Wolaita Times

Wolaita Times

Tikvah Ethiopia


"ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ" ከመንግስት አካል ይደርስብኛል ባለው ጫና ሥራ ማቋረጡን ገለጸ።

በኢትዮጲያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በሚዲያ ሥራ ለመሰማራት ሕጋዊ ፈቃድ ወስዶ በዞናዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የነበረው "ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ" በደረሰበት ጫና ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ሥራ ማቆሙን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የላከው መረጃ ያሳያል።

የሚዲያው መስራች ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ በሥራው በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መዳረጉን ጠቅሶ በቅርቡም ከቀን 19/03/2015 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ላይ ጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል በሚል ተጠርጥሮ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደነበር ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ / Source: Natenael Gecho Betalo FB page

ጋዜጠኛው በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ከቆየበት በትናንትናው ዕለት 28/03/2015 ዓ.ም በ30 ሺህ ብር ዋስትና መለቀቁንም ተናግሯል። ተመሳሳይ ጫና በመኖሩና ሌሎች የሚዲያው ጋዜጠኞችም ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው በመሆኑ ሥራው ተቋርጦ ቢሮው መዘጋቱን አክሎ ገልጿል፡፡

ይህንን ጫና ሚዲያው ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ጭምር ማስታወቁን የገለጸ ቢሆንም ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱን ጋዜጠኛ ናትናኤል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።

ሚዲያው በክልልና በዞኑ እንደ ህጋዊ ሚዲያ ለመስራት የሚያስችል መረጃ የማግኘት ነጻነት፣ የጋዜጠኞች የአካል ነጻነት፣ በተለይም በተለያዩ መድረኮች የመገኘት መብቱ በዞኑና በክልሉ መንግስት በተደራጀ ሁኔታ የሚደረግበት ክልከላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱ ፈተና እንደሆኑበት ነው የገለጸው።

ሥራ ማቆሙን ባስታወቀበት የፌስቡክ ልጥፉም በአከባቢው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማንሳትና መጠየቅ፣ የመንግስት አሰራር ክፍተቶችን መናገርና መተቸት "እንደ ጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ህዝብን በመንግስት ላይ ማነሳሳት" የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ከህግ አካሄድ ውጪ ወደ የሚያሳስርበት ደረጃ ደርሷል ብሏል።

Source: wolaita Times

ጋዜጠኛ ናትናኤል፥ "አማራጭ የሀሳብ ልዩነት ያላቸውን ህብረተሰብ ክፍሎችን አሳታፊ በሆነ መንገድ ዘገባ ለመስራት የመረጃ ነጻነት በአከባቢው ባለመኖሩ እንዲሁም የሀሳብ ልዩነት የሚያራምዱ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ የፓለቲካ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ማሳደድ በሰፊው በመስተዋሉ ለሥራ ማቆሙ ምክንያት ነው" ሲል ጠቅሷል።

ሚዲያው ይህንን ውሳኔ ሲያሳልፍ ውሳኔው ለፌደራል መንግስትና ለዓለም ለማሳየትና ለማሰማት ማሳያ እንዲሆን በሚል ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት ለማቆም መወሰኑን አስታውቋል።

Report Page