Yenetube
ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሙሉ
(ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው መማክርት ጉባኤ (Senate) የተላለፉ ውሳኔዎች)
እንደሚታወቀው በዩኒቨርሲቲያችን በደረሰው የፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ እንደነበረ ይታወሳል፡፡
የዩኒቨርሲቲያችን መማክርት ጉባኤ (senate) ሀዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ተማሪዎች ዓርብ ህዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለስ ትምህርት እንዲጀምሩ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በተወሰኑ የትምህርት ክፍሎች የመማር ማስተማር ሥራ የተጀመረ ቢሆንም አሁንም እስከ ዛሬ ህዳር 18 ቀን 2012 በትምህርት ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ተማሪዎች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህንንም በመረዳት የዩኒቨርሲቲው መማክርት ጉባኤ በዛሬዉ ዕለት ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም በድጋሚ ባካሄደዉ አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትን ዉሳኔዎች ወስኗል፡፡
- በአሁኑ ጊዜ የዩኒቨርሲቲዉን ሰላም ለማስጠበቅ ከዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ፤ ከድሬዳዋ አስተዳደር፤ አካባቢዉ ማህበረሰብ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ ያለዉ አመርቂ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፡፡
- በትምህርት ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ተማሪዎች እስከ ማክሰኞ ህዳር 23 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሚመለከታቸው የትምህርት ክፍሎች ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ፤ ነገር ግን ከተጠቀሰው ጊዜ ውጪ ለሚመጡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነት እንደማይወስድ ተረድተው ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ፤ አብላጫ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ወደ ግቢ መመለሳቸው ሲረጋገጥና ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የሰላም ጉባዔ እንዲደረግ
- በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ላይ በአሉታዊ መልኩ ተሳታፊ የነበሩ የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አካላት (ተማሪዎችና ሰራተኞች) ላይ እንደየተሳትፎቸው በዩኒቨርሲቲው ደንብ መሰረት ጥብቅ ርምጃ እንዲወሰድ፡፡ እንዲሁም በሌላ ደረቅ ወንጀል የተጠረጠሩ ሃገሪቷ ላይ ባለው ህግ አግባብ በሚመለከተዉ መንግስታዊ አካል ጉዳያቸው እንዲታይ፡፡ ነገር ግን ጥፋተኞችን ለይቶ ተገቢውን ቅጣት ወይም ፍርድ እንዲተላለፍ የማድረጉ ስራ የራሱ ጊዜ የሚወስድና በሂደት የሚፈጸም መሆኑን ተማሪዎች እንዲረዱንና ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ግን በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸዉን እየተከታተሉ እንዲጠብቁ፡፡
- በዚህ ረገድ ጥፋተኞችን የመለየት፤ የመመርመርና ለዉሳኔ የማቅረቡን ስራ በተለየየ ደረጃ ላይ ያሉ የሚመለከታቸዉ የዩኒቨረሲቲዉ ስራ ክፍሎች ስራቸዉን ባስቸኳይ ሰርተዉ እንዲያቀርቡ የዩኒቨርሲቲዉ መማክርት ጉባዔ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
- በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዉ የተጠናከረ የዲሲፕሊን እርምጃ ለመዉሰድ በሚያደርገዉ ጥረት ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲዉ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የራሳቸዉን በጎ አስተዋፅኦ ከልብ በመነጨ ሃላፊነት ስሜት ሃላፊነታቸዉንና የዜግነት ግዴታቸዉን እንዲወጡ ሲል በዚህ አጋጣሚ ሴኔቱ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡
- በዩኒቨርሲቲያችን ተፈጥሮ በነበረዉ የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ህይወቱ ያለፈው ተማሪያችን አበባየሁ አጅቤን ለማሰብ የሚያስችል የሻማ ማብራት ፕሮግራም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲደረግ፡፡
- እንዲሁም ከሁሉም ዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ የተወጣጡ አካላት ያሉበት ቡድን በተማሪ አበባየሁ አጅቤ ቤተሰቦች ቤት ተገኝቶ ቤተሰቡን የማጽናናት ፕሮግራም እንዲከናወን፡፡
- በተፈጠረው ችግር ምክንያት ወደ ቤተሰብ ለሄዱ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ቢያንስ ከመሃል አገር አካባቢ ማለትም ከአዲስ አበባ እስከ ድሬዳዋ አገልግሎት የሚሰጥ ትራንፓርት እንዲያዘጋጅ፡፡
በመሆኑም የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ትምህርት ገበታችሁ እንድትመለሱ እንጠይቃለን፡፡
ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ
ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም
@Yenetube @Fikerassefa