UN

UN


በትግራይ ክልል የነበረው እርዳታ አቅርቦት ከተጠናቀቀ ሁለት ሳምንት እንደሆነ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ግራንት ሌይቲ አስታወቁ።

አስተባባሪው ትናንት ባወጡት መግለጫ አስፈላጊ የሆኑ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ማቅረብ አለመቻሉ፣ የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት መኖሩ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

በትግራይ ክልል 90 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል፤ 400 ሺህ ያህሉ ደግሞ ረሃብ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ሲሉ አስተባባሪው ገልጸዋል።

በአማራ እና አፋር ክልል ደግሞ 1.7 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ሊጋለጡ ከጫፍ ደርሰዋል ብለዋል ሲሉ የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪው አመልክተዋል።

"የስብዓዊ እርዳታ እቀባ"

ግራንት ሌይቲ እንዳሉት በትግራይ ክልል ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለና የደኅንነት ሁኔታው ቢሻሻልም ክልሉ "ይፋ ባልሆነ የስብዓዊ እርዳታ እቀባ ስር ይገኛል" ብለዋል።

ሕይወት አድን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች እጅጉን የተገደቡ ሆነው ቀጥለዋል ብለዋል።

መግለጫው በአፋር በኩል የሚያቀና አንድ መንገድ ብቻ መኖሩን አስታውሶ የሎጂስቲክስ እና ቢሮክራሲው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን ከባድ እንዳደረገው አመልክተዋል።

በክልሉ ውስጥ የእርዳታ ክምችት፣ ጥሬ ገንዘብ እና ነዳጅ እጅግ በጣም አነስተኛ ናቸው አልያም ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል የተባለ ሲሆን፤ የምግብ ክምችት ከሁለት ሳምንት በፊት ማለትም ነሐሴ 13 ተጠናቋል ብሏል መግለጫው።

የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተመጣጣኝ እርዳታ ለማቅብ በየቀኑ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ቁስ እና ነዳጅ የጫኑ 100 ተሸከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባት ቢኖርባቸውም፤ ከዚህ ውስጥ እስካሁን ወደ ክልሉ መግባት የቻለው ዘጠኝ በመቶ ብቻ የሚሆኑ ተሸርካሪዎች ናቸው ብሏል የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም።

በአሁኑ ወቅት 172 ተሸከርካሪዎች በአፋር መዲና ሰመራ መቆማቸውን በመግለጽ ከእሁድ ነሐሴ 16 ወዲህ ወደ ትግራይ የገባ የሰብዓዊ እርዳታ የጫነ ተሸከርካሪ አለመኖሩም ተገልጿል።

"መንቀሳቀስ ያልቻሉ 172 ተሸርካሪዎች ሰመራ ላይ ቆመዋል። የፌደራል እና ክልል መንግሥት እክል በመሆናቸው ከፍተኛ መጠን ያለው የእርዳታ አቅርቦት በጂቡቲ፣ አዳማ እና ኮምቦልቻ ተከማችቷል" ይላል መግለጫው።

የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ ወደ ክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ እክል የሆኑት የህወሓት አማጺያን ናቸው ይላል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢል ለኔ ስዩም ትናንት ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እርዳታ በተገቢው ሁኔታ እንዳይቀርብ "እንቅፋት እየፈጠረ ያለው ህወሓት በመሆኑ የተደራሽነት ችግር ጥያቄ መነሳት ያለበት ከዚሁ ቡድን አንጻር ነው" ብለዋል።

ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት ናቸው የተባሉ አሠራሮች እንዲስተካከሉ ማድረጉን ገልጸዋል።


#የጥሬ_ገንዘብ_እጥረት

ለሰብዓዊ ቀውሱ ምላሽ ለመስጠት 6.5 ሚሊዮን ዶላር (300 ሚሊዮን ብር) በየሳምንቱ ያስፈልጋል ያሉት ግራንት፤ ከሐምሌ 5 ወዲህ ወደ ትግራይ የተጓጓዘው 88 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት መመሪያ መሠረት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች ላይ መያዝ የሚችሉት እስከ 2 ሚሊዮን ብር ድረስ ነው ብለዋል የተቋሙ የኢትዮጵያ አስተባባሪ።


#ነዳጅ

የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪው ለሰብዓዊ አቅርቦት ሥራው በሳምንት ቢያንስ 200 ሺህ ሊትር ነዳጅ ያስፈልጋል ይላሉ።

ይሁን እንጂ ከሐምሌ 5 ወዲህ ትግራይ የደረሰው የነዳጅ መጠን 282 ሺህ ሊትር ነው ብለዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ደግሞ ወደ ክልሉ የገባ የነዳጅ አቅርቦት አለመኖሩን በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ መሠረት በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን እንዲፈቅዱ እና እንዲያሳልጡ እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሠራተኞች እና ንብረቶችን እንዲያከብሩና እንዲጠብቁ አስተባባሪው ጠይቀዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች፣ አቅርቦቶች፣ ነዳጅ እና ጥሬ ገንዘብን ጭምሮ ቁሳቁሶች፤ አመቺ በሆነ መንገድ ያለምንም ገደብ ወደ አገሪቷ እንዲገቡ መፍቀድ አለበት ብለዋል የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪው።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ሕግ መሠረት መብራት፣ ኮሚኒኬሽን፣ የባንክ አገልግሎቶችን የማስጀመር ግዴታ አለበት ብለዋል።

በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚሊዮኖች ሕይወት በእኛ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦ መጠን ላይ ይወሰናል ያሉት አስተባባሪው፤ ያለምንም እክል የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው መድረስ አለበት ብለዋል።

(BBC)

Report Page