ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፰

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፰

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

          አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

                   ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ክርስቶስ ተንሥአ እም ሙታን
በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን
አግዓዞ ለአዳም
ሰላም
እምይእዜሰ
ኮነ
ፍስሐ ወሰላም

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፰


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ግንቦት ስምንት በዚች ቀን አባ ዳንኤን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን አረፈ።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

       ታላቁ አባ ዳንኤል

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው፤ በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው፤ ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን አይቷልና፤ አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ (መንኖ) ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው፤ ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን (በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነበር:: በገዳመ አስቄጥስ እና በደብረ ሲሐት ይታወቃል::

❖ ታላቋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው::

❖ ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል፤ ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል፤ ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው::

❖ በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆኖ የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው፤ አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በኋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል::

❖ ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም፤ ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ ድውያንን ሲፈውስ ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል፤ ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል::

❖ በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር፤ በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል፤ ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል፤ እርሱ ገንዞ ቀብሮ ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እሥራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን (ለ38 ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች) እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን (መንግስቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት) መጥቀስ እንችላለን::

❖ ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል፤ ለምሳሌ በሴቶች ገዳም እብድ ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዻዻሳቱ ሳይቀር "እብድ ነው" ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል::

❖ አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር፤ አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል::

❖ ጻድቁ አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባልድሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ድሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ፤ ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው "አዎ ጌታየ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው:: ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ::

❖ ጻድቁ ወሬውን ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት፤ ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ" አለው፤ እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች "ልጄ ሆይ ማር!" አለችው፤ ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው፤ ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም ሊዘርፍ በማታለል ገባ ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዐይነ ስውሯን ቢቀቧት ዐይኗ በርቷል፤ ሽፍታውም ደንግጦ ንስሃ ገብቷል:: አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::

📌 በተረፈው ግን ከቅድስና ሕይወቱ ባሻገር

1.በገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ ባሳየው ትጋት::

2.በሃይማኖት ጠበቃነቱ በደረሰበት ድብደባና ስደት::

3.ብዙ የበርሃ ቅዱሳንን በየበአታቸው እየዞረ በመቅበሩ::

4.የብዙ ስውራን ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በመሰብሰቡ::

5.በየጊዜው በእግዚአብሔር ኃይል ይፈጽማቸው በነበሩ ተአምራት እና

6.ለድንግል እመቤታችን ማርያም በነበረው ልዩ ፍቅር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብረዋለች::


ቸር አምላክ ክርስቶስ ከዕርገቱና ከጻድቁ በረከት በረከት አይለየን፤ በጸሎቱም ይማረን


  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

    ሰማዕቱ አቡነ ዮሐንስ

 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህንንም ቅዱስ ግብፅ ስንሑት በምትባል ሀገር በ14 ዓመቱ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት እየመራው ወስዶ ከገዳም አስገባው፤ ሃይማኖትን ጠንቅቆ ከተማረ በኋላ በ21 ዓመቱ መንኩሶ ተጋድሎውን ጀመረ፤ ቅዱስ ዮሐንስ በገዳም በተጋድሎ ሲኖር መልአኩ ድጋሚ ተገልጦለት የብርሃን አክሊል አሳይቶ ወደ አትሪብ ከተማ ሄዶ በክርስቶስ ስም ሰማዕት እንዲሆን ነገረው።

❖ በጥሪውም መሥረት እናትና አባቱን ተሰናብቶ ወደ አትሪብ ሄዶ በከሃዲው መኰንን ፊት የክርስቶስን አምላክነት መመስከር ጀመረ፤ ብዙዎቹ የመኰንኑ ወታደሮች በእርሱ እምነት አመኑ፤ ነገር ግን መኰንኑና ክፉዎች ተባብረው በልዩ ልዩ ዓይነት መንገድ ጽኑ መከራን አደረሱበት፤ መልአኩም እየተገለጠ እያጽናናው ቁስሎቹን ይፈውስለት ጀመር፤መኰንኑም ወደ እንዴና ሀገር ላከውና በዚያም እጅግ አሠቃዩት፤ በተአምራትም ብዙዎችን አሳመነ፡፡

❖ የእንዴናውም መኰንን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ግንቦት 8 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠውና ሰማዕትነቱን በድል ፈጽሞ የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፤ ማኅበርተኞቹ የሆኑ 224 ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተሰይፈው ዐረፉ፤ በቅዱስ ዮሐንስም በመቃብሩም ላይ 12 ቀን ሙሉ ቀስተ ደመና ተተክሎና መቃብሩን ሸፍኖት ታይቷል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን


📌 ግንቦት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱሳን የጌታ ቤተሰብ (120ው)

2.ቅዱስ አባ ዳንኤል ጻድቅ

3.ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት

4.ቅዱስ መክሲሞስ መስተጋድል

5.አቡነ ዮሐኒ ዘደብረ ዳሞ (አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ለምንኩስና ያበቁ)


📌 ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት

2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)

3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)

4.አቡነ ኪሮስ

5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን

6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)


✍️"እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ፤ እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ"

📖ሉቃ 24:50-53

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።

ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ

             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 

───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page