#UpdateDW
ረ/ኮሚሽነር ግርማ አደሬ ዛሬ ችሎት ቀረቡ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነአቶ ጃዋር መሃመድ ህክምና ላይ አስተላልፎ የነበረውን ውሳኔ ለምን እንዳልፈፀመ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አዣዥ ረዳት ኮሚሽነር ግርማ አደሬ በአካል ቀርበው መልስ እንዲሰጡ ቢያዝም ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ፖሊስ አዛዡን ለዛሬ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ/ም አስሮ እንዲያቀርብ ማዘዙ ይታወሳል።
ዛሬ የቃሊቲ ማረሚያ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ዳይሬክተር ረ/ኮሚሽነር ግርማ አደሬ ችሎት ቀርበው ምላሽ ሰጥተዋል።
ከተከሳሾች ጠበቆች አንዱ የሆኑት ጠበቃ ከድር ቡሎ እንዳሉት ኃላፊው ለፍርድ ቤት እንደገለፁት ተከሳሾቹን የግል ዕክምና ተቋም ያልወሰዷቸው ከፀጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መሆኑን አንስተዋል።
በደብዳቤው ላይ ከሰፈረው ፅሁፍ መካከል ፦
"...ተከሳሾችን ወደግል የህክምና ተቋም ተገቢውን ጥንያቃቄ ከሚመለከተው የፀጥታ አካላት ጋር በመነጋገር ጥረት ቢያደርግም ተከሳሾች ወደተባለው ቦታ ቢሄዱ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት የፀጥታ አካላት ለተቋሙ ሲቀርብ የነበረ እና እንዲሁም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተከሳሽ ደጋፊዎች ለፍርድ ቤት መረበሽ እንዲፈጠር ምክንያት ሲሆኑ መቆያታቸውን የሚታወስ ሲሆን ይህም ችግር በተመሳሳይ ኮሚሽኑ ተከሳሾችን ከፍርድ ቤት አጅቦ በሚመላለሱበት ጊዜ ስጋቱ በተደጋጋሚ የሚታይና እንዲህ ያሉትን ችግሮች እንዳያጋጥም በመከላከል ተከሳሾችን የማቅረብ ሂደቱ ነገር በጥንቃቄ ይከናወናል የሚል ጥናት እየተደረገ ነው"
ችሎቱ እንዴት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊከበር እንዳልቻለ / የበላይ አካል ያዘዛችሁን ነው ወይስ ፍርድ ቤት ያዘዛችሁን ነው የምትፈፅሙት እንዲሁም ፍርድ ቤቱ እንዲቀርቡ ሲያዞት ለምን አልቀረቡም የሚል ጥያቄዎችን ለረ/ኮሚሽነር ግርማ አቅርቦ ለዚህ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም።
ጠበቆች በበኩላቸው ላንድ ማርክ ሆስፒታል የሚገኝበት ሜክሲኮ አካባቢ የፀጥታ ችግር እንደሌለ አንስተው ተከራክረዋል።
በተጨማሪ ጠበቆች የበላይ አካላትስ ቢሆኑ ለህግ ተገዢ አይሆኑም ወይ ? እነዚህ ሰዎች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፈው ተከሳሾች ህይወታቸው ቢያልፍ ኃላፊነቱን ማን ይወስዳል የሚል ጥያቄም አንስተዋል።
የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. አቶ በቀለ ገርባን ከሃኪማቸው ጋር ወደ ላንድ ማርክ ሆስፒታል እያቀኑ በመሃል ያለፈቃዳቸው ወደ መንግሥት ሆስፒታል ሲወሰዱ ቡድኑን የመሩት ሁለት የማረሚያ ቤቱ የፖሊስ ኃላፊዎች ከከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል ዳይረክተሩ ጋር ለተጨማሪ ማብራሪያ ለየካቲት 22 ቀን በተያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተወስኗል።
ምንጭ፦ DW