Yenetube
የዎላይታ ሕዝብ የክልል ጥያቄን አስመልክቶ ከዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) የተሰጠ የአቋም መግለጫ
_______________________________________
የዎላይታ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ካቀረበ ነገ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ዓመት ይሞላል፡፡ ይህ የዎላይታ ሕዝብ ታሪካዊ እና ሕገመንግስታዊ ጥያቄ ከቀበሌ እስከ ዞን ምክር ቤት ድረስ በሰከነ መንፈስ በመወያየት አጽድቆ የላከው የክልል መዋቅር ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ ሕገወጥ መንገድ እንዳይታይ ታግዶ ቆይቷል፡፡ ይህ አካሄድ ሕገመንግስቱ ያጎናጸፈውን የሕዝቦችን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሉዓላዊ መብት አደጋ ላይ በመጣል ሀገሪቷን ለከፍተኛ የፖለቲካ እና የደህንነት ቀውስ ውስጥ የሚከት አካሄድ በመሆኑ እንዲታረም በሚሊዮኖች የሚቆጠረው የዎላይታ ሕዝብ ግንቦት 09 ቀን 2011 ዓ.ም በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ከመጠየቁም ባለፈ የኢፌዴሪ ጠ/ሚ አብይ አህመድ የዎላይታ ሕዝብን ለማነጋገር በመጡበት ወቅት ራስን በራስ የማስተዳደር የክልል መዋቅር ጥያቄውን በሰለጠ መንገድ በአንድ ድምጽ አቅርቧል:: ከዚህም በተጨማሪ ጠ/ሚንስትሩ ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም ከዎላይታ ሕዝብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የዎላይታ ሕዝብ ጥያቄ ሕገመንግስቱን ተከትሎ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ለጠ/ሚንስትሩ በዲጋሚ ተገልጾላቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ለዎላይታ ሕዝብ ሕገ-መንግሰታዊ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ የዎላይታ ዞን ም/ቤት ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የዎላይታ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገመንግስታዊ መብት መታፈኑን በማውገዝ እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ በመጥራት ጥያቄውን ለምርጫ ቦርድ በመምራት የሪፌረንደም ቀን እንዲያሳውቅ ቢጠይቅም እስከ ዛሬ ታህሳስ 09 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለሕዝባችን ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ የሰጠ መንግስታዊ አካል የለም፡፡ ይባስ ብሎ ሕገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄውን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየጠየቀ የቆየውን የዎላይታ ሕዝብ ፍርሃት እና የሥነ-ልቦናዊ ጫና ውስጥ ለመክተት ታቅዶ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የመከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሰማራ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ሁኔታ ሕዝባችን እያደረገ ያለውን ሰላማዊ ትግል እና አጠቃላይ የሀገሪቷን የፖለቲካዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲያሳይ የቆየውን ጨዋነት እና ትዕግስት በመፈታተን የትግሉን አቅጣጫ በማሳት በአካባቢው ያለመረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ የዎላይታ ሕዝብን ሕገመንግስታዊ የመብት ጥያቄውን የማፈን ሴራ እንደሆነ ንቅናቄያችን ይገነዘባል:: ይህ ሁኔታ ወደ ግጭት ቢያመራ የዎላይታ ሕዝብን ሕገመንግስታዊ እና ሰላማዊ ጥያቄ ኢ-ሕገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ያፈኑ አካላት ተጠያቂ እንደሆኑ ዎብን አጥብቆ ይገልጻል::
የዎላይታ ሕዝብ በ371 ቀበሌያት በሰከነ መንገድ ለጠየቀው የዘመናት ራሱን በራሱ የማስተዳደር ታሪካዊ እና ሕገመንግስታዊ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ አካል መንግስታዊ አካል መጥፋቱን እና በሕገወጥ መንገድ መታፈኑ የሕዝቦችን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሕገመንግስታዊ ዋስትና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ንቅናቄያችን በጥብቅ ያወግዛል፡፡
በመሆኑም በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 47 የተቀመጠው የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ነገ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም የሚጠናቀቅ በመሆኑ እና የዎላይታ ሕዝብ ላለፈው አንድ ዓመት ባደረገው ትግል የራሱን ዕድል በራሱ የወሰነ በግልጽ በአደባባይ የገለጸ በመሆኑ የሚመለከተው የመንግስት አካል ሕጋዊ ሂደቶችን አልፎ በአስቸኳይ እውቅና እንዲሰጥ ንቅናቄያችን አጥብቆ ያሳስባል፡፡
የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን)
ታህሳስ 09 2012 ዓ.ም
ዎላይታ ሶዶ
@Yenetube @FikerAssefa