#ETH

#ETH


የሰላም ዋጋው ስንት ነው?(በውብዓለም ፋንታዬ)

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች ሲገናኙ ቅድሚያ ስለ ሰላማቸው ሁኔታ የሚጠያየቁት፡፡ ጠዋት ከእንቅላፋቸው ተነስተው “በሳላም አውለኝ”፤ ማታ ሲተኙም “በሰላም ያዋልከኝ በሰላም አሳድረኝ” ብለው ምስጋናቸውን የሚገልጹትም የሰላምን ትልቅ ዋጋ በመረዳት ነው፡፡ እናም ሁሉም ሰው ሊባል በሚችል መልኩ ሰላም በህይወቱ ላይ ትልቅ ውድ ዋጋ ያለው ነገር መሆኑን ይገነዘባል፤ ለሰላሙም ዘብ ይቆማል፡፡


ሆኖም ከብዙዎች በተቃራኒ ሰላም ለማደፍረስ የሚተጉ ኃይሎችም አሉ፡፡ በእነዚህ አይነት ሰዎች የተነሳ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ህዝቦች ሰላምና መረጋጋት እንዲርቃቸውና በአንጻሩ ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ሽብርተኝነትና ወንጀል ተንሰራፍተው የሰዎችን ዕለታዊ ኑሮ እንዲታወክ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

በሰላም እጦት ምክንያት የሚሊዮኖች ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተከስቷል፤ እየተከሰተም ነው፡፡ የ2017 Global Peace Index እንደሚያሳየው በአለም አቀፍ ደረጃ በሰላም እጦት ምክንያት በየዓመቱ 13 ነጥብ 6 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ እየተስተናገደ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ በእያንዳንዱ ቀን አንድ ሰው ማግኘት ከሚገባው ውስጥ 5 ዶላር ያጣል ማለት ነው፡፡

ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅና ደቡብ ሱዳን በሰላም እጦት ምክንያት እየተናጡ ከሚገኙ ሀገራት ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ፡፡ በተለይም ሶሪያና የመን በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየሩ ነው፡፡ የዓለም የስልጣኔ ቁንጮ የነበረችው ሀገረ ኢራቅም በአሸባሪ ቡድኖች ምክንያት ታላላቅ የስልጣኔ አሻራዎቿን ለመገበር ከመገደዷም በላይ ህዝቡ ለሞትና ለስደት ተዳርጓ፤ በከፍተኛ ስነ ልቦና ጫና ውስጥ ወድቋል፡፡


የሰላም መናጋት ሞት፣ አካላዊ ጥቃት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ወረርሽኝና ርሃብ እንዲነግሱ በር ይከፍታል፡፡ ላለፉት ዓመታት የግጭት አውድማ ሆነ የቆየችው የመን በርካታ ዜጎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን ሌሎች ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በኮሌራ ወረርሽኝ ፍዳቸውን እያዩ ነው፡፡ የተቀሩትም ርሃብ እያንዣበበባቸው በመሆኑ በሀገሪቱ ሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍራቻን አንግሷል፡፡

ለችግሮቹ ተጠያቂና መፍትሄ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ በህይወት አምልጠው ለስደት የወጡትም ቢሆን እንደተመኙት ሳይሆን የበርካቶች ህይወት መዳረሻ ሜድትራኒያን ባህር ሆኗል፡፡ በሰላም መደፍረስ ምክንያት ለሚከሰቱ ችግሮች ሰላባ ከሆኑት መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ህጻናትና ሴቶች መሆናቸው ሲታሰብ የሰላም ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደሆነ የሚያሣይ ነው፡፡

ለዘመናት የተገነቡ የስልጣኔ አሻራዎች በሰዓታት ወይንም ከዚያም ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዶጋመድ ሲሆኑ፤ በሀገር ልጆች አለመግባባት የሀገራት ሰማይ በባሩድ ጪስ ሲታጠን፤ ሰማይ ጠቀስ ቅንጡ ህንጻዎች ሲጋዩ፤ መሰረተ ልማት ሲወድም፤ በሰላም ወጥቶ መግባት አደጋ ላይ ሲወድቅ፤ ዜጎች ሰላማዊ ህይወት ፍለጋ ድንበርና ባህር ለማቋረጥ ሲሰቃዩ ሰላም በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ኃብት መሆኑንና ጥብቅና ልንቆምለት የሚገባ መሆኑን ማንም ይረዳል፡፡

የእነዚህን ሀገራት ተሞክሮ አነሳን እንጂ እኛም ሰላም ማጣት የሚያስከትለውን ጉዳትና የሰላምን ጣዕም ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ ሰላም ማጣት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመረዳት በደርግ ዘመን በቀይና ነጭ ሽብር ስም ያጣነውን ትውልድ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡ የቅርቡን ላንሳ ብዬ እንጂ በነገስታቱ ዘመንም ለእነሱ ስልጣን ሽኩቻ መስዋዕት የሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ በሁሉም የአገዛዝ ዘመናት ታዲያ እጆቻችን ወደ ጦርነት እንጂ ለልማት ባለመዘርጋታቸው ከስልጣኔ ማማ ተንከባለን ወርደን የድህነት ቅርቃር ውስጥ ገብተናል፡፡

ዛሬ ግን ያን አስቸጋሪ ወቅት አልፈን ሰላም በማስከበር ለሌሎች የምንተርፍ ህዝብ ሆነናል፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑ ችግሮችና ቅራኔዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በመቻሉና ህዝቡም የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅና ዘብ ሆኖ በመቆሙ በሀገራችን ሰላም ሊሰፍን ችሏል፡፡


የዘመናት የኋልዮሽ ጉዞ በፈጣን እድገት ድል የተመታው ከምንም በላይ በዚህ ሀገር ሰላም በመስፈኑ ነው፡፡ በሰላም ውሎ ስለማደሩና ወጥቶ ስለመመለሱ እርግጠኛ መሆን ያልቻለ ዜጋ አምራች ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ አምራች ዜጋ በሌለበት ደግሞ የኢኮኖሚ እድገት ሊታሰብ እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ የሀገራችን የርሃብና የእርዛት ተምሳሌትነት ሊፋቅ የቻለው የሰላም አየር እየተነፈስን፤ የኢትዮጵያን ከፍታ እያሰብን በጋራ በልማት ጎዳና በመትመማችን ነው፡፡

ሁሌም ቀውስ መለያው በሆነው የአፍሪቃ ቀንድ መገኘታችን በሰላማችን ላይ የሚያሣድረው ተጽእኖ ቀላል ባይሆንም ለሰላም መደፍረስ መንስኤ የሆኑ ውስጣዊ ችግሮችን በመፍታት ላይ በትኩረት በመሰራቱና ተገቢውን የውጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመከተላችን ሀገራችን የቀጠናውና የአፍሪቃ የሰላም ዘብ ልትሆን ችላለች፡፡

ዛሬ የሰፈነው ሰላም ነገም በአስተማማኝ ደረጃ የሚቀጥለው ሁሉም ለሰላም ተግቶ ሲሰራና ሰላምን የሚያደፈርሱ ነገሮችን ያለ ምህረት ሲታገል ብቻ ነው፡፡ ትናንት በአስተማማኝ ሰላም ላይ የነበሩ ሀገሮች ዛሬ ሰላማቸው ደፍርሶ ዜጎቻቸው ሰርቶ መኖርን ይቅርና በህይወት ለመቆየት እንኳ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ እናም ሰላማችንን ነቅተን መጠበቅ አለብን፡፡ 

በሀገራችን ሰላምና ሰላማዊ ሁኔታ ጠብቀን ማስቀጠል ከቻልን ወቅታዊ ችግሮቻችን ብቻ ሳይሆን ተብትቦ ከያዘን ድህነትና ኋላቀርነትም ለዘለቄታው መላቀቅ እንችላለን፡፡ ሰላም ከሆን የሀገራችንን ራዕይ እውን ማድረግ እንደምንችል መገመት አያዳግትም፡፡