#eth

#eth


የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሰሎሞን አሰፋ (ዶክተር) ባለፈው ሰኔ ወር ከሳዑዲ ዐረብያ ወደ ኢትዮጵያ የገባ አንበጣ መንጋ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች ላይ ተባዝቶ ወደ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ሰብል አብቃይ አካባቢዎች መዛመቱን አስታውቀዋል፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦና ሀብሩ ወረዳዎች፣ በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦና እና አርጎባ ወረዳዎች፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባቲ፣ ደዌ ሀረዋ እና አርጡማ ፉርሲ ወረዳዎች ላይ አልፎ አልፎ ቢከሰትም በሰብል ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የመከላከል ሥራውን ከሰኔ ወር ጀምሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየሠሩ መሆናቸውን የተናገሩት ዶክተር ሰሎሞን ‹‹አንበጣው በመጠኑ ሲያድግ እና የመንቀሳቀስ ሁነት ሲያሳይ በአውሮፕላን እና በመኪና የሚረጭ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹የሚበርረው አንበጣ ጉዳት አያደርስም፤ የሚበርረው አንበጣ እንቁላል ሲጥልና ማደግ ሲጀምር ነው ጉዳት የሚያደርሰው›› ብለዋል ምክትል ኃላፊው፡፡

እንደ ዶክተር ሰሎሞን ራያ ቆቦ ላይ አንበጣው ምንም ጥቃት አላደረሰም፤ አርሶ አደሮቹም በተለያዩ ከፍ ያለ ድምፅ በሚያወጡ መሳሪያዎች በመጠቀም እያባረረው ነው፡፡

የኬሚካል ርጭቱ የሚደረገው ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ መፈልፈያ ከሆነው አፋር ክልል ጭፍራ እና ተላላክ የሚባሉ ወረዳዎች ላይ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

አልፎ አልፎ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር ደዌ ሀረዋ አካባቢ ትናንት ጥዋት ተከስቶ እንደነበርና በአውሮፕላን ርጭት በማድረግ እንዲጠፋ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

አንበጣው በትግራይ ክልል አላማጣ እና ህንጣሎ ዋጅራት ወረዳዎች አካባቢ በመከሰቱ በአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ አውሮፕላኑ ወደዚው መሄዱንም ዶክተር ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡

‹ጂፒኤስ› በመጠቀም አንበጣው በጧቱ ሳይንቀሳቀስ በሰፈሩበት ቦታዎች ተጠንቶ የሚረጭ መሆኑን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ‹‹አንበጣው ወደ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር የመሄድ ዕድል የለውም›› ብለዋል፡፡

ክስተቱን የአማራ፣ የትግራይ፣ የአፋር እና የሶማሌ ክልል መንግሥታት በቅንጅት የአንበጣውን የሕይወት ዑደት ከእንጭጩ መቅጨት ካልቻሉ ለቀጣይ የመኸር ወቅት ሰብልም አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገበየሁ ወርቁ አንበጣው በዝናብ እጥረቱ ምክንያት ከተፈጠረው ድርቅ ያመለጡ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ደርሶ ጉዳት እንዳያደርስ በአስቸኳይ የደረሱ ሰብሎች እንዲሰበሰቡ ከአርሶ አደሮች ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ከባለፉት ሦስት ቀናት ጀምሮ አንበጣው በተከሰተባቸው የትግራይ ክልል ወረዳዎች ጋር አጎራባች የሆኑ የጻግብጂ፣ አበርገሌ፣ ጋዝጊብላ እና ሰቆጣ ወረዳዎች ባደረጉት ቅኝት አንበጣው እንዳልተከሰተ ማረጋገጣቸውን አቶ ገበየሁ ተናግረዋል፡፡

AMMA

Report Page