በዘርኝነት ታሟል...!
ከዚህ ስሜት ለመውጣት ስታገል ድንገት ሰባራው ወንበር ሊጥለኝ አጋደለ ሚዛኔን ለመጠበቅ ስታገል ደብተሩ ከእጄ ወደቀ...መውደቅ እንዲህ እንደሚያስፈራኝ አላውቅም ነበር...ደብተሩን ከመሬት ላይ ሳነሳው የታጠፉ ወረቀቶች ከውስጡ ወደቁ...አንስቼ ልመልሰው ስል በደማቁ የተፃፈው ፅሁፍ ቀልቤን ሳበው...አነበብኩት...እንዲህ ይላል <<አንቺን ለመቅረብ ስታገል ከራሴ እርቄያለሁ...የእኔ መገለጫ ብዬ የማስባቸውን ነገሮች ሁሉ ሽሬያለሁ...አሁን ማን እንደሆንኩ እኔ እራሴ አላውቅም።>>

ወረቀቱን ገልጬ እንስካነበው ጓጓሁ፤የፍቅር ደብዳቤ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ...ከወንድሜ ጋር ሁሉንም ነገር እናወራለን፤ለነገሩ እኔ ምን የተደበቀ ነገር አለኝ?...እሱ የደበቀኝ ነገር እንዳለ ስለተሰማኝ ከፋኝ...በርግጥ ስለዚህ ዓይነት ነገር አንስቼበት አላውቅም...ወንድሜ በእኔ አይን አሁንም ልጅ ነው፤የየዋህነት መንፈሱ ያልጎደፈ፤ልቡ በዚህ ዓለም ክፋት ያልቆሸሸ፤ለማዘንና ለመከፋት ገና የሆነ ሳቂታ ፍልቅልቅ...የሚያሳስብና የሚያስከፋ ስሜት እንዳንዣበበብኝ ወደ ደብዳቤው አቀረቀርኩ...ወንድሜ ይህን ደብዳቤ ለመፃፍ ከስሜቱ ጋር እንደታገለ ያስታውቃል...ብዙ ስርዝ ድልዝ አለው...የመጀመሪያው ወረቀት እንዲህ ይላል...

<<ትምህርት ብዙም ያልተጀመረበት ጊዜ ነበር...አስተማሪዎቹ ስላልመጡ እንደተለመደው ተጋድሜ ፊልም ሳይ ቆይቼ የእራት ሰዓት በመድረሱ ከጓደኛዬ ጋር ወደ መመገቢያ አዳራሽ በተለመደው መንገድ ሄድን...መንገድ ላይ ግን ያልተለመደ ውበት ተመለከትኩ...ብዙ ጊዜ ቆንጆ ሴቶችን ተመልክቼ፤አፍ አውጥቼ ባልናገረውም በልቤ አድንቄያለሁ...ያንቺ ውበት ግን ያፈዝ ነበር...እነኚያ የሚያስፈሩ አይኖችን ጣል ስታደርጊብኝ፤የልቤን ባዶነት የመረመሩ መስሎኝ ተሳቀኩ...ውበትሽ ልክ ፀሐይ ምድርን ልትሰናበት ስትቀርብ እንደምታሳየው ያለ ነው...ከፍ ብሎ ተቀምጦ መላ ተፈጥሮን እንደማድነቅ ያለ...ከሚወዱት ሰው ጎን ቆሞ የፏፏቴን ውብ ዝማሬ እንደመስማት ያለ የሚደንቅ ውበት...ፍቅር መስፈርት ባይኖረውም መስፈርት ብዬ ልደረድራቸው የምችለውን ሁሉ እንደምታሟይ እርግጠኛ ነኝ።
ያቺ የተያየንባት ሴኮንድ ምናልባትም ደቂቃ...አህምሮዬ እና ልቤ እየተቀባበሉ ደጋግመው ሲያሳዮኝ ትውውቃችን ዘለግ ያለ ጊዜን ያስቆጠረ ይመስል ነበር...ጥቂት ጊዜ ግን ጥልቅ ስሜት...አልተናገረውም እንጂ ሁኔታዬ ጓደኛዬን ሳያስገርመው አልቀረም...እንደተለመደው አላወራንም...ደስታው ብዙም ሊያስበላኝ አልቻለም...ተስፋው የተቀጠለለት ሰው ይመስል ፊቴ ፍክት ፍክክት አለ...ወደ ዶርም እንደተመለስን አልጋው ላይ በጀርባዬ ለጥ አልኩና ከሃሳብ ማጠራቀሚያ የአህምሮዬ ክፍል ውስጥ ምስልሽን ምዥርጥ አድርጌ፤ሁኔታሽን አጤን ጀመር...አጭሯን ቅፅበት ደግሜ ደጋግሜ አየሁ
ድንገት ፈንጠር ብዬ ተነሳሁና በለስ ሲቀናኝ የምደንሳትን ዳንስ ደነስኩ ያኔ ዶርም ውስጥ ያሉት ሁሉ ደስ እንዳለኝ ገባቸው...>> በፍጥነት ሁለተኛውን ወረቀት ማንበብ ጀመርኩ...

<<ይህ ስሜት ለእኔ አዲስ ነው ለመረዳት የሚርቅ...ነገ ፈተና አለን ግን ሐሳቤን ሰብስቤ 1 ገፅ እንኳን ማንበብ አልቻልኩም ... ይሄን 2 ወር ልክ አይደለውም ... ካላየሁሽ ቀን ጀምሮ ... አሁን እንደቀድሞ አዕምሮዬን ማዘዝ አልችልም እሱም ከልቤ ጋር አብሯል ... ያንቺን ዳና ይከተላል ... ከራሴ በላይ ብዙ ስላንቺ አውቃለሁ ለምሳሌ ... ምን አይነት ልብስ እንደምታዘወትሪ አይቼ ቀሚስ መልበስ እንደሚያስደስትሽ ተረድቻለሁ ... ብዙ ቦታዎች ብቻሽን ስለምትንቀሻቀሽ ብችኝነትሽን የምትወጂ ሰው እንደሆንሽ ገብቶኛል ... Non cafe እንደሆንሽ የትኛው ካፌ እንደሚመችሽ ... ቁርስ ላይ ፣ምሳ ላይ ምን እንደምትመገቢ የእራቱንም ጭምር አሁቃለሁ... ወደ 11 ሰዓት አካባቢ ፀሐይዋ ወደ መግቢያዋ ስታቀና፤አንቺ ከግቢው በር ፊት ለፊት ያሉት ዛፎች መካከል በአንዱ ስር ቁጭ ብለሽ እሷን መመልከት ደስ እንደሚልሽ አውቃለሁ፤ከዚህም የተፈጥሮ አድናቂ እንደሆንሽ መገመች ችያለሁ ... ቤተ - ክርስትያን ሰው በማይኖርበት ሰዓት መሄድ እንደሚያስደስትሽ፤ሁለት ሰንበት እኛ ስንመለስ አንቺ ስትሄጂ አጋጥሞኛልና ... እና ፊት ለፊት በተለያየንባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አንቺም አይኖችን እንደምትጥይብኝ ከኔም አልፎ ጓደኛዬ ነግሮኛል ... ጓደኛዬ አይዞህ ያለው ልቤ እኔን አልሰማ ብሎኛል ... ቆይ እኔን ያለሰማ ማንን ሊሰማ ነው ? ( እስካሁን ተለጉሞ አንቺን ብቻ እያሰበ የነበረው አዕምሮዬ መልስ ሰጠ <<እሷን ነዋ !>>) ልቤን አንድ ነገር በይው ትምህርቴን ልማርበት።>>

በጉጉት ሶስተኛውን ወረቀት ገለጥኩ...<<ዛሬ ልብ የሚሰነጥቅ ድንጋጤ፤ደነገጥኩ። ብዙ ነገሮች ግልብጥብጥ አሉብኝ ... ምን ሆነ መሰለሽ ... በአንቺ ሀሳብ ተሸብቤ ሳልማር ከመማሪያ ክፍላችን ወጥተን እናንተ በምትማሩበት ክፍል አቅራቢያ ከሁለት ጓደኞቼ ጋር ስናልፍ ... አንቺ እንደተለመደው ብቻሽን ወደ ክፍል ስታመሪ ፊት ለፊት ተላልፈን ... አንቺ አታውቂም ... ስላንቺ ያለኝን ስሜት የማያውቀው አንዱ ጓደኛዬ ውበትሽን እጅግ አድንቆ ፊቱ ፍክት እንዳለ <<እቺ ልጅ አታምርም አለኝ ?>> ድንገት ብስጭት ብዬ <<አታምርም ! >>አልኩት ። የንዴቴ ምክንያት ባይገባውም <<ለእኔ ግን በጣም ቆንጆ ናት >>አለ ። ሁሉንም የሚያውቀው ጓደኛዬ ወሬውን ለማስቀየር ጥረት አደረገ ... ምሳ መመገቢያ አዳራሽ ውስጥ ተለጉሜ ምንም ሳላወራ ከአንቺ ሀሳብ መለስ ስል የውሸት ፈገግታ ፈገግ እላለሁ ፤ አልችልበትም ያስታውቅብኛል ... ከመመገቢያ አዳራሽ ስንመለስ እነርሱ ሻይ ሊጠጡ ሄዱ ... እኔ ፈጠን ብዬ ወደ ዶርም ተመለስኩ እና መከረኛ አልጋዬ ላይ ከነጫማዬ ጋደም እንዳልኩ የሐሳብ መንኮራኩሩን ተሳፈርኩ ... እንዴት ይሄ ሁሉ ጊዜ የእኔ እንደሆነች አይገባቸውም ? ይሄ ገመድ አፍ ማንንም በሚያደንቅበት አፉ አታምርም ይበለኝ ! እና ምን ይሁን ትመራ ትመር ! ላተምሪ ነው ? እውነት ለመናገር እሱን የማታምረው ሴትስ አለች ?! ሁል ጊዜ ይበርደው ይመስል የደረባቸውን ሴቶች ጀብድ መስሎት ለእኛ አይደል እየመጣ የሚለፈልፍብን ? አታምርም ወይ ይለኛል፤ደግሞ አንቺ አማርሽው ? እኔ ግን ካወኩሽ ቀን ጀምሮ አንቺን ነው የምለው አንቺን ብቻ !በርግጥ ከዚህ በፊት አፍቅሬ አላውቅም፤ያፈካሽውን ብርሀኔን እንዳያደበዝዝብኝ ... እርሷን እንኳን ተውልን ? ብዬ ልለምነው? ጭንቅላቴ አንድ መፍትሔ ሹክ አለኝ <<ለምን አትነግራትም ?>> አዎ ልነግርሽ ይገባል።>>

ሶስተኛው ወረቀት አለቀ...አራትኛው ወረቀት ሙሉ አይደለም...እንዲህ ይላል

<<ቃላትን አሰካክቼ ሰው ማግባባትና ማሳመን አላውቅም...እንደ'ኔ 'ላለው ሰው ይሄ በጣም ከባድ ነው። መጥቼ ፍቅሬን ልገልፅልሽ ብወድ ... ሌሎች ወንዶች እንደሚያደርጉት ተራ ለከፋ እንጂ፤ የፍቅሬን መጠን ይገልፅልኛል ብዬ አላምንም ... የጤናን ዋጋ የሚይልውቀው የታመመ ሰው ነው ... የፅድቅን ዋጋ የሚያውቀው በበደል ልቡ የቆሸሸበት ሰው ነው ... የሰላም ዋጋ የሚገባው(ላልቶ ይነበብ) የተረበሸ ነው ... የፍቅሬንም መጠን እንደ'ኔው አፍቅረሽ እንጂ በምነግርሽ ቃላት ይገባሻል ብዬ አላስብም ...>>

ከዚህ በኋላ ያለው ወረቀት ታጥፎ ተቆርጧል በጣም ብሽቅ አልኩ ... ሰርቄ እያነበብኩ ቀጥልልኝ አልለው ነገር ...

ከወረቀቶቹ መሀል ሌላ ቁራጭ ወረቀት ... አምስተኛ መሆኑ ነው እርሱ ደግሞ እንዲህ ይላል...

<<ሰው በአጋጣሚ ይገናኛል ... ከዛ ይቀራረባል ... የእኛ ግን እንደዛ አልነበረም ... በርግጥ ለአንቺ እንደዛ እንዲመስልሽ አድርጌያለሁ ... ምክንያቱም ጓደኞቼ እንደ ፈለኳት ካወቀች ትኮራብሀለች ስላሉ ...>>

ተቀራርበዋል ማለት ነው? ቀጣዩን ለማንበብ ተጣደፍኩ...

<<እነዚያ የመጀመሪያ ጊዚያት ... ውብ ነበሩ ፤ በሩቁ ውበትሽን የማደንቅበት ... ያልተናገርሻቸውን በማናቤ የምሰማበት...የሆንሽውን ሳይሆን እኔ ካላበስኩሽ ማንነት ጋር ልብ ለልብ የምናወራባቸው ጊዜያት ደስ ይሉ ነበር ... እነኚያን ፊትለፊት ለማየት የማልደፍራቸውን አይኖችሽን ሳያቸው ቆይቼ ድንገት ገፅሽን ወደ እኔ ስትመልሺ የምደናበርባቸው ጊዜያት ይናፍቃሉ... እኔ በምናቤ እንደሳልኩሽ መልዓክ አልነበርሽም አንቺም ሰው ነሽ፤ባዶነትሽን በብዙ ሰዎች ከበባ ለመሙላት የምትዳክሪ ምስኪን ሰው ... በምናቤ የሰፋሁልሽ ማንነት ሰፋሽ።

እንደ ተራራ የገዘፈው ፍቅሬ በአንዴ አልተናደም ... በአንቺ ላይ ዕምነት ማጣቴ ሸረሸረው ... ሰዎች የነገሩኝን ሰምቼ አላውቅም ... በፍቅር አይን የምታደርጊያቸው ሁሉ ልክ ነበሩ ... ማስተዋል ስጀምር ግን እየገባኝ የመጣው እውነታ ጥያቄን እየፈጠረ ከህሊናዬ ጋር ያላተመኝ ጀመር... መቀራረባችን ለመራራቃችን ምክንያት ሆነ ... ሰዎችን ቀርቦ ከመናቅ በሩቁ ማክበርን የመሰለ ነገር የለም ። ምናልባት ጥፋቱ ያንቺ አይደለም ... ግዴታ የሳልኩትን ማንነት መላበስ የለበሽም ... ግን ከጎንሽ ሆኜ ትርፍ ነበርኩ...
<<በዝ ዓለም ዘኢያስተፌሥሑ ክልኤቱ ነገራት ሀለዉ ወእሙንቱሂ ሀጢዖት ዘኀሠሥዎ ወረኪቦት ዘኀሠሥዎ።

በዚህ ዓለም ሁለት የሚያስከፉ ነገሮች አሉ እነርሱም የወደዱትን ማጣትና የወደዱትን ማግኘት። >>
የእኔ ጥፋት ይህ ነው...አንቺን ሳገኝ ሙሉ የምሆን ይመስለኝ ነበር...እኔ ያጎደልኩትን አንቺ ችለሽ አትሞይውም። መቼም እርሱ ሁሉን ሙሉ አድርጉ ፈጥሯል...እኔ ያጎደልኩትን መጀመሪያ መሙላት ነበረብኝ።>>

አለቀ...እውነትም ከምናውቀው ሰው ውስጥ ሌላ ፍፁም የማናውቀው ሰው አለ። ወንድሜን የማውቀው ይመስለኝ ነበር...ለካ ሌላ ሰው ነው። ሰው ግን የሚያስገርም ፍጥረት ነው።ወረቀቶቹን እንደነበረው ባይሆንም በተመሳሳይ መልኩ አጥፌ ደብተሩ ውስጥ መለስኩት...
አይኖቼን ጨፍኜ ግርግዳውን በጭንቅላቴ ተደገፍኩት...ወንድሜን ልመክረው አስቤ ነበር ግን ህይወት የመከረችው ይበልጣል፤ስለዚህ ነገር ምንም ላላነሳ ወሰንኩ።

ወዲያው ወንድሜ ከአራት ጓደኞቹ ጋር ሲመጣ ተመለከትኩ...እያየሁት እንደሆነ ሲያውቅ መደነስ ጀመረ...ኤይ ኤይ ኤይ እያሉ አጀቡት...በፈገግታ ተቀበልኳቸው፤አንድ በአንድ አስተዋወቆኝ ተሰናብተናቸው ሄድን...

መንገድ ላይ <<አንተ ጨበሬ ይሄን ፀጉርህን ወደዛ አስወግደው? >> አልኩት።(እንደሚያምርበት ባውቅም ሰው ምን ይላልን ፈርቼ...)
<<ከማን ተማርኩትና>> አለኝ።ወደ ተንጨባረረው ፀጉሬ እያየ...
<<እና ለእኔ የሰጡትን ስም ላንተ ይስጡህ?>>
<<ተው 'ባክህ ሶፊ አንተ በዚህ አይነት መንገድ እንደማታምን አውቃለሁ...<<ከላይ ከምትደርበው ድሪቶ በላይ ያማርክ ሁን...ንፁህ ልብስህ የቆሸሸ ማንነትህን መሸፈኛ አይሁን>> ትል የለ።ግድ ስለማይሰጥህ አይደል መርጠህ የማትለብሰው? አለኝ አይኑን ጠበብ አድርጎ።(ቁም ነገር ሲያወራ አይኑን ያጠባል)
<<ግድ ስለማይሰጠኝ ሳይሆን ስለሌለኝ ነው...ቆንጆ ልብስ መልበስ ማን ይጠላል>> አልኩት ፈገግ ብዬ።
<<አይ ይቺ አለም ...ልብስ አጥታችሁ የማትለብሱትንም እብድ ነው የምትለው...>> አለ የስላቅ ሳቅ እየሳቀብኝ።
<<ምነው "alien" ነኝ አልክ?>> አልኩት ገፍተር እያረኩት...
እህቴ ትዝ አለቺኝ እና <<ቆይ ቆይ አንተ ለምንድነው እህቴን ያልጠራሃት?>> አልኩት።
<<'ባክህ ይሄኔ እህትህ(የኔ ብቻ እህት አደረጋት...) ከጓደኞቿ ጋር ናት፤አንተ ማንን ታገኛለህ ? በዛላይ ስራ ፈት ነህ ብዬ ነው...ደግሞ እንዳትኮራበት...ምን የዛሬ ልጆች እኮ በምን እንደምትኮሩ አታውቁም...>> አለ እየተመለከተኝ።
<<ኧረ ማሾፍህ ነው ?>>ብዬ ዝም ልለው ስል...ከት ብሎ እየሳቀ << ደግሞ ምንድነው እንደ ሳራ ቲ አስሬ ፀጉርህን የምትነካካው?>>
<<ልታደንቀኝ ይገባል ቢያንስ እኔ የራሴን ፀጉር ነው...>> ይሄን እየተባባልን ሊጋብዘኝ ካሰበው ቦታ ስንደርስ...ቀድሞኝ ገባ(ጋባዥ ቀልብ የለውም)...ተከተልኩት።

ተፈፀመ

እስከዚህ ድረስ ስላነበብከው/ሽው አመሰግናለሁ።

ምስጋና ይህን ስራ ለወዳጆቹ ላካፈለ እና በፅህፈት ላገዘኝ ጓደኛዬ ሶላ።

ቻናሌን ለመቀላቀል የሚፈልግ @bestletters

©ሶፊ


Report Page