ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፯

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፯

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

          አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

                   ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ክርስቶስ ተንሥአ እም ሙታን

በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን

አግዓዞ ለአዳም

ሰላም

እምይእዜሰ

ኮነ

ፍስሐ ወሰላም

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት ፯

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ግንቦት ሰባት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያኛ የሆነ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አትናቴዎስ አረፈ።

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

   ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ ይህም ቅዱስ ሐናፊ ከሚባል የእስላም ነገድና ከአረማውያን ተወላጅ ነው ይባላል፤ እርሱም ከመምህር ከሚማሩ ሕፃናት ጋራ እያለ እርስ በርሳቸው በመጫወት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እየሠሩ ከእነርሱ ውስጥ ዲያቆናትን ኤጲስቆጶሳትንም ሲያደርጉ እሊያን የክርስቲያንን ልጆች አይቶ ጨዋታቸው ደስ ስለአለው ከእሳቸው ጋራ በጨዋታቸው አንድ ይሆን ዘንድ የክርስቲያንን ልጆች ለመናቸው፤ እነርሱም አንተ አረማዊ ነህና ከእኛ ጋራ አትደመርም ብለው ከለከሉት እርሱም ክርስቲያን እሆናለሁ አላቸው እነርሱም ደስ ተሰኙበት።

❖ ያን ጊዜም ወስደው በሊቀ ጳጳሳት አምሳል አደረጉት ከበታቹም ወንበር አድርገው ይሰግዱለት ጀመር፤ በዚያን ጊዜም ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስ በዚያ አለፈ የክርስቲያን ልጆች ሲጫወቱ በአያቸው ጊዜ አብረውት ላሉ ይህ ሕፃን ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ሹመትን ይሾም ዘንድ አለው አላቸው።

❖ አባቱም በሞተ ጊዜ ወደ አባ እለእስክንድሮስ መጣ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው፤ ከዚህም በኋላ የአባቱን ገንዘብ ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥቶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ሕግ ሥርዓትንም ከአባ እለእስክንድሮስ ዘንድ እየተማረ ኖረ እርሱም ተወዳጅ ልጅ አደረገው።

❖ ከዚህም በኋላ ዲቁና ሾመው የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ የተመላ ሆነ፤ የከበረ አባት እለእስክንድሮስም በአረፈ ጊዜ ይህን አባት አትናቴዎስን በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት።

❖ ከዚህ አስቀድሞ ግን የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ በተደረገ ጊዜ አባ እለእስክንድሮስ ከዚህ ዓለም ሳይለይ ይህም አትናቴዎስ ከእሳቸው ጋራ ተሰብስቧል፤ የጉባኤውም ጸሐፊ አድርገውት በኒቅያ ከተማ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከእሳቸው ጋራ ሠራ።

❖ ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ በሞተ ጊዜ አርዮሳዊ ልጁ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ አርዮሳውያንም በዙ ይህንንም አባት አርዮሳዊው ንጉሥ ከመንበረ ሢመቱ አሳደደው በእርሱም ፈንታ ጊዮርጊስ የተባለ ከሀዲ ሰው ሾመ።

❖ ከዚህም በኋላ ብዙ ጊዜ ሲአሳድዱትና ሲመልሱት ኖረ በስደቱም በአንዲት ምዕራባዊት አገር በአለ ጊዜ በዚያ የጣዖት ቤት አለች፤ በዚያችም የጣዖት ቤት ብዙ ሕዝቦች በውስጧ ይሰበሰባሉ፤ ለዚያችም የጣዖት ቤት በውስጧ የሚሠሩ ብዙ የሰይጣን ሥራዎች አሏት፤ እርሱም የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው ያቺንም የጣዖት ቤት አፍርሶ የአገር ሰዎችን ሁሉ እግዚአብሔርን ወደማወቅ መለሳቸው።

❖ ይህንንም አባት አምስት ጊዜ አሳደዱት የሹመቱም ዘመን አርባ ሰባት ሲሆን ዐሥራ አምስቱን ዓመት በስደትና በእሥራት ነው ያሳለፈው፤ ይህንንም አባት ብዙ መከራና ድካም መሰደድም ስለደረሰበት ሐዋርያዊ ተብሎ ተጠራ፤ በሚሞትበትም ጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ባገኝ ይህን የጣዖት ቤት ያፈርስ ዘንድ በፊቱ እኔ እየሰገድኩ እለምነዋለሁ፤ ይህም አባት ከአረፈ በኋላ ንጉሥ ልኮ ያንን የጣዖት ቤት አስፈረሰው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                      አርኬ

✍️ሰላም ለአትናቴዎስ ከመ ላዕሌሁ ተነበዩ። ደቂቀ ክርስቲያን ኵሎሙ እንዘ ይትዋነዩ። ሊቀ ጳጳሳት ዘኮነ ወምእመነ ክርስቶስ ዲበ ንዋዩ። ወበእንተ ዘበጽሖ ስደት እመንበረ ክብሩ ወእበዩ። ተሰምየ ሐዋርያዌ በኵሉ ዓያዩ።

✍️ሰላም ለዮሐንስ ዮሐንስ በጽድቁ። እምኁልቁ ከዋክብት ዘበዝኁ። ወእምኆፃ ባሕር ደቂቁ። እንዘ ይጼጉ ምጽዋተ ለእለ ይጽሕቁ። አሕለቀ ልብሶ ወኢያትረፈ ለስንቁ። እስከነ ተረክበ ውስተ ግብ ዕራቁ።


✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

      አቡነ ሲኖዳ 

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ዳግመኛም በዚህች ዕለት የባሕታዊያን አለቃ ግብፃዊው አባ ሲኖዳ ልደታቸው ነው፤ እኚኽም ታላቅ ጻድቅ ሀገራቸው ግብፅ ነው፤ የባሕታውያን አለቃ የሆኑ መስተጋድል አቡነ ሲኖዳ ከላዕላይ ግብፅ ከአክሚም አውራጃ የተገኙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡

❖ ገና ሳይወለዱ እናታቸው አንድ ቀን ውኃ ልትቀዳ ስትሄድ አንድ የበቁና ሴት አናግረው የማያውቁ ጻድቅ አባት ‹‹የማኅፀንሽ ፍሬ የተባረከ ነው›› ብለው ለደቀ መዛሙርቶቻቸውም የልጁን ታላቅ ክብር ነግረዋቸዋል፡፡

❖ ይህ ቅዱስ አባትም ስለ አቡነ ሲኖዳ መወለድ ትንቢት በተናገሩት መሠረት በዛሬዋ ዕለት ግንቦት 7 ቀን ተወለዱ፡፡

❖ የበግ እረኛም ሆነው ሳለ ስንቃቸውን ለነዳያን እየሰጡ እሳቸው ግን እስከ ማታ ድረስ ይጾሙ ነበር፤ ሌሊት ደግሞ ባሕር ውስጥ እየገቡ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፤ በጉድጓድ ውስጥ ሆነው ሲጸልዩ ዓሥር ጣቶቻቸው እንደፋና ሲያበሩ አንድ ጻድቅ አባት አይተዋቸው የልጁን ክብር ለወላጆቻቸው ቢነግሯቸው እነርሱም ‹‹እንዲህ ከሆነማ ለእግዚአብሔር ይሁን›› ብለው ወስደው ለመምህር ሲሰጧቸው ከሰማይ ‹‹እነሆ የባሕታውያን ራስ ይባላል›› የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰምቷል፡፡

❖ በገዳምም በታላቅ ተጋድሎ ሲኖሩ መልአክ ለመምህሩ የኤልያስን አስኬማ የዮሐንስን ቅናት እንዲያለብሳቸው ነግሮት አመንኩሰዋቸዋል፡፡

❖ አቡነ ሲኖዳ ንስጥሮስን ለማውገዝ በ431 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ቅዱስ ቄርሎስን ተከትለው በጉባኤው ተገኝተዋል፡፡

❖ ንስጥሮስንም አውግዘው ሃይማኖትን አጽንተው ሲመለሱ መርከበኞች ‹‹ሊቀ ጳጳሳቱ በሚሳፈሩበት መርከብ አትሳፈርም›› ብለው ቢከለክሏቸው አቡነ ሲኖዳ ሊቀ ጳጳሳቱን እጅ ከነሱ በኋላ ብሩህ ደመና ጠቅሰው በደመና ተጭነው ሲሄዱ ሊቀ ጳጳሳቱም መርከበኞቹም አይተዋቸው መርከበኞቹ ‹‹ጻድቅ ሰው አስቀየምን›› ብለው አዝነው ንስሓ ገብተዋል፡፡

❖ አንድ ቀን ሌሊት በጸሎት ላይ ሳሉ ጌታችን ተገልጦላቸው አብሯቸው ተቀመጠ፤ አባታችንም ጌታችንን ‹‹ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ ልዩ ሦስትነትህንና ጌትነትህን ስለሚነቅፉ ከሃድያን ወደ ጉባዔው እሄድ ዘንድ እንዲጠሩኝ ሊቀ ጳጳሳቱ ወደ እኔ ልኳልና እንደቀድሞው ታጸናኛለህን›› ብለው ጠየቁት፡፡

❖ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ ሲኖዳ ሆይ 120 ዓመት ኖረሃል ገና ሌላ ዕድሜ ትሻለህን በ9 ዓመትህ አስኬማን ለብሰህ እስካሁን አገልግለኸኛልና ይበቃሃል›› አላቸው፤ትልቅ ቃልኪዳንም ከሰጣቸው በኋላ ሐምሌ 7 ቀን ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለይቶ በክብር አሳርጓታል፡፡

ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን

📌 ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

2.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ)

3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን: ንብረቱን: ልብሱን ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው)

4.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ

📌 ወርሐዊ በዓላት

1. ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ) 

2. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

3. አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)

4. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት

5. አባ ባውላ ገዳማዊ

6. ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

✍️"ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ፤ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና"

📖ማቴዎስ 5፥10

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።

ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ     


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 

───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page