በመተከል ዞን ከገዢው ፓርቲ አመራርና አባላት ውጭ በኢንቨስትመንት መሳተፍና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ማግኘት እንደማይቻል ተገለጸ

በመተከል ዞን ከገዢው ፓርቲ አመራርና አባላት ውጭ በኢንቨስትመንት መሳተፍና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ማግኘት እንደማይቻል ተገለጸ

http://addismaleda.com/archives/34635

ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት ውጭ በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሳተፍም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ማግኘት እንደማይቻል ተገልጿል።


በዞኑ በተለይም በቡለን ወረዳ የከበሩ የማዕድን ሃብቶችን ለማውጣት፣ የእርሻ መሬት ወስዶ ለማልማት እና የመንግሥት ሠራተኞች ሆኖ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት የገዥው ፓርቲ አመራር ወይም አባል መሆን ግድ ይላል ነው የተባለው።


በዚህ ጉዳይ ላይ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ካቀረቡ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ፤ ማንኛውም የገንዘብ አቅም ያለውና መስፈርት የሚያሟላ ሰው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተደራጅቶ ቦታ መጠየቅና መውሰድ ቢችልም፤ በቡለን ወረዳ ውስጥ ግን “የእኛ ፓርቲ አባል ስላለሆናችሁ ማስተናገድ አንችልም” የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡


አክለውም፤ በዞኑ የቀበሌ መታወቂያ እንኳ ለማውጣት እና ለማሳደስ የገዢው ፓርቲ አባል መሆንን እንደሚጠይቅ በመጠቆም፣ ገዢውን ፓርቲ የማይደግፉ ሰዎች አገልግሎቱን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን አክለዋል።


“ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች በብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና በቤተሰቦቻቸው እየተያዙ ነው፡፡” ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በቡለን ወረዳ ማሳ፣ ዳንጉርጋ፣ ሞራ፣ ማጣ እንዲሁም ኩየ በተባሉ ቀበሌዎች በብዛት የከበሩ ማዕድናት ያሉባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ተከትሎ፤ ከባለስልጣናት ውጭ ሌላው የአካባቢው ማህበረሰብ እየተጠቀመ አይደለም ብለዋል።


ይህን ዓይነት ድርጊት “ለምን?” ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው እንደሚባረሩ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በዚህም በቡለን ወረዳ ጥያቄ ያነሱ ስድስት የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ መባረራቸው ተመላክቷል።


የብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባልትን ብቻ የተለየ ተጠቃሚ የማድረጉ ሥራ፤ በኹሉም የክልሉ አካባቢዎች እየተባባሰ የመጣ ድርጊት ሆኗልም ነው የተባለው።


የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የቀረበው ቅሬታ ውሸት መሆኑን ገልጾ፤ “ማንኛውም መስፈርቱን የሚያሟላ ሰው በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መሳተፍ ይችላል” ሲል ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል።


ቢሮው አክሎም ቅሬታ ያላቸው ሰዎችም በግልጽ ቅሬታቸውን ለእኛ ቢያሳውቁን ጉዳዩን አጣርተን የምናሳውቅ ይሆናል ሲል ገልጿል።

Report Page