What happened in Tigray? Via BBC

What happened in Tigray? Via BBC


መነሻ

ለዚህ ሁሉ እንደመነሻ የሚጠቀሰው የወረዳ ማዕከል እንሁን በሚል የሁለት ቀበሌ ነዋሪዎች ያነሱት ጥያቄ ነው። ጥያቄ የቀረበባቸው ቀበሌዎች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የሚገኘው ማይ ሓንሰ እና በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ የሚገኘው ባሕሪ ሓፀይ መሆናቸውን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።


ሽረ አካባቢ የምትገኘው የማይሃንሰን ሕዝባዊ ቅዋሜ ከወረዳነት ጥያቄ በዘለለ፥ በስፍራው በተመደቡ አስተዳዳሪዎች ቅር መሰኘትንም ያካትታል ይላሉ የተቃዋሚ ፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ። በደደቢት እና አደጋ ሕብረትም ተመሳሳይ ድርብ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ነው አቶ አንዶም የሚናገሩት።


ከጥቂት ዓመታት በፊት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ ‘ተሃድሶ’ ባካሄደበት ወቅት፤ በትግራይ የአስተዳደር መዋቅር ለውጥ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።


ይህም አስተዳደራዊ ለውጥ ያልተማከለ አስተዳደር ለመፍጠር፣ ሥልጣንን በዋናነት ወደ ወረዳዎችና ጣቢያዎች ማውረድ የሚል ነበር። በዚህም መሠረት አዲስ የወረዳ እና የጣቢያ አደረጃጀት እንዲኖር ተደረጓል።


የአንድ ወረዳ ማዕከል የሚሆነው ቀበሌ የትኛው ይሁን? የሚለው ግን በአንዳንድ አካባቢዎች አወዛጋቢ ጥያቄን ማስከተሉንና አሁን ለተፈጠረው ነገር መነሻ እንደሆነ ይነገራል።


በሰሜን ምዕራብ ትግራይና በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ የሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ጥያቄ ያቀረቡትም እኛ የወረዳችን ማዕከል መሆን አለብን ብለው ነው።


በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የወረዳ ምክር ቤት የወረዳው ማዕከል ብሎ የወሰነውን ቀበሌ ያልተቀበሉ የሌላ ቀበሌ ነዋሪዎች መንገድ ዘግተው መኪና አናሳልፍም ብለው ለተቃውሞ መውጣታቸውን ከዘጋቢያችን ለመረዳት ችለናል።


በአካባቢው አዲስ የተዋቀረ አስገደ የሚባል ወረዳ አለ። በወረዳው ከሚገኙ ሕፃጽ፣ ዕዳጋ ሕብረት፣ ክሳድ ጋባ እና ማይ ሓንሰ የተባሉ ቀበሌዎች ለወረዳው ማዕከልነት ተወዳድረው ነበር።


የወረዳው ምክር ቤት ክሳድጋባ ማዕከል እንድትሆን ውሳኔ ቢያስተላለፍም፤ የማይ ሓንሰ ነዋሪዎች ውሳኔውን አልተቀበሉም።



ተቃውሞና መንገድ መዝጋት


በሰሜን ምዕራብ ዞን የማይ ሓንሰ ነዋሪዎች፡መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ ማሰማት ከጀመሩ 11 ቀናት አልፎባቸዋል።


ነዋሪዎቹ የዞኑ አተዳዳር እና የፀጥታ አካላት ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም የሚሉ ሲሆን ጥያቄያቸው ከክልሉ መንግሥት መልስ እስካላገኘ ድረስ ወደ ቤታቸው እንደማይመለሱ ይናገራሉ።


የማይ ሓንሰ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብርሃለይ ገብረእየሱስ "የወረዳው አስተዳዳሪዎች ለራሳቸው ወደ ሽረ እንዲቀርባቸው ክሳድ ጋባ ወረዳው ትሁን አሉ። ህዝቡ ደግሞ የተሰጠንን ወረዳ የመሆን መብት ለምን እንከለከላለን በማለት ነው የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄደ ያለው" በማለት ገልፀዋል።


ሌላኛዋ የማይሓንሰ ነዋሪ ወይዘሮ ለተብርሐን ደግሞ "ውሳኔው በጉቦ እና በሙስና በድብብቆሽ ተደረገ ነገር ነው" በሚል ነዋሪው ለተቃውሞ እንደተነሳ ይጠቅሳሉ።


የኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ ባለበት በዚህ ወቅት ለተቃውሞ መውጣታቸውን በሚመለከትም ሲናገሩ "ሕዝቡ ስለተቸገረ እንጂ ወዶ አይደለም። ሞትም ቢሆን እንሙት። ፍትህ ማጣትም ሞት ነው፤ በኮሮና መሞትም ሞት ነው" ብለዋል።


የአስገደ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብቶም አበራ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የአካባቢው ወጣቶች ለሰባት ቀናት ያህል መንገድ ዘግተው ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።


“የወረዳው ምክር ቤት የወሰነውን የማይቀበሉ ከሆነ የክልሉን ኃላፊዎች ማነጋገር እንዳለባቸው ገልጸንላቸዋል። ቢሆንም ኃላፊዎች መጥተው ካላናገሩን እኛ ወደ ክልል አንሄድም ብለዋል” ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል።


የወረዳው አስተዳደር የአገር ሽማግሌና የሐይማኖት መሪዎች በማነጋገር፤ ወጣቶቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲግባቡ ለማድረግ እየጣሩ መሆኑንም አክለዋል።


"ጥያቄያቸው በሰላማዊ እና ዲሞክራስያዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርቡ እየሰራን ነው" የሚሉት አቶ ሃብቶም፡ መንገድ መዝጋት ምዝጋት ግን ህጋዊ እንዳልሆነ እና እህም ለህዝቡ በግልፅ እንዲነገረው ተደርጓል በማለት ስለሁኔታው አስረድቷል።


'ተቃውሞውን በትኑ ወይ ትጥቅ ፍቱ'

የማይ ሓንሰ ነዋሪዎች ግን የዞን አስተዳደር እና ፖሊስ ጥያቄያቸውን ከመስማት ይልቅ እኛ ያልናችሁ ስሙ በማለት መፍትሄ እንዳልሰጣቸው ይገልፃሉ። የዞኑ ፖሊስም፡ ለአካባቢው ሚሊሻዎችም መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ እያሰማ ያለውን ሕዝብ በመበተን መንገዱ እንደከፍቱ አልያም ሚልሻዎቹ ትጥቃቸው እንዲፈቱ ጫና በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ገልፀውሉናል።


ወይዘሮ ለተብርሃን "ሚሊሻዎቹ፡ እኛ የህዝብ ነን፤ እናንተ አላስታጠቃችኑም። ህዝብ ያለን እንጂ እናንተ ያለቹን አንሰመማም። ከፈለጋቹ ወደ ህዝቡ ቅረቡ እና እንረዳዳ ሲሉዋቸው ግዜ፡ በሉ ፈርሙ ሲሉዋቸው ህዝቡ ይህን ስለአወቀ ውጡልን በማለት አባረርናቸው" በማለት በሚሊሻዎቹ እየተፈጠረ ያለውን ጫና ገልፀውልናል።


በማይ ሓንሰ ሚሊሻ የሆነት አቶ ገብረክርስቶስ ገብረኣረጋዊም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ተሰባስቦ ተቃውሞ ማሰማት ጥሩ እንዳልሆነ ሕዝቡን ለማስረዳት እንደሞከሩ ገልጸው "የዞኑ አስተዳዳሪዎች ከኮሮና የሚሰብሱ እንጂ የሚሻሉ አይደሉም" በማለት ሰሚ አለማግኘታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።


"የዞኑ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝቡን የማትበትኑ ከሆነ ትጥቃችሁን እንድትፈቱ ብሎናል። እኛም ከእናንተ ጋር ትውውቅ የለንም ሕዝቡ ነው ያስታጠቀን፤ ሕዝብ ትጥቃች እንድትፈቱ ካለን እንፈታለን። ካልሆነ ግን ለእናንተ ብለን ትጥቅ አንፈታም ብለናቸዋል" በማለት ህዝቡ እያነሳ ያለው ጥያቄ ትክክል እንደሆነ ይናገራሉ።


ወጀራት

በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወጀራትና ሕንጣሎ የተባሉ ከዚህ ቀደም አንድ የነበሩ፤ አሁን ግን ለሁለት የተከፈሉ ወረዳዎች አሉ። በወጀራት ወረዳ ከሚገኙት ባሕሪ ሓጸይ እና ዓዲ ቀይሕ የተባሉ ቦታዎች መካከል የወረዳ ማዕከል መሆን ያለበት ባህረሀፀይ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ጥያቄ አቅርበዋል።


የአረናው አባል አቶ አንዶም እንደሚሉት የወረዳነት ጥያቄ የተነሳበት የወጀራት ሕዝባዊ ተቃውሞ አራተኛ ቀኑን ይዟል። እዚህም አአካባቢውን የሚያስተዳድሩት 'የዞን እና የክልል መልዕክተኞች ናቸው እንጅ እኛን አይወክሉንም' በሚለው ቅሬታ የተቃውሞው አካል ሆኗል ይላሉ። "ጥያቄው [ወረዳነት] ተፈቅዶልን እያለ፤ እንደገና ተከልክለናል የሚል ነው።"


የቀድሞው የወጀራት ወረዳ ማዕከል የነበረችው ጣቢያ ባሕሪ ሓፀይ ነዋሪዎቿ፤ ባሕሪ ሓፀይ የወረዳው ማዕከል ስለነበረች ከጣቢያ ዓዲ ቀይሕ ጋር መወዳደር የለባትም በማለት ይጠይቃሉ።


ይሁን እንጂ የወጀራት ምክር ቤት የወረዳዋ ማዕከል ማን ትሁን? በሚል ውሳኔ እንዳላሳለፈ የወረዳው አስተዳደር አቶ ዳርጌ ፀጋይ ለቢቢሲ ገልፀዋል።


በጣብያ ባሕሪ ሓፀይ ሰላዊ ሰልፍ ከማካሄድ ጥያቄ ከማቅረብ ውጪ በወጣቶቹ ላይ የተወሰደ እርምጃ እንደሌለ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።


"ወጣቶቹ ሥርዓት ያላቸው ናቸው። እስከአሁንም በአካባቢው የደረሰ ችግር የለም። አሁን ከእነሱ ጋር ንግግር ጀምረናል። መንግሥት ጥያቄያችንን ሰምቶ የቀድሞ ወረዳችን ይመልስልን ነው የሚሉት" ብለዋል።


የወረዳው ምክር ቤት የትኛው ወረዳ ማዕከል እንደሚሆን ውሳኔውን ባያስተላልፍም፤ የባህረሀፀይ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት የወረዳው ማዕከል ስለነበርን ከሌሎች ጋር መወዳደር አንፈልግም ብለዋል።


በቅርቡ ያጋጠሙ ክስተቶች

በክልሉ መዲና መቀለ ከሳምንት በፊት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የወጣውን ደንብ ተላልፈዋል ከተባሉ ወጣቶች ጋር በተከሰተ አለመግባባት የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱ እታወሳል።


አቶ አንዶም እንደሚሉት በጸጥታ ኃይል አባላት በተተኮሰ ጥይት ከሞተው ወጣት በተጨማሪ ሦስት ሰዎች ከቆሰሉ በኋላ "በአካካቢ ባሉት 05፣ 06 በሚባሉ ቀበሌዎችና አይደር የሚባለ ሠፈር ተቃውሞዎች ተቀስቅሰው ነበር" ብለዋል።


አቶ አንዶም ጨምረውም በወቅቱ በጥይት ከተመቱ ሦስት ግለሰቦች መካከል የአንደኛው ሕይወት በቅርቡ ማለፉን ተናግረዋል።


ተቃውሞውም በየዕለቱ ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት አንስቶ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መፋጠጥን፣ አንዲሁም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን የጨመረ እንደነበረ አመልክተዋል።


አቶ አምዶም ከመቀሌው ክስተት ውጪ ተቃውሞዎችን ለማፈን ወይም ለመበተን በሚል በፀጥታ ኃይሎች ወይንም በመንግሥት የተወሰደ የኃይል እርምጃ እስካሁን እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።


"የኃይል እርምጃ የለም፤ ምላሽም ግን የለም። እንዲያውም የክልሉ የኮምኒኬሽን ፅህፈት ቤት ምንም ዓይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴ የለም የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር። የመካድ [አዝማሚያ] ነው ያለው። መፍትሔ የማበጀት ተግባር የለም" ብለዋል።

Via BBC

Report Page