Yenetube

Yenetube


ህዝበ ውሳኔውን መሠረት ያደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችን የገመገመ ጉባኤ ተካሄደ፡፡

የሲዳማ ብሄር ክልል ሆኖ የመደራጀትን ጥያቄ ተከትሎ በመጪው ወር በመላው የሲዳማ ዞን በሚካሄደው ህዝበ ውሣኔ ላይ የዞኑ ዋና ከተማ በሆነችው የሀዋሳ ከተማ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ሲካሄዱ የነበሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በከተማው ከፍተኛ አመራር አባላት ተገምግመዋል፡፡

ጉባኤው ሌሎች የመልካም አስተዳደር ስራዎችንም የገመገመ ሲሆን በዚህና በሪፈረንደም ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መልካም የሚባሉ አፈፃፀም እንደተመዘገቡ ተመላክቷል፡፡

በጉባኤው የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ የስምንቱም ክ/ከተሞች እቅድ ክንውን ሪፖርት በየክ/ከተማ አስተዳዳሪዎች የቀረበ ሲሆን በዚህም ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

ከምርጫ ቅስቀሳ ስራ ጀምሮ የምርጫ ጣቢያ ዝግጅት፣ የምርጫ ጣቢያ ግብዓቶችን ከማሟላት አንፃር እንዲሁም ደግሞ ህዝበ ውሣኔው በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ በእስካሁኑ ሂደት የተሠሩ ስራዎች በጉባኤው በቀረቡት ሪፖርቶች የተካተቱ ሲሆን በተለይ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በአብዛኛዎቹ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መልካም አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደተቻለ ጉባኤው አመላክቷል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በስምንቱም ከ/ከተሞች የምርጫ ጣቢያዎች ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን እንደ ወንበር ጠረጴዛ፣ ማብራት የመሳሰሉት ግብዓቶችም እየተሟሉ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩልም በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ አንዳንድ የተሣሣቱ አመለካከቶችን የማስተካከል ስራም ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ህዝበ ውሳኔውን ተከትሎ በህብረተሰቡ መሀል አልፎ አልፎ የስጋት ሁኔታዎች የሚስተዋሉ ሲሆን ከነዋሪዎች ጋር በተለያዩ ጊዜያት በተከናወኑ የውይይት መድረኮች እነዚህን አመለካከቶች የማስተካከል ሰራ ተሰርቷዋል፡፡

የብሄሩ ክልል የመሆን ጥያቄ ከብሔሩ ተወላጅ ውጪ የሆኑትን የሚገፋ ሣይሆን ይልቁንም አብሮነትንና ፍቅር እንዲሁም መቻቻልን በሰፊው የሚያጎለብት መሆኑን በተለያዩ መድረኮች በማስረዳት ከነዋሪዎቹ ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል፡፡

ፀትታውን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ስጋቶችም እስከታች መንደር ድረስ ህብረተሠቡን ባቀናጀ መልኩ ተለይተው የመከላከል ስራ በከፍተኛ ደረጃ በ8ቱም ክ/ከተሞች ሲከናወን ቆይቷል፡፡

ይህም ሪፈረንደሙ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጉባኤው አስምሮበታል፡፡

Via:- Hawassa city administration

@Yenetube @FikerAssefa

Report Page