#fbc

#fbc


አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት ቀረቡ!

አቶ ልደቱ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

ፖሊስ በሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ/ም በቢሾፍቱ ለወጣቶች ገንዘብ በመስጠት ለብጥብጥና አመፅ በማነሳሳት በሚል ወንጀል እንደጠረጠራቸው አስታውቋል።

ባለፈው አርብ አራት ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸውና በዚህም ወቅት ሁለት ሽጉጦች ማግኘቱን አስታውቋል።

የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ለማቅረብም የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜንም የኦሮሚያ መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።

አቶ ልደቱ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቋሚ አድራሻ እና ቤት ያላቸው መታወቂያቸውም በዚያው መሆኑን በማንሳት በጊዜያዊነት በቢሾፍቱ ቤት እንዳላቸው በመግለፅ በፌደራል ፍርድ ቤት ነው መቅረብ ያለብኝ በሚል መቃወሚያ አንስተዋል።

በዋስ እንዲፈቱም በመጠየቅ የዛሬ ዓመት የልብ ቀዶ ጥገና ወዳደረጉበት ሀገር ዛሬ 4 ሰዓት ላይ ለመጓዝ የተዘጋጁ መሆናቸውን እና ትኬት ያላቸው ቢሆንም አሁን ታስረው እንደሚገኙና የአስም በሽተኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

የእስር አያያዙም ለኮቪድ-19 እንዳያጋልጠኝ ያሰጋኛል በማለት ይህ ታሳቢ ተደርጎ በዋስ ይፍታኝ ብለዋል።

መርማሪ ፖሊስ የእስር አያያዛቸው ምቹ እና ጥንቃቄ ያለው መሆኑን እና ከእስር ቢፈቱ ማስረጃ እንደሚሸሽበት በማሳወቅ ዋስትናውን ተቃውማል።

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው በዚያው በቢሾፍቱ አይታይ በሚል ላቀረቡት ወንጀሉ የተፈፀመው በቢሾፍቱ በመሆኑ እና መኖሪያቸወም በዚያው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እዚያው የማየት ስልጣን እንዳለው በማስረዳት ጉዳዩ በችሎቱ መታየት እንደሚቀጥል ትእዛዝ ሰጥቷል።

የዋስትና ጥያቄውንም ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

የአቶ ልደቱ ጠበቃም የክልሉ የጥብቅና ፍቃድ ባለማቅረባቸው ጥብቅና ሳይቆሙላቸው ቀርቷል። ፍርድ ቤቱም ፍቃድ ከሌላቸው ማማከር እንደማይፈቀድላቸው ገልፆላቸዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ

Report Page