ክፍል 3 የመሳብ ሕግ እምነቶች

ክፍል 3 የመሳብ ሕግ እምነቶች

ናዝራዊ Tube telegram channel


የመሳብ ሕግ መምህራን ( አነቃቂ ተናጋሪዎች) ስለ ገንዘብ፣ ስለ ጤና እና ስለ እግዚአብሔር ያላቸው እምነትና ትምህርት 

( Law of attraction teachers (motivational speakers) beliefs and teachings about money, health and God)


ተጻፈ፦ በነብዩ ኢሳይያስ 

ክፍል ሦስት ፦


የመሳብ ሕግ  ( Law of attraction) ምንድነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ ባጭሩ “ አዎንታዊ እና አሉታዊ አስተሳሰብ እና እምነት ወደ ሰው ሕይወት ውስጥ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ  ልምዶችን ያመጣል የሚል ጽንሰ ሓሳብ ነው። 

 

በትምህርቱ አራማጆች (በአነቃቂ ተናጋሪዎች)  ዘንድ፣ ስለ ጤንነት፣ ገንዘብ ፣ ብልጽግናና ሀብት ያላቸው አስተሳሰብ ከናፓሊሆን ሂል ተቀድቶ ወይም ተጠልፎ የመጣ ነው። ናፓሊዮን ሂል ብዙ ጊዜ የሚታወቀው “አስብና በልጽግ” ( Think and Grow Rich) በሚለው መጽሓፉ ሲሆን፣ በእምነቱ ረገድ መንፈሳዊና ሜታፊዚካል አንድ ላይ የያዘ ሰው ነው ። እዚህ ላይ ግን እርሱ መንፈሳዊ የሚለው ሃሳን ፣ መጽሓፍ ቅዱስ የሚናገርለት መንፈሳዊነት  እንዳልሆነ ልብ ይሏል። 


የመሳብ ሕግ ( Law of attraction) ትምህርቶቹ፦


የመሳብ ሕግ፣ የሰው ጤንነት እና ሕመም፦


በመሳብ ሕግ  ትምህርት ውስጥ የሰው አካላዊ ጤንነነት የሚወሰነው ( determined ) የሚሆነው፣ በሰው አስተሳሰብና ስሜት  ( thoughts and feelings) ነው የሚል ነው።  እንግዲህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰውየው ታሞ አልታመምሁም ብለህ አውጅ ፣ ምንም ሳይኖረው ሀብታም ነኝ ብለህ ተናገር፣ ምንም ቤት ወይም መኪና ሳይኖረው  በስሙ ጠርቶ  ያ ቤት ፣ ያ መኪና የእኔ ነው ብለህ አውጅ፣  እንዲሁም ነቢዩ ቃል አወጣሁ ሲል “በእምነት ወሰድኩ በል  የሚለው ትውልድን ያሳተ አስተሳሰብ የተቀዳው ከዚህ የምስጢሩ ትምህርት ( Law of attraction) ስንጽ ሓሳብ ውስጥ ነው። 


በእርግጥ ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ቢኖሩም ሰው ግን  የሚታመመውም ሆነ የሚድነው በአስተሳሰቡና በስሜቱ ነው ብሎ መደምደም ለእኛ ክርስቲያኖች  ትልቅ ነገረ - መለኮታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ሕመም በባህሪው  በውድቀት ምክንያት የመጣ እንጂ በሥነ - ልቦና ችግር የመጣ ብቻ ስላይደለ። እንግዲህ በወንጌላውያኑ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዳንድ ስመ - ጥር ፓስተሮች፣ ነቢዮች ፣ ተዋቂ ግለሰቦች እና ምዕመናን ከክርስቶስ ወንጌል ፈጥነው ዘወር  ያሉት ወደ እዚህ  ልዩ ትምህርት እና ልምምድ ነው።


በእርግጥ ጭንቀት እና  ድባቴ ለሰውነት ጎጂ መሆኑ በህክምናም የተረጋገጠ  ነው። ደስታ እና ሰላም ደግሞ ውስጣዊ ፈውስን እንደሚያመጣ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እናነባለን።  መጽሓፈ ምሳሌ ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን “ደስተኛ ልብ መልካም መድኃኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን አጥንትን ያደርቃል” (ምሳሌ 17፡22) ። “  ብሩህ ገጽታ ልብን ደስ ያሰኛል፤ መልካም ዜናም አጥንትን ያለመልማል”( ምሳሌ 15:30 ) ። ዳዊት ያልተናዘዘው የክፋት ድርጊቶቹ ከበደለኛነት ጋር እንዲታገል እንዳደረገው ሲናገር” ሁል ጊዜ ከመጮኼ የተነሳ ፣ “ዝም ባለሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ”  በማለት ተናግሯል (መዝ 32፡3) ።  ሀሳቦቻችን እና ስሜቶቻችን በአካላዊ ደህንነታችን ላይ ተፅእኖ አላቸው፤ ነገር ግን፣ ይህ የሆነው እግዚአብሔር ሰውነታችንን በፈጠረበት መንገድ ነው እንጂ "ከሁለንተናዊ የኃይል ጉልበት" (universal energy force)  ጋር ባለን  አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ግንኙነትና አካላዊ ምልክቶችን ስለምናስብ ወይም ስለማናሳብ አይደለም። የሰው በኅጢአት መውደቅ ብዙ ያስከተላቸው ውጤቶች አሉ።


የመሳብ ሕግ ፦  ገንዘብ ፣ ሀብትና ብልጽግና ፦


ሌላው በ "የመሳብ ሕግ " ውስጥ  ያለው ሁለተኛው ስህተት በገንዘብ፣ በሀብትና በብልጽግና  ጉዳይ ከሚገባው በላይ አፅንዖት መስጠት ነው.። መጽሐፍ ቅዱስ ሀብት፣ ገንዘብንና ብልጽግናን አስመልክቶ ብዙ  የሚናገረው አለው። ምሳሌ 13:11 ላይ “ ያለ አግባብ የተገኜ ገንዘብ እየተመናመነ ያልቃል ፣ ገንዘቡን ጥቂት በጥቂት የሚያከማች ግን ይጠራቀምለታ”ይላል። በተመሳሳይም ምሳሌ 17: 16 “ ጥበብን ለማግኜት ፍላጎት ስለሌለው፣ በተላላ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድነው?  በማለት ይናገራል። የሰው ልጅ  የፋይናንስ ስኬት የሚወሰነው በውሳኔዎቹ፣  ጠንክሮ በመስራቱ፣ በጥረቱና ባለው  ጥበባዊ ባላደራነት ነው። ሀሳባችን የቱንም ያህል አዎንታዊ ቢሆንና አእምሯችንም በሀብት ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣  በተለይም በምዕራቡ ዓለም በብድር የኢኮኖሚ ሥርየት የገዛናቸው የቁሳቁሶች ሒሳብ  የእዳ ተራራ ( mountains of debt) ሆነው ምጣታቸው አይቀርም።  የእግዚአብሔር ቃል በምሳሌ 22፡7 ላይ “ ባለ ጠጋ ድኻን ይገዛል፤ ተበዳሪም የአበዳሪው ባሪያ ነው “ ይላል። የ“አዎንታዊ አስተሳሰብ” ምስጢር ሰዎች በገንዘብ ነክ ሁኔታቸው ላይ የሚያሳድረው ብቸኛው ተጽእኖ፣ ጠንክረው እንዳይሠሩና ገንዘባቸውን  በጥበብ እንዳያወጡ ማድረግ ነው ። አስተሳሰቡና ትግበራው በአገራችን ሰዎች የሰላቢ መንፈስ ከሚሉት ጋር ይመሳሰል ይሆን?


የመሳብ ሕግ ሀብትን በማግኘት ላይ ያለው ትኩረት  በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ይቃረናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ጥበበኛ እና ባለጸጋ የሆነው ሰሎሞን “ገንዘብን የሚወድ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናንም የሚወድ በትርፉ አይረካም። ይህ ደግሞ ከንቱ ነው”  ብሏል (መክብብ 5፡10)።  የፍጥረቱ ፈጣሪና ባለቤት የሆነውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ” ብሏል (ሉቃስ 12፡15)። ጳውሎስም  1ኛ ጢሞ 6፡10   “ የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው። አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጕጕት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ሲል መክሯል።  የገንዘብ አደገኛነቱ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል ማስቀመጡና ሐሰተኛ አምላክ መሆኑ ነው።


የመሳብ ሕግ እና  የእግዚአብሔር ሉዓላዊ አምላክነት፦


ሦስተኛው  የ“ምስጢሩ” ወይም የመሳብ ሕግ ዋና ስህተት ስለእግዚአብሔር ያለው አመለካከት ወይም የእግዚአብሔርን ሕልውና መካዱ  ነው።  ዋና በሚባሉት የጽንሰ ሓሳቡ አራማጆች ዘንድ፣  ጽንሰ ሓሳቡን ተቀብሎ ለመለማመድ በእግዚአብሔር ማመን መስፈርት አይደለም ። ማንም ሰው ጽንሰ ሓሳቡን እስከተቀበለ ወደ ልምምዱ ዘው ብሎ ሊገባ ይችላል። እንዲያውም ሮንዳ ብይነርን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የዩንቨርስን ኅይልና ጉልበት ይቀበላሉ እንጂ የእግዚአብሔርን ሕልውና የሚያምኑ አይመስሉም። እንዲያውም ይህንን ትምህርት ተቀብለው የሚለማመዱ ሰዎች እኔ ባለሁበት በምዕራቡ ዓለም “ሕይወት ወይም ሥራ እንዴት ነው ?  ብላችሁ ብትጠይቋቸው ፈጣሪን  ይመስገን” ከሚለው ምላሽ ይልቅ ቶሎ ፈገግ ብለው የሚቀድማቸው “ግሩም ነውና ድንቅ” ነው (amazing and fantastic) የሚለው ነው። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ጆን ዊልደን ሲናገር” ምስጢሩን  ተቀብለው ከመጽሓፍ ቅዱስ ጋር ሓሳቡን በመደባለቅ የሚያስተምሩ ሰዎች፣ እግዚአብሔር ይመስገን በሚለው ጥላ ውስጥ ተደብቀው ባዕድ ኅይልን ወደ መቀበልና ወደ ማምለክ የመጡ  ይመስላሉ” ይላል።

እንዲያውም በምስጢሩ ተቀባይ ማህበረሰብ ዘንድ የሚታመነው እግዚአብሔር የለም  “ እግዚአብሔር፣እሱ እንኳን ካለ፣ ከሓሳባችን እና ከስሜታችን ጋር በማቀናጀት የምንጠቀምበት ሁለንተናዊ የኅይል ጉልበት ከመሆን ያለፈ  አይደለም” ( God, if He even exists, is nothing more than a universal force of energy that we manipulate through our thoughts and feelings.”) ትብሎ ነው ።  የፕሮቴስታንቱ አነቃቂ ተናጋሪ (ሰባኪዎች) አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት የሚከተሉት የእነዚህ ሰዎች አመለካከት ነው ።  ዳሩ ግን የሚከተሏቸውን ሰዎች እየመሯቸው ያሉት በስወር ተፈጥሮን ወደ ማምለክ  ልምምድ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።


በምስጢሩ ተከታዮች ዘንድ   ስለ አምላክ ያለው አመለካከት “እግዚአብሔር ሁሉም ነገር ነው” ወይም  “እግዚአብሔር እና  አጽናፈ ዓለም አንድ ናቸው” የሚል  የፓንቴይዝም ( Pantheism)  አመለካከት እንዳለ ይታመናል ። የሚያምኑት ሓሳባቸውን፣ ስሜታቸውንና የራሳቸውን እምነት ነው ። እግዚአብሔር ግን በባህሪው  ሉዓላዊ፣ ሁሉን ቻይ ፣ ሁሉን አዋቂ፣ በሁሉም ቦታ የሚገኝና ሁሉን  ነገር የሚቆጣጠር  ቅዱስ፣ ጻድቅና መሐሪ አምላክ ነው ። ምስጡሩ ይህንን እውነታ ይክዳል፣ አይቀበልም።  ዋና መልእክቱም  ሰው የራሱን  እጣ ፈንታ ራሱ እንደሚቆጣጠር አድርጎ ማቅረብ ነው ። ወደ መጽሓፍ ቅዱስ ስንመጣ ግን እውነታው ከዚህ የተለየ ነው። መዝ 139፣ 16 ላይ “ ያልተሰራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ ፣ የተፈጠሩ ቀኞቼ ሁሉ አንድስ እንኳ ፣ ሳይኖሩ በመጽሓፍህ ተጻፉ” ይላል። የሰው እድል ፈንታ የሚወሰነው በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ነው ። የጥንቷ ባቢሎን ታላቁ ንጉሥ ናቡከደነፆር  ይህንን “ምስጢር ”  ለሚያውቅ እድል ተሰጥቶታል (ዳንኤል 4፡34-35)።


የመሳብ ህግ ደጋፊዎች የሚሉት እግዚአብሔር ካለ ሰው ሁሉ “የእግዚአብሔር ትስጉት” (incarnations of God) ነው። ይህንን ሓሳብ የኒዎ ካርዝማቲክስ አቀንቃኞች ( የቃል እምነት እና የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች )ይጋሩታል። “ እኛ ሁላችን የራሳችን አማልክቶች ስለሆንን፣ የራሳችንን እውነታ መፍጠር የምንችል ነን። ስለዚህም  የራሳችንን እጣ ፈንታ መቆጣጠር እንችላለን ይላሉ። ይህ ውሸት  አዲስ አይደለም ። በመጀመሪያ  የሰይጣን ቀድሎም የሰው ፈተናው ነበር   (ኢሳ 14፡13-14  ፤ዘፍ 3፡5) ። ሰይጣን አምላክ ( በእግዚአብሔር ቦታ) ለመሆን ያደረገው ጥረት እንደከሸፈበት፣ ሰውም እንዲሁ አምላክ ለመሆን ያለው ፍላጎት ይከሽፍበታል (ኢሳ 14:15፤ ራእይ 20:10)  የሰው ልጅ የመለኮትነት ባህርይ የሌለው ፍጡር ነው ፤ የራሳቸው አምላክ ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ ይወድቃሉ(መዝ ዳዊት 82፡6-7)።

እውነተኛው “ምስጢር”  ክርስቶስ ነው ። ደግሞም ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ የሆነ ምስጢር የለም ። እግዚአብሔር ለማንኛውም የሰው ልጅ ሉዓላዊ እና ፍጹም እቅድ አለው። ቁልፉ ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት፣ ፈቃዱንና ሓሳቡን ማወቅ ብቻ ነው። ሀብትን፣ ዝናን፣ ስልጣንን፣ እና ተድላን ከመፈለግ በላይ  እግዚአብሔርን  መፈለግና በእርሱም ደስ መሰኜት የከበረ ነው  መዝ. 37፡4-6)።


ማጠቃለያ ፦

የመሳብ ሕግ ( Law of attraction) ከሰው አዎንታዊ እና  አሉታዊ ሀሳቦች በመነሳት አዎንታዊም ይሁኑ አሉታዊ አስተሳሰቦች በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ በሁለቱም አቅጣጫ ልምዶችን እንደሚያመጣ ይመን እንጂ፣  እንደ ብዙዎች  አስተያየት  ጽንሰ ሓሳቡ ከአብረታችነት ያለፈ ፋይዳ እና እውነታነት የለውም ። ይልቁንም ከመሳብ ሕግ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው አንዳንድ ትችትና በሰው ሥነ ልቦና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጣጣ በቀላል አልታየም። የመሳብ ሕግ አማኞች ጽንሰ ሓሳቡን እንደ አስተሳሰብ ወይም ማበረታቻ መሳሪያ አጋዥ ሆኖ ቢያገኙትም፣ ከልምምዱ  ጋር የተያያዙ አንዳንድ ትችቶች እና ስጋቶችም አሉ። ዋና ዋናዎቹም የሚከተሉት ናቸው፤-


1.የመሳብ ሕግ ለጥብቅ ሳይንሳዊ  ማስረጃ ድጋፍ የለውም ( Lack of scientific evidence) ። ብዙ ጊዜ  የሚቀርበው እንደ ሁለንተናዊ መርህ ነው ፤ ጽንሰ ሓሳቡ ስለ ስበት ያነሳና ፣ በዚያ ውስጥ የሚነሱት የይገባኛል ጥያቄዎች ግን በሜታፊዚካል ወይም በግል ታሪኮች እና ተሞክሮዎች ላይ የተመሰረቱ ሆነው ይገኛሉ ፣በዚህ ምክንያት ሳይንቲስቶቹ አስተማማኝ ሳይንሳዊ ማስረጃ እንደሌለው ይናገራሉ።  


2.የተወሳሰቡ ሁኔታዎችን ከመጠን በላይ የሚያቃልል መሆኑ (Oversimplification:)- የመሳብ ህግ ግለሰቦች የውጫዊ ሁኔታዎችን እና የስርዓት ጉዳዮችን ተፅእኖ በመመልከት በሃሳባቸው እና በስሜታቸው ብቻ ክስተቶችን እና ሁኔታዎችን እንደሚስቡ ያደርጋል። ይህ በሰዎች የሕይወት ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። 


3.ተጎጅውን ወይም ሰለባዎችን መውቀስ ( Blaming the victim:)፡- ማንም ሰው በዚህ ኣለም ላይ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል ፡፡ ይሁን እንጂ ጽንሰ ሓሳቡ የሚያሳየው  ሰዎች በአስተሳሰባቸው አሉታዊ ልምዶችን ወደ ራሳቸው እንደ ሳቡ ነው ። በዚህ ጊዜ ተጎጅዎቹ በሌሎች  ይወቀሳሉ። ክርስቲያን ከሆነ ደግሞ እንዳላመነ ይነገረዋል። ይህ አመለካከት ግለሰቦች ለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ውጫዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት ባለመቻል የመጣ ችግር ነው። ወይም ደግሞ አሉታዊ ልምምድን የራሴ አሉታዊ አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች ናቸው ብሎ የሚደመድም ሰው ሁኔታውን መለወጥ ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶት በራሱ ላይ እንዲፈርድ ሊያደርገው ይችላል። በዚህ ምክንያት የብቃት ማነስ ስሜት እየፈጠረ ሰዎች በመጨረሻ ህይወታቸውን ለማሻሻል እርምጃ እንዳይወስዱ ተስፋ ያስቆርጣቸዋል።


4.ከእውነታው የራቁ ተስፋዎች ( Unrealistic expectations:)፡- የመሳብ ህግ በአዎንታዊ አስተሳሰብ ብቻ  ግለሰቡ የሚፈልገውን  ማንኛውንም ገንዘብና ጤና ያለ ምንም ችግር መሳብ እንደምትችል ቃል በመግባት ከእውነታው የራቁ ተስፋዎችን በሰዎች ውስጥ ይፈጥራል። አወንታዊ አስተሳሰብ ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም፣ ግቦችን ማሳካት ብዙውን ጊዜ ቁርጠኝነትን፣ ጠንክሮ መሥራትን እና የተለያዩ ስልቶችን እንደሚጠይቅ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ትምህርቱም ሆነ ልምዱ ሰዎች ምኞቶቻቸውን እንዲያሳዩ እና ስለ ግቦቻቸው በአዎንታዊ መልኩ በማሰብ በሕይወታቸው ውስጥ አዎንታዊ ልምዶችን ማምጣት እንደሚችሉ የሚጠቁም ታዋቂ ጽንሰ-ሀሳብ ነው.


ጨረስኩ 

ቸር ሰንብቱ 

________

ከዚህ በፊት የቀረቡ ክፍሎች

ክፍል አንድ

ክፍል ሁለት

_____

ናዝራዊ Tube

Report Page