Turmeric & Inflammation
Crohn's & Colitis Ethiopia | Dr. Armoniam Mulatu & Dr. Fasika Shimeles
የእርድ የጤና ጥቅሞች
በደፈናው የአንጀታችንን ጤና ለማማሻሻል ስናስብ፣ የጠቃሚ ረቂቅ ነፍሳት አዘል ምግቦች/Probiotics/ እና የተብላሉ ምግቦች/Fermented foods/ ወደ አዕምሮአችን በቀዳሚ ደረጃ ይመጣሉ፤ ሆኖም ግን ማዕዳችን ላይ እርድን/Turmeric/ መጨመር የአንጀታችንን ጤና ከመደገፍ በተጨማሪ ሌሎች የጠኑ የአንጀት ህመሞችን በመከላከል የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
አንጀት
በእርድ ውስጥ የሚገኝ Curcumin የተሰኘ ንጥረ ነገር አንጀታችንን እንደ ንብር ሸፍነው የሚገኙትን ጡንቻዎች በማፍታታት እና ምግቡን በቀላሉ እንዲሸራሸር በማድረግ የምግብ መፈጨትን ያሳልጣል። በተጨማሪም ከምግብ መፈጨት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ጋዞች እና የሆድ መነፋትን ይቀንሳል።
ትልቅ አንጀት
ጤናማ ትልቅ አንጀት ለስኬታማ የሆድ እቃ ክንውን እንዲሁም ለጠቃሚ የአንጀት ባክቴርያ ሥራ እና ዕድገት እጅግ ጠቃሚ ነው። በእርድ ውስጥ የሚገኘው ቢጫ፣ብርቱካናማ ቀለም እንዲኖረው የሚያደርግው ንጥረ ነገር/Curcumin/ በአንጀት ግድግዳ ላይ የሚገኙ እጢዎችን በማነሳሳት ጎጂ ረቂቅ ነፍሳት/Bacteria/ እንዲሁም ¹ሸሸራ አንጀት በሚኖርበት ጊዜ የሰውነታችንን የመከላከል አቅም ከማጎልበት በተጨማሪ በአንጀት ውስጥ ከሚገኙ ጠቃሚ ባክቴርያዎች ጋር ያለውን ሚዛን ይጠብቃል።
¹ሸሸራ አንጀት- በተለያዩ ምክኒያቶች በአንጀት ረቂቅ ቀዳዳዎች ማፍሰስ የተነሳ ከአንጀታችን ወደ ሰውነታችን ጎጂ ነፍሳት መተላለፉቸውን የሚያሳይ ቃል።
ሆድ/ጨጓራ
Turmeric/እርድ/ የጨጓራችን ንብሮችን በተለያየ መንገድ ያግዛል። ከእነዚህም መካከል የጨጓራን ጤና የሚያሳሱ ኢንዛይሞችን በመግታት እንዲሁም የጨጓራ ግድግዳ የንፍጥ(ዝልግልግ ፈሳሽ) መለቀቅን በመጨመር የጨጓራ ጤናን ይጠብቃል። የጨጓራ ንፍጥ የመጀመሪያ የመከላከል ደረጃ ሲሆን ፤የጨጓራ አሲድ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ይረዳል።
የአንጀት መቆጣት እና እርድ
Curcumin የአንጀት መቆጣት ያለባቸው ሰዎች ላይ አመርቂ ለውጥ አሳይቷል። በክሮንስ እና አልሰረቲቭ ኮላይተስ የተጠቁ ሰዎች ላይ የሚከሰት የአንጀት ብግነት ለጠና ህመም እንዲሁም ዘላቂ የአንጀት መቆጣት ስለሚዳርግ የአንጀት ካንሰር የመከሰት ዕድልን ይጨምራል።
በአንጀት መቆጣት የተጠቁ ዘጠኝ ህመምተኞች ላይ Curcumin'ን መጠቀም ስለሚያሳየው ለውጥ በተደረገ ጥናት፤ አምስቱ በአልሰሬቲቭ ኮላይተስ የተያዙት፤ 5-aminosalicyclic acid የተባለ መድሐኒት እና Corticosteroids በመውሰድ የሚገኙ ታካሚዎች ላይ፤ በተጨማሪ 550mg Curcumin በቀን ሁለቴ ለአንድ ወር እንዲሁም በቀን ሶስቴ ለቀጣይ ወር እንዲወስዱ ከተደረገ በኁዋላ፤ ሁሉም ታካሚዎች የሚያስደንቅ ለውጥ አምጥተዋል ፤ ካሳዩት ለውጥ የተነሳም ከአምስቱ አራቱ የሚወስዱትን መድሐኒት መጠን ቀንሰዋል፣ አልያም አቁመዋል።
በተመመሳሳይ በክሮንስ ህመም በተያዙ ሰዎች ላይ በተሰራ አነስተኛ ጥናት፣ ተመሳሳይ ግኝት አግኝቷል፤ እንዲሁም ሁሉም ተሳታፊዎች ላይ የበሽታ ምልክቶች መሻሻል ታይቶባቸዋል። በቀጣይ ወራት በነበራቸው ክትትል አመርቂ ለውጥ በማሳየት፤ የተቅማጥ መሻሻል እና ደዳር ዓይነ ምድር መመልከት ጀምረዋል፣ የሆድ ህመም እና ቁርጠትም በተመሳሳይ መሻሻል አሳይተዋል። እነኚህ ለውጦች ከታካሚዎች የግል አስተያየት በተጨማሪ በላብራቶሪ በታዩ ውጤቶችም ተደግፏል። ከእነዚህም መካከል CRP እና ESR የሚባሉ የሰውነት ብግነት ጠቋሚዎች Curcumin'ን ለሁለት ወር ከወሰዱ በኁዋላ ወደ ተለመደው ደረጃቸው ተመልሰዋል።
በቀጣይ ሳምንት የእርድን ተጨማሪ የጤና ጥቅሞች፣ እርድን መጠቀም ለማን አይመከርም? የሚለውን፣ እንዲሁም ስለ ቁንዶ በርበሬ መረጃን እናቀርብላችሗለን።
ይከታተሉን!
Crohn's & Colitis Ethiopia
19/07/2022
ማጣቀሻ / References:
- Curcumin: An age-old anti-inflammatory and anti-neoplastic agent - ScienceDirect
- Curcumin therapy in inflammatory bowel disease: a pilot study - PubMed (nih.gov)
- Curcumin Maintenance Therapy for Ulcerative Colitis: Randomized, Multicenter, Double-Blind, Placebo-Controlled Trial - Clinical Gastroenterology and Hepatology (cghjournal.org)
- Curcumin in Combination With Mesalamine Induces Remission in Patients With Mild-to-Moderate Ulcerative Colitis in a Randomized Controlled Trial - Clinical Gastroenterology and Hepatology (cghjournal.org)