ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፮

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፮

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

          አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


                   ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ክርስቶስ ተንሥአ እም ሙታን
በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን
አግዓዞ ለአዳም
ሰላም
እምይእዜሰ
ኮነ
ፍስሐ ወሰላም

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፮

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ግንቦት ስድስት በዚች ቀን ከግብጽ ደቡብ ዳፍራ ከሚባል አገር የከበረ አባ ይስሐቅ ምስክር ሁኖ አረፈ።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

      አባ ይስሐቅ ጻድቅ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ለዚህም ቅዱስ በሌሊት ራእይ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾለት የሰማዕትነትን አክሊል ትቀበል ዘንድ ጣዋ ወደሚባል አገር ሒድ አለው፤ ከዚያም በነጋ ጊዜ ከመሔዱ በፊት አባትና እናቱን ሊሰናበታቸው ተነሣ፤ ሁለተኛም የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ከአገሩ እስከ አወጣውና ሀገረ ጣዋ እስካደረሰው ድረስ እነርሱ በላዩ እያለቀሱ አልለቀቁትም፤ በደረሰም ጊዜ መኰንኑን በዚያ ከውሽባ ቤት አገኘው ከዚያም በወጣ ጊዜ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የማምን እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ በመኰንኑ ፊት በግልጽ ጮኸ።

❖ ከኒቅዩስ ሀገርም እስኪመለስ ቅዱሱን ወስዶ እንዲጠብቀው ከወታደሮች አንዱን አዘዘው ከዚያ ወታደርም ጋራ ቅዱስ ይስሐቅ አልፎ ሲሔድ በመንገድ ዳር የተቀመጠ አንድ ዕውር የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ይቅር በለኝ ዐይኖቼንም አድንልኝ ብሎ ለመነው።

❖ አባ ይስሐቅም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለዚያ ዕውር ለመነው ያን ጊዜም ዐይኖቹ ተገለጡ፤ ይህንንም ድንቅ ተአምር ወታደሩ አይቶ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የክርስቲያን ወገን ሆነ፤ መኰንኑም በተመለሰ ጊዜ ያ ወታደር በመኰንኑ ፊት የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ በመታመን ሰማዕት ሁኖ አክሊል ተቀበለ።

❖ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ቅዱስ ይስሐቅን ጽኑ ሥቃይን አሠቃይቶ ወደ ሀገረ ብህንሳ ሰደደው በዚያም አሠቃዩት፤ በመርከብም ሲወስዱት የጽዋ ወኃን ለመናቸው ከቀዛፊዎችም አንዱ አንድ ዐይኑ የታወረ ውኃን በጽዋ ሰጠው የከበረ ይስሐቅም ያን ውኃ በላዩ ረጨ ዐይኑም ድና እንደ ሌላዪቱ ሆነች።

❖ ጽኑ ሥቃይን የሚአሠቃዩት የብህንሳ ሀገር ሰዎችም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ ወደ መኰንኑ ወሰዱትና ብትገድለውም ብትተወውም አንተ ታውቃለህ አሉት፤ መኰንኑ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ወዲያውኑ አዘዘ የከበረች ራሱንም ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም ተቀበለ።

❖ በዚያም ምእመናን ሰዎች ነበሩ የአባ ይስሐቅንም ሥጋ በሠረገላ ጭነው በበሮች እያሳቡ ዳፍራ ወደተባለ አገሩ አደረሱት ያሻግሩትም ዘንድ መርከብ ባላገኙ ጊዜ ተሸክመው አሻግረው ወደ ቤቱ አደረሱት፤ ቤቱንም አፍርሰው በስሙ ቤተ ክርስቲያን አድርገው ሠሩዋት ሥጋውንም በውስጥዋ አኖሩ ከእርሱም የሚያስደንቁ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ እውነተኛ ምስክር ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                  አርኬ

✍️ሰላም ለይስሐቅ በትዕግሥተ ሕማም ዘተኀየለ። ቀኖተ ኀፂን ርሱን አመ ውስተ ዕዝኑ ተተክለ። ኢተግሕሠ ዓዲ ወኢተአንተለ። ወድኅረ በመጥባሕት አጽፋረ እዴሁ ተነቅለ። እንዘ ይወድዩ በቍስሉ ግንፋለ።        

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

          አባ መቃርስ ካልዕ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚችም ቀን የእስክንድርያ ቄስ የከበረ አባት አባ መቃርስ አረፈ፤ ይህም ቅዱስ በአባቱ በሚቀድመው በታላቁ በክቡር አባ መቃርስ ዘመን ለአስቄጥስ ገዳም አባት ሁኖ ብዙ ትሩፋትን ሠራ።

❖ ስለእርሱም እንዲህ ተባለ አንዲት ዘመሚት ነክሳው ገደላት ከዚህም በኋላ ተጸጽቶ ነፍሱን ገሠጻት ስለ ዘመሚቷም ሞት በበረሀ ወደአለ ወንዝ ወርዶ ሥጋውንም ለዘመሚት ገልጦ እንደዝልጉስ እስኪሆን በዚያ ስድስት ወር ኖረ፤ ከዚህ በኋላ ወደበዓቱ ተመለሰ መቃርስ እንደሆነም ማንም አላወቀውም።

❖ አንድ ጊዜም እየጸለየ አምስት ቀን አምስት ሌሊት ቆመ ልቡም ወደ ሰማይ ተመስጦአል ሰይጣናትም እስከ ተቃጠሉ ድረስ ይቺ ትጋትና ተጋድሎ ከሠራው ትሩፋት ሁሉ ትልቃለች አሉ፤ አንድ ጊዜም የረዓይትን ቦታዎች ሊያይ ወዶ ወደ በረሀ ውስጥ ገባ ዐሥር ቀኖችም እየተጓዘ ኖረ፤ በሚመለስም ጊዜ ምልክት ሊሆኑት መንገዱን እንዳይስት ለምልክት የሚያኖራቸው ሸንበቆዎች ከእርሱ ጋራ ነበሩና በየመንገዱ ተከላቸው።

❖ በደከመም ጊዜ ጥቂት ሊያርፍ በምድር ላይ ተኛ ተኝቶ ሳለም እነዚያን ሸንበቆዎች ሰይጣን ነቀላቸው አሥሮም በቅዱስ መቃርስ ራስጌ አኖራቸው፤ በነቃም ጊዜ አያቸውና ወዲያውኑ አጣቸው አደነቀ እንዲህ የሚልም ቃልን ሰማ።

❖ መቃርስ ሆይ ሃይማኖት ካለህ አታወላውል በሸንበቆዎችም አትታመን የእስራኤልን ልጆች በበረሀ ሲመራቸው የነበረ የብርሃን ምሰሶ እርሱ እንደሚመራህ እመን እንጂ አትጠራጠር፤ ወዲያውኑ የብርሃን ምሰሶ አይቶ ተመለሰ።

❖ ከዚህም በኋላ በጎዳና ሳለ ተጠማ እግዚአብሔርም ከበረሀ ላሞች አንዲቷን ልኮለት ወተቷን ጠጥቶ ረካ ወደ በዓቱም ተመለሰ፤ በአንዲት ቀንም ጅብ ወደርሱ መጥታ ልብሱን ይዛ ትስብ ጀመር እርሱም እስከ ዋሻዋ ተከተላት፤ ሦስት ልጆቿን አወጣችለት በአያቸውም ጊዜ ዕውሮች ሁነው አገኛቸው ከልቡናዋም አሳብ የተነሣ ያቺን ጅብ አደነቃት፤ ግልገሎቿንም ይዞ በዐይኖቻቸው ውስጥ ምራቁን ተፋ፤ አዳኝ በሆነ በመስቀል ምልክትም አማተበባቸው ያን ጊዜ ድነው ከእናታቸው ኋላ ሮጡ ጡቷንም ጠቡ ከዚህ በኋላም ወደ በዓቱ ተመለሰ እርሷም የበግ አጐዛ አመጣችለት እርሱም ተቀብሎ በላዩ እየተኛ እስከሚአርፍበት ጊዜ በእርሱ ዘንድ አኖረው።

❖ በአንዲት ጊዜም ደግሞ ልብሱን ለውጦ በሕዝባዊ አምሳል ሆኖ ወደ አባ ጳኵሚስ ገዳም ሔደ በታላቁም ጾም ሳይበላ ሳይጠጣ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ቆመ፤ የሚሠራውንም እንደቆመ ይታታ ነበር እንጂ አይቀመጥም መነኰሳቱም አባ ጳኩሚስን ይህን ሰው ከእኛ ዘንድ አውጣው ሥጋ የለውምና አሉት አባ ጳኵሚስም ሥራውን ይገልጥልኝ ዘንድ እግዚአብሔርን እስከምለምነው ታገሡኝ አላቸው፤ በለመነውም ጊዜ የእስክንድርያው መቃርስ እንደሆነ እግዚአብሔር አስረዳው።

❖ በዚያን ጊዜም አባ ጳኵሚስና መነኰሳቱ ሁሉ ወደርሱ ሒደው እጅ ነሱት ከእርሱም ቡራኬ ተቀብለው ደስ ተሰኙበት ወደቤተ መቅደስም ከእሳቸው ጋራ አስገቡት፤ በገዳሙ ውስጥም በሥራቸው በመመካት በባልንጀሮቻቸው ላይ የሚታበዩ የዚህን ቅዱስ አባት የአባ መቃርስን ጸጋውን አይተው ትሑታኖች ሆኑ። ከዚህ በኋላም ወደ በዓቱ ወደ አስቄጥስ ገዳም ተመለሰ።

❖ በእስክንድርያ አገርም ዝናብ በተከለከለ ጊዜ ዝናብን እንዲያወርድ አንበጣንም እንዲአጠፋ ወደ እግዚአብሔር አብሮት ለመጸለይ ወደርሱ ይመጣ ዘንድ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስ እየማለደ ላከበት፤ ያንጊዜም ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ አገር ሔደ ሕዝቡም በታላቅ ደስታ ተቀበሉት በልቡም ጸለየ ብዙ ዝናብም ዘነበ ከዝናብ ብዛት የተነሣ ምድሪቱ ትጠፋለች ብለው እስቲአስቡ ድረስ ሁለት መዓልት ሁለት ሌሊት እየዘነበ ኖረ፤ እጅግም ፈርተው አባታችን ሆይ ዝናቡን አስወግዶ በልክ ይሆን ዘንድ እንዳንጠፋ ስለ እኛ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ ብለው ለመኑት ያንጊዜም ጸለየ ዝናቡም በርቶ በእግዚአብሔር ቸርነት ፀሐይ ወጣላቸው።

❖ ይህም አባት ብዙ ታላላቅ ትሩፋቶችን ሠርቷል እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆች ተአምራትን ገለጠ ርኵሳን አጋንንት ያደሩባቸውንና ብዙዎች በሽተኞችን አዳናቸው፤ ይህ አባትም የሠራቸውን በጎ ሥራዎች ሊቆጥራቸው የሚችል የለም አንድ ሰው በጎ ሥራ እንደሠራ የሰማ እንደሆነ ሰውዬው እንደሠራው እስከሚሠራ አይተኛም፤ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ክብር ምራቁን ሳይተፋ ስልሳ ዓመት ኖረ። መቶ ዓመት ከሆነውና ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በበጎ ሽምግልና አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

                    አርኬ

✍️ሰላም ለመቃርስ ሕሊና መንፈስ ዘተውህቦ። መንገለ አርያም ያንብር ኃይለ መለኮት ኀበ ቦ። ወዕጓላቲሃ ለዝዕብ እምሕማመ ዑረት ወተመንድቦ። ህየንተ አሕየወ ላቲ በአጸብዒሁ አቲቦ። አነጻ በግዕ ወሀበቶ ዐስቦ።        

በዚችም ዕለት የቅዱስ ኤስድሮስ አባት በንደላዖስ በምስክርነት አረፈ። ደግሞ የምንኵስናን ሥራ ገንዘብ ካደረግሁ ይበቃኛል ብሎ ጵጵስና አልሾምም ያለ የጻድቁ የአባ አሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

   ቅድስት ዲላጊና 4 ሴት ልጆቿ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚችም ቀን ቅድስት ዲላጊ ከአራት ልጆቿ ጋራ ምስክር ሆና አረፈች እነርሱም ሱርስ ኀርማን ያአፋ ናቸው፤ ይችም ቅድስት በክብር ባለቤት ክርስቶስ ሃይማኖት የጸናች ናት።

❖ መኰንኑ አርያኖስም ሀገረ አስና በደረሰ ጊዜ ልጆቿን እየነዳች ተቀበለችው በፊቱም ቁማ አርያኖስ ሆይ ሰማይንና ምድርን በውስጣቸው ያለውን በፈጠረ በክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ አለችው።

ልጆቿም እንደርሷ እኛ ክርስቲያን ነን እያሉ በግልጽ ጮኹ።

መኰንኑም ሰምቶ ቁጣን ተመላ ራሳቸውንም በሰይፍ ቆረጠ ምስክርነታቸውንም ፈጽመው ነፍሶቻቸውን ወደ ክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክት ወሰዱ። በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                     አርኬ

✍️ሰላም ለኪ ሰማዕት ዲላጊ። ሠናይተ ስምዕ ዘሀገረ እስና ዘኀዳጊ። ምስለ ደቂቅኪ አርባዕ እንበለ ትንትጊ። እምትሡዒ ለአማልክት ወእምዕጣነ ታዕርጊ። ተመትሮ ክሣድ አብደርኪ ወኀረይኪ ዮጊ።

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

   እናታችን ቅድስት ሰሎሜ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚችም ዕለት ደግሞ ንጽሕናን ቅድስናን ድንግልናን ገንዘብ ያደረገች ተሐራሚት ሰሎሜ አረፈች፤ ይችም ቅድስት ወረብ ከሚባል አገር ናት ወላጆቿም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው በበጎ አስተዳደግም አሳደጉዋት፤ በአደገችም ጊዜ እርሷ ሳትፈቅድ አንድ መኰንን አጭቶ በሠርግ አገባት። ያን ጊዜም አምላካዊ ኃይል ከልክሎት ወደርሷ መቅረብ አልቻለም አባለ ዘሩ ተቀሥፎአልና።

❖ በእንደዚህም እያለች ራሷን ሠውራ በሌሊት ሔደች በእግዚአብሔር ኃይል አመለጠች፤ ቅዱሳን በአሉበት ሁሉ በመዞር በጾም በጸሎት ተወስና ዕውነተኛ መንገድን ጌታ ይመራት ዘንድ በቀንና በሌሊት ስትማልድ ኖረች።

❖ ጌታችንም ልመናዋን ሰምቶ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም አደረሳት የመላእክት የሆነ አልባሰ ምንኲስናን በአባ ዮሐንስ ከማ እጅ ለብሳ የሰውን ልብ የሚያስደነግጥ ጽኑ ገድልን ተጋደለች።

❖ በጾም በጸሎት በተመሰገነ ገድል ሁሉ የፍጹማን አባቶችን ጐዳና ተጓዘች፤ በመጽሐፈ ገድሏ እንደ ተጻፈ ብዙዎች ድንቆች ተአምራትንም እስከ ማድረግ ደርሳ ከዚህ በኋላ በሰላም አረፈች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                        አርኬ

✍️ ሰላም ዕብል ለሰሎሜ ጠባብ። ጸቃውዐ መዐር ዘትትዔለድ አምሳለ ተገብሮታ ለንህብ። ምስለ ደናግል ትትዓሠይ በቤተ ከብካብ። አህለቀት ሥጋሃ በሥቃየ ፃማ ዕፁብ። እስከ ወደይዋ በንስቲት መሶብ።

በዚችም ዕለት ገድሉን በሰይፍ የፈጸመ የከበረ አባት አባ ደናስዮስ አረፈ። እግዚአብሔርም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

                      አርኬ

✍️ሰላም ለደናስዮስ ለይስሐቅ ማእምሩ። እስመ ተፄወወ በተአምሩ። መኰንን ጠግዐ ወለጸቀ ምስለ መንበሩ። ከመ ኢይሑር ለምሳህ ኀበ ተጽሕፈ ማኀደሩ። እስከ በመጥባሕት ፈጸማ ለበድሩ።

✍️ሰላም ለልደትከ እምነ ኅሪት ማሕፀን። ዘየዓውዳ መልአክ በሰይፈ እሳት ርሱን። ሲኖዳ ርእሶሙ ለባሕታውያን ኄራን። ከመ ገብረ እኅወ እምከ አመ ለሊከ ሕፃን ።መልዕልተ ድማሕየ ይንበር እዴከ ዘይምን።        

📌 ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ

2.እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮዽያዊት

3.አባ ይስሐቅ ጻድቅ

4.ቅድስት ዲላጊና 4 ሴት ልጆቿ (ሰማዕታት)

5.ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት

6.ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት (የታላቁ ኤስድሮስ አባት)

7.አባ አሞን ጻድቅ (ዽዽስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት)

📌 ወርኀዊ በዓላት

1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም

2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን

3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል

4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ

5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ

6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ

7.ቅድስት ሰሎሜ

8.አባ አርከ ሥሉስ

9.አባ ጽጌ ድንግል

10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

✍️"ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ፤ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በርሱ እኖራለሁ"

📖ዮሐንስ 6፥53-56

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።

ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ     


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 

───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page