ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ ፲፪

ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ ፲፪

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

          አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ ፲፪

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሚያዝያ ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አባ እለእስክንድሮስ አረፈ።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

 ኤጲስቆጶስ አባ እለእስክንድሮስ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህ ቅዱስም አስቀድሞ በቀጰዶቅያ አገር ኤጲስቆጶስነት ተሹሞ ነበር፤ እርሱም የከበሩ ቦታዎችን ተሳልሞ በረከት ተቀብሎ ወደ አገሩ ሊመለስ አስቦ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በኢየሩሳሌምም ስሙ በርኪሶስ የሚባል መቶ ዐሥር ዓመት የሆነው ጻድቅ ሰው ነበረ ሹመቱንም ሊተው ይወድ ነበረ ወገኖቹ ግን አልለቀቁትም ።

❖ ቅዱስ እለእስክንድሮስም ሥራውን ፈጽሞ ወደ አገሩ ቀጰዶቅያ ሊመለስ በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ የሚል ቃል እነሆ ከሰማይ አሰማ ወደ እገሌ በር ውጡ አስቀድሞ የሚገባውንም ይዛችሁ በላያችሁ ኤጲስቆጶስነት ሹሙት፤ ያን ጊዜም ሲወጡ አባ እለእስክንድሮስን አገኙትና ያዙት፤ እርሱም እኔ የቀጰዶቅያ ኤጲስቆጶስ ነኝ የክብር ባለቤት ክርስቶስ በእነርሱ ላይ የሾመኝን መንጋዎቼን ልተው አይቻለኝም አላቸው።

❖ እነርሱም ከሰማይ ስለሰሙት ስለዚያ ቃል ስለርሱም እንደአመለከታቸው ነገሩት፤ ይህ ነገር ከእግዚአብሔር እንደሆነ በተረዳ ጊዜ ለበዓሉም የተሰበሰቡ አባቶች መከሩት ቃላቸውንም ተቀበለ ወደ ሀገሩ ቀጰዶቅያም እንዲህ ብሎ መልእክት ጽፎ ላካት፤ ይቅርታ አድርጉልኝ በእኔ ላይ አትዘኑ በእናንተ ላይም ኤጲስቆጶስ በእኔ ፈንታ ሹሙ እናንተም የተፈታችሁ ናችሁ ያቺን መልእክትም ከእርሱ ጋራ አብረው ከመጡ ከቀጰዶቅያ ሰዎች ጋራ ላከ።

❖ ከዚህም በኋላ እየተራዳው አምስት ዓመት ያህል ከአባ በርኪሶስ ጋራ ኖረ፤ ከዚህም በኋላ ሽማግሌው አባ በርኪሶስ አረፈ፤ አባ እለእስክንድሮስም መንጋውን ተረክቦ እንደ ሐዋርያት በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው፤ ከሀዲ መክስምያኖስም በነገሠ ጊዜ ይህን አባት ይዞ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ አሠቃየው።


❖ ከዚያም በላዩ የሚያደርግበትን እስከሚያስብ ድረስ አሠረው፤ ጌታችንም ይህን ከሀዲ ፈጥኖ አጠፋው ወገኖቹም ይህን አባት እለእስክንድሮስን ከእሥር ቤት አወጡት፤ ገርድያኖስም በነገሠ ጊዜ ጸጥታና ሰላም ሆነ ከክርስቲያን ወገኖች ላይም ጥቂት ወራት መከራው ጸጥ አለ፤ ገርድያኖስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ አማኒ የሆነ ፊልጶስ ነገሠ፤ እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ስለሚአምን በክብር ባለቤት በጌታ ክርስቶስ ሰም የታሠሩትን ምእመናንን ፈታቸው እጅግም አከበራቸው ይህም አባት በጸጥታ ኖረ።

❖ ከዚህም በኋላ ከሀዲ ዳኬዎስ ተነሣ ፊልጶስንም ገድሎ መንግሥቱን ወሰደ ክርስቲያኖችንም እጅግ አሠቃያቸው ይህንንም አባት ያዘው ብዙዎችንም የቤተ ክርስተያን ሊቃውንት ጽኑ ሥቃይም አሠቃያቸው፤ ይልቁንም ይህን አባት አብዝቶ አሠቃየው ጽኑ ግርፋትንም ገርፎ ስለት በአላቸው በትሮች የጐኑ ዐጥንቶች ተሰብረው ወደሆዱ እስቲገቡ አስመታው።

❖ ከዚህም በኋላ እስከ እሥር ቤት ጐትተው በዚያ እንዲጥሉት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት፤ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማይ እስከ ወረሰ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠ ድረስ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየታመነ በዚያ ወድቆ ኖረ በጸሎቱ የምትገኝ በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

                     አርኬ

✍️ሰላም ዕብል ለዘበእንተ ጽድቅ ዘተዘብጠ። ዐፅመ ገቦሁ ዘውስጥ እስከ ተቀጥቀጠ። እለእስከንድሮስ ዘኮነ በኢየሩሳሌም ሥሉጡ። ይምጻእ ይእዜ ንርአዪ ኅዳጠ። ዘምስለ እንጦንስ ወሉቃስ ወአኮ ፍሉጠ።

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚችም ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እግዚአብሔር ወደ ነቢዩ ኤርምያስ ላከው ጠባብና ረግረግ ከሆነ እሥር ቤት ሴዴቅያስ ንጉሥ በአሠረው ጊዜ የንጉሡ ባለሟልና የጭፍራ አለቃ የሆነው አቤሜሌክ አወጣው።

❖ ያንጊዜም የኢየሩሳሌምን ጥፋት እንዳያይ መራራ ምርኮንም እንዳይቀምስ ኤርምያስ ነቢይ መረቀው እንዲሁም ሆነ፤ ስሳ ስድስት ዓመትም ተኝቶ ኖረ ከእርሱ ጋራ ወይንና በለስ ነበረ አልተለወጠም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስቲመለሱ በለሱንም ከደብዳቤ ጋራ ወደ ኤርምያስ ባቢሎን አገር ላከው።

❖ ስለዚህም የዚህን የከበረ መልአክ ሚካኤልን በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን መታሰቢያውን እንድናደርግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙን አማላጅነቱ ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለም ይኑር አሜን።

                    አርኬ

✍️ሰላም ለከ ዘተፈሰይከ በክብር። መልአከ ኪዳኑ ወምክሩ ለእግዚአብሔር። ሚካኤል ረዳኢ ለእለ ውስተ የብስ ወባሕር። ለረድኤትከ ዘየዓዕቦ ነገር አልቦ በሰማይ ወአልቦ በምድር።

በዚችም ቀን የሀገር ጠመው ኤጲስቆጶስ የከበረ እንጦንስና የአውሳንዮስ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸው ከእኛ ጋራ ለዘላለም ይኑር አሜን።

በዚቺም ቀን መጥምቁ ዮሐንስ የተገለጠላቸው ጋይዮስና ኤስድሮስ አረፉ።በረከታቸው ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

                     አርኬ

✍️ሰላም ለጋይዮስ ወለኤስድሮስ ዓበሞ። ትእዛዘ ወንጌል ለፈጽሞ። ለረድኤተ ብእሲ ድውይ በጽሒቅ ወአስተሐምመ። አሐዱ ተሠይመ በፈቃዱ በዘይፌውስ ሕማሞ።ወካልኡ ተኀድገ ይትለአክ ድካሞ።


  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

    አባ ሳሙኤል ዘቆየጻ

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥   

❖ በኢትዮዽያ ቤተክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል፤ ምክንያቱም ዘመኑ፤ ክርስትና ያበበበት፤ መጻሕፍት የተደረሱበት፤ ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት፤ ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው፤ ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ

❖ አቡነ ተክለ ሃይማኖት

❖ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ

❖ አባ ሰላማ ካልዕ

❖ አቡነ ያዕቆብ

❖ ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ

❖ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ፤ አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው፤ በተጨማሪም

❖ 7ቱ ከዋክብት

❖ 47ቱ ከዋክብት

❖ 5ቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር::

❖ ከእነዚህ መካከልም የ7ቱ እና የ47ቱ ከዋክብት አስተማሪ የአበው 3ቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ ዘጣሬጣና ዘቆየጻ) የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::

❖ ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው አስተምረው አመንኩሰው መርቀው ሰደው ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ::

❖ ታላቁ ጻድቅና ሰባኬ ወንጌል አባ ዓቢየ እግዚእም (ጐንደር ውስጥ እባብና ጅብ እንዳይጐዳ የገዘቱ አባት ናቸው) የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ነበሩ ይባላል::

❖ ከ7ቱ ከዋክብት አንዱ የሆኑት የቆየጻው አባ ሳሙኤል የመድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዝሙር ናቸው፤ ፋሾ ውስጥ (ትግራይ አካባቢ) ተወልደው እንደሚገባ አድገው መጻሕፍትን ተምረው ደብረ በንኮል ገብተዋል::

❖ በዚያም ከ6ቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር የምናኔን ምሥጢርና ተጋድሎን አጥንተው በመነኮሱበት ቀን ብርሃን ወርዶላቸዋል፤ በጻድቁ መምህራቸው ለአገልግሎት ሲላኩም ለእርሳቸው ቆየጻ (ትግራይ) ደርሷቸዋል::

❖ በዚያም በጾም በጸሎት እየተጉ ስብከተ ወንጌልን እያስፋፉ ደቀ መዛሙርትን እያፈሩ ለዘመናት ኑረዋል::

❖ አባ ሳሙኤል በተለየ መንገድ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይጽፉ ነበርም ይባላል፤ በጊዜው 72ቱ ከዋክብት (70ው ሊቃናት) ከሚባሉ አበው ጋር በመተባበር 4ቱ ወንጌል በብራና በልዩ ጌጥ

❖ ያንንም ወስደው በመቃብራት አካባቢ ቢያስቀምጡት 211 ሰዎች ከሞት ተነስተዋል "ማን አስነሳችሁ" ሲባሉም "አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት ወአምላከ ሳሙኤል ጻድቅ" ሲሉ መስክረዋል::

❖ ይህን ወንጌል ሲጽፉም ቅዱሳን መላእክት ረድተዋቸዋል፤ ጻድቁ አባ ሳሙኤል ዘቆየጻ ከብዙ ድካምና ተጋድሎ በሁዋላ እዚያው በገዳማቸው ዐርፈዋል::

አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ በረከት ረድኤት ይክፈለን፤ በተሰጣቸው ቃልኪዳንና በጸሎታቸው ይጠብቀን

📌 ሚያዝያ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አቡነ ሳሙኤል ዘቆየጻ (ኢትዮዽያዊ)

2.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ

3.ቅዱስ አቤሜሌክ ኢትዮዽያዊ

4.ቅዱስ ባሮክ

5.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ዘኢየሩሳሌም

📌 ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት

2.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ

3.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ

4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)

5.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

6.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

7.ቅዱስ ድሜጥሮስ

✍️"ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም፤ እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላቹሃል፤ እላችሁአለሁና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም"

📖ማቴ 3፥37-39

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።

ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ

             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 

───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page