Yenetube
በዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ የነበረው ችግር እስካሁንም መፍትሔ ባለማግኘቱ ወደ ግቢያቸው መመለስ እንዳልቻሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
የችግሩን ምንጭ ለማወቅ እና እርምጃ ለመውሰድ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 09/2012ዓ.ም (አብመድ) የመቱ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በስልክ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ዩኒቨርሲቲያቸውን ለቀው ወጥተዋል፤ ችግሩም እስካሁን መፍትሔ ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው መመለስ አልቻሉም፡፡ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደነገሩን 3 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች በአዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር በተለያዩ ተቋማት ተጠልለው ይገኛሉ፤ የሌሎች ክልል ተማሪዎች ደግሞ ትምህርት ከጀመሩ ሦስት ሳምንታት አስቆጥረዋል፡፡ ተማሪዎቹ ለደኅንነታቸው በመስጋት እንደወጡ ነው የገለጹት፡፡
ችግሩ እንዲፈታ ለሚመለከተው አካል ቢጠይቁም ‹‹መማር ስላልፈለጋችሁ እንጅ ‹‹አሁን ላይ የፀጥታ ችግር የለም›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
በመቱ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሕዝብ እና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ኦልቀባ አሰፋ እንደገለጹት ደግሞ ከዩኒቨርሲቲው የወጡት ተማሪዎች ቁጥር 3ሺህ ሳይሆኑ 1 ሺህ 560 ናቸው፡፡ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በተደጋጋሚ ውይይት ቢያደረጉም ተማሪዎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መታወቂያቸውን መልሰው እንደወጡም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሴኔትም ሕዳር 22 እና 23/2012 ዓ.ም ፈቃደኛ የሆኑትን የዳግም ምዝገባ አድርጎ ትምህርት መጀመሩንና ፈቃደኛ ያልሆኑት ደግሞ ወደ ፈለጉበት እንደሄዱ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡ ይሁን እንጂ መታወቂያቸውን አስረክበው ከወጡት 1ሺህ 560 ተማሪዎች ውስጥ አስከ ባለፈው ዓርብ ድረስ 387 ተማሪዎች መመለሳቸውን እና በዚህ ሳምንትም የተመለሱ እንዳሉ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡ አሁንም ተጸጽተው የሚመለሱ ተማሪዎች ካሉ ዩኒቨርሲቲው ደኅንነታቸውን አስጠብቆ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያስቀጥል እንደሆነም ነው የተናሩት፤ ከዚህ በላይ ዩኒቨርሲቲው አማራጭ መፍትሔ እንደሌለውም ነው ዳይሬክተሩ ያስታወቁት፡፡
የጎንደር የኒቨርሲቲ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች እንደገለጹት ደግሞ ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውጭ በሌሎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ከተቋረጠ ሁለተኛ ሳምንት አስቆጥሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ጥሪ ቢያደርግም በስጋት እስከ ዛሬ ትምህርት መጀመር እንዳልቻሉ ነው ያነጋገርናቸው ተማሪዎች የገለጹት፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት መምህር መርሻ ጫኔ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት ተማሪዎች የሚያነሱት ጥያቄ የዩኒቨርሲቲው አስተዳድራዊ ችግር ሳይሆን በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከተፈጠረው ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲ መፍታት አይችልም፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ጥያቄውን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በየጊዜው ቢያመለክትም እስከ ዛሬ በዩኒቨርሲቲው በአካል ተገኝቶ ያወያየ አካል እንደሌለ ነው ፕሮፌሰር መርሻ የገለጹት፡፡ ለችግሩ ሀገራዊ መፍትሔ ካልተሰጠው በስተቀር በዩኒቨርሲቲው አቅም መፍታት እንደማይቻልም ፕሮፌሰር መርሻ ገልጸዋል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ደቻሳ ጉሩሙ እንደገለጹት ደግሞ በሀገሪቱ በተወሰኑ ክልሎች ግጭቶች ከተነሱ ጀምሮ ተማሪዎች ወደ መማር ማስተማሩ ሂደት እንዲመለሱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሠራ ይገኛል፡፡ በወልድያ፣ መዳ ዋላቡ እና መቱ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ለሁለት ሳምንት ያህል ውይይት ተደርጓል፡፡
‹‹ወደ መጨረሻ አካባቢ ወደ ግጭት ከገቡት ዩኒቨርሰቲዎች ውጭ በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መደበኛ መማር ማስተማሩ ተመልሰዋል›› ያሉት አቶ ደቻሳ ተማሪዎች የሚያነሱትን የግቢ ጥበቃ እና የሠላም አስተማማኝነት ችግር ለመፍታት አሁንም እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት፡፡
የዩኒቨርሲቲዎችን ሠላም በጥበቃ ብቻ ማረጋገጥ ባይቻልም የፌደራል ፖሊስ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲገባ መደረጉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፤ ተማሪዎቹ የራሳቸውን ሠላም በመጠበቅ እንዲያግዙም ጠይቀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚመለሱ ተማሪዎች የማካካሻ ጊዜ በመጠቀም ትምህርታቸውን እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ዘግይተው ለሚመለሱትም ዩኒቨርሲቲዎች ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም የችግሩን ምንጭ ለማወቅ እና እርምጃ ለመውሰድ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በሚገኙ 20 ዩኒቨርሲቲዎች አራት አባላት ያሉት ቡድን ከክልሎች እና ከቦርድ መሪዎች ጋር በመቀናጀት ለመሥራት ስምሪት መሰጠቱንም አመልክተዋል፡፡
ተማሪዎችም አሁን የተፈጠረውን ሠላም በመጠቀም ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እንዲመለሱም አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዎች ችግር በማኅበረሰቡ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስላለው ማኅበረሰቡም የአካባቢውን ሠላም የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ደቻሳ እንደገለጹት መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እየሠራ ባለበት ወቅት በተለያዩ ውጫዊ እና ውስጣዊ አካላት ተፅዕኖ ተደናግረው ወደ ትምህርታቸው የማይመለሱ ተማሪዎች ካሉ በራሳቸው ላይ እንደወሰኑ ተቆጥሮ ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን የሚያስቀጥሉ ይሆናል፡፡
Via:- AMMA
@Yenetube @Fikerassefa