UNHCR

UNHCR


"ስደተኞቹ የት እንዳሉ አላውቅም" - UNHCR

ከሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን ለስደተኞች የሚሰጥ መታወቂያን የያዙ ግለሰቦች ከህወሓት ወገን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ማለቱ ይታወቃል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት፥ UNHCR የሚሰጠውን የስደተኞች መለያ መታወቂያ የያዙ ታጣቂዎች ከሱዳን ድንበር ተሻግረው ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሁም ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን ገልጾ ነበር።

አማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገር ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ በሱዳን አቅጣጫ ጥቃት ሊያደርሱ ሲሉ እርምጃ የተወሰደባቸው የህወሓት ታጣቂዎች የተመድ የስደተኛ መታወቂያ የያዙ መሆናቸውን አሳውቀው ነበር።

ዛሬ ደግሞ UNHCR ባወጣው መግለጫ በሱዳን በሚገኙ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም እነዚህ ስደተኞች የት እንዳሉ አላውቅም ብሏል።

UNHCR ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚወጡት ስደተኞች የት እንደሚሄዱ የሚያረጋግጥበት መንገድ የለኝም ሲል ገልጿል።

ሱዳን ውስጥ የመዘገባቸው አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በጦርነት ስለመሳተፋቸው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡን እንደሚያውቅም UNHCR አመልክቷል።

UNHCR የመዘገባቸው እና መታወቂያ የሰጣቸው ግለሰቦች በስደተኞች ማቆያ ካምፕ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ መውሰዳቸውን አረጋግጦ ለዚህም ምዝገባ የሚሆን የራሱ አሠራር እንዳለው አመልክቷል።

"ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች ስደተኛ ተደርገው አይወሰዱም" ሲል አሠራሩን አብራርቷል።

ስደተኛ የሚለው መለያ፤ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ለሆነ ሰው እንደማይሰጥም ገልጿል።

UNHCR ፤ የስደተኞች መጠለያዎች ሰብዓዊ እርዳታ መስጫ ሆነው መቀጠል አለባቸው ያለ ሲሆን ፥ "በግጭት ወቅት የስደተኞች ማቆያዎችን ሰብዓዊ መዳረሻ አድርጎ ማስቀጠል ከባድ ቢሆንም ከሱዳን መንግሥት ጋር በመተባበር ይህንን መርኅ ለመጠበቅ አንሠራለን" ብሏል።

ድርጅቱ ይህን መርህ ለማስጠበቅ ሲልም በስደተኞች መጠለያዎች ታጣቂዎችን ከሲቪሎች እንደሚለይ አስታውቋል። 

በሱዳን ያሉት የስደተኞች መጠለያዎች ለኢትዮጵያ አማጺያን መሸሸጊያ እንዲሆኑ እንደማይፈቅድም ገልጿል።

Report Page