VOA

VOA


" ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም " - ነዋሪዎች


የአንድ የባህር ዳር ነዋሪ ባለፈው ሳምንት ጤፍ ለመግዛት ወደ ገቢያ በወጡበት ወቅት ከወር በፊት በ10 ሺህ ብር የገዙት ጤት በሺዎች ብር ጨምሮ እንዳገኙት ገልጸዋል።


እኚሁ ነዋሪ ከ6 እና 7 ወር በፊት አንድ ኩንታ ጤፍ 6,700 ብር ገደማ መግዛታቸውን አስታውሰው አሁን 13,000 ብር መባሉን ገልጸዋል።


" በጣም ደንግጫለሁ ፤ ከእጥፍ በላይ ነው የጨመረው ዝቅተኛው ጤፍ 11 ሺህ 500 እና 12 ሺህ 500 ነው የሚባለው እኔ የገዛሁት 13 ሺህ ብር ነው " ብለዋል።


ለምን በዚህ ልክ እንደጨመረ ነጋዴዎችን ጠይቀው የተሰጣቸው ምላሽ " ከትራንስፖርት አንፃር አቅርቦት የለም ፣ በየቀኑ መንገድ ይዘጋል " የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።


ከጤፍ በተጨማሪ ሽንኩርት አንድ ኪሎ 110 ብር እንደገዙ አመልክተዋል። ቲማቲምን ጨምሮ ሌሎችም የዕለት ዕለት ግዢዎች ላይ ዋጋ ጨምሯል ብለዋል።


" 13 ሺህ ብር ጤፍ ተገዝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻል አይገባኝም ፤ በተለይ መካከለኛ እና ዝቅተኛ እንደኔ አይነት ገቢ ያላቸው የወር ደሞዝተኞች መኖር የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። " ሲሉ አክለዋል።


ይህንን እየፈጠረ ያለው አንደኛው ወታቂው የመንገድ መዘጋት ነው ፤ በተጨማሪ ስግብግብ ነጋዴዎች ወቅቱን ተጠቅመው ሰው እንደተቸገረ አውቀው በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ በመሆኑ ነው ብለዋል።


አማራ ክልል በተለይ ምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም ጤፍ አምራች ቢሆንም የአካባቢው ነዋሪ በዚህ ዋጋ ለመሸመት መገደዱ አስደንጋጭ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህ ምክንያት እየሆነ ያለው ግጭት በፍጥነት ካልቆመ ህዝቡ በኑሮ ይጎዳል ብለዋል።


አንድ ስማቸው እንዲገልፅ ያልፈለጉ ከምዕራብ ጎጃም አዴት እና ጎንጂ ቆለላ ጤፍ አምራች አካባቢዎች ጤፍ እያመጡ የሚሸጡ ነጋዴ ፤ በወቅታዊ ግጭት ምክንያት አርሶ አደሩ ምርቱን ወደገበያ እንደማያወጣ ገልጸዋል።


" አርሶ አደሩ በሰላም ውለን መግባት ስላልቻልን ምርቱን እያወጣ አይደለም። ነጋዴው ደግሞ ያገኘውን ይዞ ይመጣል " ብለዋል።


እኚሁ ነጋዴ ጤፍ 12 ሺህ ብር እየሸጡ እንደሆነ ተናግረዋል።


የጎንደር ነዋሪ የሆኑት ይፍቱ ስራማረው ፤ የዋጋ ንረቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል።


" እውነት ለመናገር እንኳን በሁለት ዓመት ውስጥ በዚህ ወር ውስጥ እንኳን ከፍተኛ ጭማሪ ነው ያለው። 30 እና 20 ብር ስንገዛው የነበረው እቃ አሁን 100 ቤት ውስጥ ነው።


ሽንኩርት ከግርግሩ በፊት ከ50 - 55 ብር ነበር አሁን ሱቅ ውስጥ እስከ 120 ብር ዋና ገበያ እስከ 80-100 ብር ይሸጣል። 


ሞኮሮኒ ፓስታ ከአንድ ወር በፊት ነው የጨመሩት የ20 ብር ጭማሪ አለው ፤ ጤፍ 115 ብር - 120 ብር ይባላል በኪሎ ፤ አቅርቦትም ስለሌለ ይሆናል " ሲሉ ተናግረዋል።


አዘዞ ከተማ የሚኖሩት የችርቻሮ ነጋዴዋ ወ/ሮ አለሚቱ ደሴ ፤ ጤፍን ጨምሮ ሌሎች እህሎች ተወዷል ብለዋል።


" የገበያው ሁኔታ በጣም ከባድ ነው ለሻጭም ለገዢም ... ቀይ ጤፍ 90 ብር ነው ፣ ነጭ ጤፍ 100 ብር አሁን ላይ ነው በጣም የጨመረው 60 እና 70 ብር ነበር ፤ ግጭት ከጀመረ አንስቶ እስከ 100 ብር ገብቷል። ሽንኩርትም እስከ 100 ብር እየተሸጠ ነው። " ብለዋል።


እህል እየተቀበሉ ያሉት የገጠሩ ማህበረሰብ ይዞ ሲመጣ እነድሆነ የገለፁት ወ/ሮ አለሚቱ " ባለው ችግር የገጠሩ ነዋሪዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ አልቻሉም " ሲሉ ገልጸዋል።


የአማራ ክልል የኅብረት ስራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለልስጣን ፤ እየታየ ያለድ የዋጋ ንርተን ለመቆጣጠር ከክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር ተባብሮ ምርቱን በብዛት እንደሚያጓጉዝ እና ለዚህም ኮማንድ ፖስቱ እጀባ እንዲያደርግ እንደሚጠይቅ ገልጿል።


ይህ ግን ዘላቂ መፍትሄ ባለመሆኑ ፍፁም ሰላምን በማስፈን ሂደት እና መሰረታዊ ፍጆታ ከቦታ ወደቦታ እንዲንቀሳቀስ ህዝቡ ሊተባበር ይገባል ብሏል።

መረጃው ከአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ የተገኘ ነው።

@tikvahethiopia

Report Page