ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ

ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ

http://debregelila.org/?p=1227

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን ስለ ጌታ ትንሣኤ ማስረጃ እያቀረበ ነው:: በዚያን ዘመን ለጌታ ትንሣኤ ማስረጃ ስትጠቅስ በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል ብለህ እንዳትጠቅስ ገና ወንጌላት አልተጻፉም:: ቢጻፉም ማቴዎስ በሕይወት እያለ በቃሉ መመስከር ሲችል ጽሑፉን ማስረጃ ማድረግ አያስፈልግህም:: ስለዚህ ለመነሣቱ ማስረጃዎች ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች ነበሩ:: በሕይወት ያሉትን የዓይን ምስክሮችን መጥቀስ ይቻላል:: የዓይን እማኞች ምስክርነት ከጽሑፍ በላይ የታሪክ ማስረጃ ነው:: ስለዚህ ጳውሎስ ስለ ጌታ ትንሣኤ “እነ እገሌ አይተውታል” እያለ መዘርዘርን መረጠ::

ጌታ ከተነሣ በኋላ እንደ ቀድሞው ለሁሉ አልታየም:: እርሱን ለማየት የተገባቸው ጥቂት ወደ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ነበሩ:: በማኅበር ያዩት አሉ:: በግል ያዩት አሉ::
ያዩት ነገር ወንጌል የሆነላቸው ብፁዓን ዓይኖች ያሏቸው እንዴት የታደሉ ናቸው? የተሰቀለውን ተነሥቶ ያዩት! ዳግም በሚመጣበት አካል የተገለጠላቸው ምንኛ የታደሉ ናቸው? ከመድኃኔ ዓለም አፍ ተቀብለው ኪዳን ያደረሱ! የጌታን ቅዳሴ ተቀብለው ያስቀደሱ! የትንሣኤው ማግስት ምስክሮች እንዴት ዕድለኞች ናቸው? ቢሞቱም እንኳን መነሣታቸውን በጌታ ትንሣኤ አይተው ደስ ብሎአቸው ያንቀላፉ እነርሱ ምንኛ የታደሉ ናቸው?

ቅዱስ ጳውሎስ በወንጌል ከተጠቀሱት ከነ ኬፋ በተጨማሪ ለይቶ ጌታ ለማን ለማን እንደታየ ገለጸ:: ለያዕቆብ ታየ ብሎ የእልፍዮስን ልጅ ለይቶ ጠቀሰው:: የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት ይህ ሐዋርያ ከሌሎች በተለየ የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም ብሎ የተሳለና አክፍሎትን የጀመረ ነበርና ጌታ ለይቶ ክብሩን አሳይቶታል:: ከዚያም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ ብሎ የጌታን ድኅረ ትንሣኤ አስተርእዮ ዘረዘረ:: እኔ ማለትን የማይወደው ትሑት ቅዱስ ጳውሎስ “ከሁሉ በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ አለ::

ጭንጋፍ ምንድር ነው? ጭንጋፍ (ጸዕጻዕ/ ተውራድ) ለፅንስ የሚነገር ቃል ነው:: መወለድ ያለበትን ጊዜ ያልጠበቀ ያለ ጊዜው የተወለደ ፅንስ ነው:: በመጠኑ ከሌላው ጊዜውን ከጠበቀ ፅንስ የሚያንስ ሲሆን ዕድገቱን በተገቢው ጊዜ ከሚወለድ ልጅ ጋር ለማስተካከል ሲባል በሙቀት ማቆያ ክፍል እንዲቆይ ይደረጋል:: ይህ ፅንስ ሲወለድ በሕመም ውስጥ ሆኖ ተሰቃይቶ ተጨንቆ ነው::

ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን ለመግለጽ የተጠቀመበት ይህ አንድ ቃል የሕይወት ታሪኩን ጠቅልሎ የያዘ ድንቅ ቃል ነበር::ቅዱስ ጳውሎስ ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ብርሃን የሆነ ሐዋርያ ቢሆንም እንደ ዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በጊዜው የተጠራ አልነበረም:: እርሱ ከሐዋርያት ጋር አብሮ በዳግም ልደት የተወለደ ሳይሆን ያለ ጊዜው ክርስቶስ ባረገ በስምንተኛው ዓመት የተጠራ ነበረና ራሱን ካለ ጊዜው ከተወለደው ፅንስ ጋር አመሳስሎ እንደ ጭንጋፍ የምሆን ብሎ ጠራ::

ጭንጋፍ ሲወለድ በመጠኑ ከሌላው ፅንስ ያነሰ ይሆናል::
ቅዱስ ጳውሎስም ራሱን ጭንጋፍ ካለ በኋላ “እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ” ብሎ አብራርቶታል:: (1ቆሮ 15:9)

ልጅ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ በሥቃይ ነው:: ጤና ያጣል ይታመማል:: እናቲቱም ትታወካለች በድብታ በጭንቀት ትቸገራለች:: ባለሙያዎቹ እንደሚሉት እናት ያለ ጊዜው ከተወለደ ልጅዋ ጋር እናታዊ ትስስር ለመፍጠርና የእናትነት ፍቅርዋን ለመሥጠት ባልጠበቀችው ጊዜ የመጣ በመሆኑ ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ትቸገራለች:: በአጭሩ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ እሱም ይሰቃያል እናቱንም ያስጨንቃል:: ወዲያው እንደሌላ ሕፃን በሰው እጅ አይታቀፍም:: ከተፈጥሮአዊ እስከ ሰው ሠራሽ እንደየጊዜው እየዘመነ በሔደው የልጅ ሙቀት መስጫ መንገድ እየታገዘ የሰውነት አካሎቹ በአግባቡ መሥራት እስከሚችሉና በሽታ መቋቋም እስከሚችል ይቆያል::

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ጭንጋፍ ነበርኩ ያለው ለዚህ ነው:: በዳግም ልደት የተወለደው በደማስቆ መንገድ ወድቆ ሊቋቋመው ባልቻለው ብርሃን ተመትቶ ነበር:: “ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሲሰማ ፅንስ ነውና ዓይኑን እንኳን መግለጥ አልቻለም ነበር::
ከተወለደ በኋላም ወዲያው ወደ ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ወደ ሐዋርያት ማኅበር አልገባም:: እንደ ጭንጋፍ የምሆን እንዳለ ሙቀት ያስፈልገው ነበርና የሰው እጅ ሳያቅፈው ሦስት ዓመት በሱባኤ ቆይቶ በመንፈስ ቅዱስ ተሟሟቀ::

“ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከሦስት ዓመት በኁዋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ” ብሎ ስለ መንፈሳዊ ኃይል መልበሱ ይናገራል:: (ገላ 1:15-18)

ጭንጋፍ ሆኖ የተወለደ ልጅ የሚገጥመው ችግር ከወላጆቹ ጋር በሥነ ልቡና ለመተሳሰር መቸገሩ ነው::ቅዱስ ጳውሎስን ለማመንና እንደ ልጅ ለመቀበል የቤተ ክርስቲያን ማኅበርም ተቸግራ ነበር::

“ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት” ሐዋ 9:26 ስለዚህ ሐዋርያው እንደ ጭንጋፍ ነኝ አለ::

Report Page