Wegagen Bank
Advertisementወጋገን ባንክ ዓለም አቀፍ የቅድመ ክፍያ ቪዛ ካርድ አገልግሎት ይፋ አደረገ
(መቐለ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም፡)

ወጋገን ባንክ ከቪዛ ኢንኮርፖሬትድ ጋር በመተባበር ወደ ውጪ ሀገር ጉዞ ለሚያደርጉ የባንኩ ደንበኞች፣ የኤምባሲዎች እና የዓለም አቀፍ ድርጅት ሰራተኞች ጥሬ ገንዘብ መያዝ ሳያስፈልጋቸው በየትኛውም የዓለም ክፍል ክፍያ መፈፀም የሚያስችላቸውን ዓለም አቀፍ የቅድመ ክፍያ ቪዛ ካርድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በመቐለ ከተማ በፕላኔት ሆቴል ባካሄደው ይፋዊ የአገልግሎት ማብሰሪያ ስነስርዓት ላይ አስታወቀ፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የክብር እንግዳ በመሆን በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳድር የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አፅብሃ ገ/እግዛብሔር የተገኙ ሲሆን በዕለቱም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እና ከፍተኛ የስራ አመራር አባላት፣ የቪዛ ኢንኮርፖሬትድ የሥራ ኃላፊዎች፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች፣ የባንኩ ደንበኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት ዶ/ር አፅብሃ ገ/እግዛብሔር በክልሉ የቱሪዝም እና ኢንቬስትመንት አማራጮች ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ሰፊ ተሳትፎ አንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበው ወጋገን ባንክ ያቀረበውን ዓለም አቀፍ የቅድመ ክፍያ ቪዛ ካርድ አገልግሎት እንዲሁም በዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጎልብቶ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በይፋዊ ዓለም አቀፍ የቅድመ ክፍያ ቪዛ ካርድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባንኩ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ወጋገን ባንክ ከቪዛ ኢንኮርፖሬትድ ጋር በመተባበር ያስጀመረው ይህ አገልግሎት የባንኩ ደንበኞች ወደ ውጭ ሀገር በሚጓዙበት ወቅት ምንም ዓይነት የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘብ መያዝ ሳያስፈልጋቸው ባንኩ ያዘጋጀላቸውን የዓለም አቀፍ የቪዛ ካርድ በመጠቀም በየትኛውም የዓለም ሀገራት በሚገኙ የኤቲኤም እና የክፍያ መፈፀሚያ (POS) ማሽኖች ገንዘብ ማስተላለፍ እና ክፍያን መፈፀም የሚያስችል መሆኑ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አገልግሎቱ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እየተስፋፋ በመጣው ኢ-ኮሜርስ አማካኝነት ግብይት መፈፀም እንዲሁም በውጪ ሃገር ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጲያውያን ዳያስፖራዎች ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻችው ተጨማሪ የዲጂታል ኃዋላ አማራጭ በመሆን ከየትኛውም ቦታ እና በማንኛውም ሰዓት ደህንነነቱ በተጠበቀ መንገድ በፍጥነት ገንዘብ መላክ እንደሚያስችል አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
በአገልግሎት ማስጅመሪያ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የቪዛ ኢንኮርፖሬትድ ካንትሪ ማናጀር አቶ ያሬድ እንዳለ በበኩላቸው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለኢኮኖሚ እድገት አንቀሳቃሽ እንደሚሆን ጠቅሰው ቪዛ ኢንኮርፖሬትድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ10 የአፍሪካ አገሮች ላይ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የፋይናንስ ሴክተር ላይ ከፍተኛ እምርታ ለማምጣት የተለያዩ አካታች፣ ፍታሃዊ እና ዘላቂ ፕሮጀክቶች ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ያሬድ አክለውም የቪዛ ካርድ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነት በማስፋት እና ምቹ ዓለምአቀፍ የክፍያ አማራጮችን በማቅረብ ግለሰቦች በመደበኛው ኢኮኖሚ ውስጥ በተሟላ መልኩ እንዲሳተፉ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም ቪዛ ኢንኮርፖሬትድ ከወጋገን ባንክ ጋር በመሆን የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በ16 ባለሀብቶች በብር 30 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም የባንክ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉ ከብር 5 ቢሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታሉ ከብር 10 ቢሊዮን አድጓል፡፡
ወጋገን ባንክ በመላው ሀገሪቱ በከፈታቸው 438 ቅርንጫፎቹ ከሚሰጠው መደበኛ እና ወጋገን አማና የተሰኘ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ፤ በ385 የኤቲኤም እና 430 የክፍያ መፈፀሚያ (ፓስ) ማሽኖች፣ በ4,800 ወኪሎች እንዲሁም የኢንተርኔት እና ሞባይል ባንኪንግ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ወጋገን ባንክ በቅርቡ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሳይሆኑ የቆዩ በጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ እና መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ እፎይታ የተሰኘ የዲጂታል ብድር አገልግሎት መተግበሪያ በይፋ ማስተዋወቁ ይታወሳል፡፡
ወጋገን ባንክ