#TikvahFamily

#TikvahFamily

Tikvah-Ethiopia

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ሸምሰዲን ጠሃ የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ 12 ቀናት እንደሆናቸው ከOromo Political Prisoners Defense Team ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከነሱ በተጨማሪ የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ አድማውን ከተቀላቀሉ 6 ቀናት አልፏቸዋል።

ለምንድነው የረሃብ አድማውን እያደረጉ የሚገኙት ?

ጠበቃቸው ከድር ቡሎ ተከታዩን ብለዋል ፦

"መነሻው እነሱ ችሎት በሚቀርቡበት ሰዓት ቤተሰቦቻቸውን እና ሌሎች ሰልፍ ላይ የነበሩ ሰዎች ቢጫ ልብስ ለብሰው እንዳትገቡ ተብሎ አንዳንዶቹ መታወቂያቸው እየታየ ሲመለሱ ነበር።

እነአቶ ጃዋር በችሎት ላይ ይሄ ነገር አግባብ አይደለም ፣ ቤተሰቦቻችን መታወቂያ እየታየ እየተባረሩ ፤ ቢጫ ለበሱ ተብሎ ቤተሰቦቻችን ከችሎት በተባረሩበት ሁኔታ ይሄ አግባብ አይደለም ፤ ቤተሰቦቻችን በሌሉበት ተለቅመው በታሰሩበት ሁኔታ ቃላችንን መስጠት አግባብ አይደለም የሚል ነገር አንስተው ነበር።

በተጨማሪም በነሱ አነጋገር "በእኛ የኦሮሞ ልጆች" ማሥዋትነት የመጣው ለውጥ አንደኛ ቢሮዎቻችን እየተዘጉ ፣ አባላቾቻችን እየታሰሩ ያለበት ሁኔታ አግባብ አይደለም።

ሌሎች ደግሞ ለዚህ ለውጥ ምንም አስተዋፅኦ የሌላቸው በ5,000 ሰው ደም በመጣ ለውጥ እንዳፈለጉ ተወዳዳሪ እያዘጋጁ ባሉበት ወቅት ፣ ቢሯቸውን ከፍተው በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ባለበት ወቅት ይሄን ማየት ለህበረተሰባችን ስድብ ነው ይሄ ሊቆም ይገባል በሚል ይሄን ከምናይ ያለን መሳሪያ በራሳችን ላይ ይህን ማድረግ ስለሆነ ይህን አድርገናል የሚል አቋም ነው ያላቸው።"

የጤናቸው በሁኔታ ላይ ይገኛል ?

ጠበቃ ከድር ቡሎ ፦

"የመድከም ሁኔታ ነው የሚታይባቸው። ትላንት አቶ በቀለ ናቸው ትንሽ ደክመው የነበሩት፤ ዛሬ ደግሞ ከማንም በላይ በጣም የደከመው አቶ ጃዋር ነው፤ ሊያናግረንም አልቻለም። ሁሉም መናገር አይችሉም።

አቶ ደጀኔ ጣፋም ታመዋል፣ ዛሬ ጥዋት ደግሞ ቦና እና አራፋት አቡበክር የሚባሉት ሁለቱ በጠና ታመው ሆስፒታል ገብተዋል።"

ሀኪሞቻቸው ምን ይላሉ ?

አሁን ባለው ሁኔታ ጃዋር እጅግ በጣም ታሟል። ወደሆስፒታል መሄድ እንዳለበት ነው የገለፁት።

የነአቶ ጃዋር መሀመድ የረሃብ አድማን ተከትሎ የተደረጉት ሰልፎች ጉዳይስ ?

አርብ ዕለት በአምቦ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ተማሪዎች፤ ፍትህ ለሀጫሉ፣ የታሰሩ ፖለቲከኞች ይፈቱ፣ እና ሌሎች መፈከሮችን በማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን የሚገልፅ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

በወቅቱ ሰልፉ ብዙም ሳይቆይ ተማሪዎቹ በፖሊስ ሀይሎች እንደተበተኑ እና አንዳዶችም እንደታፈሱ ፣ እንደተመቱ የከተማው አይን እማኞች ገልፀው ነበር።

የአምቦ ፖሊስ ቢሮ በወቅቱ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ዛሬ ደግሞ ሰላማዊ ሰልፉ ወደወሊሶ፣ ጊንቢ፣ ያቤሎ፣ ነቀምት፣ ደንቢ ዶሎ፣ ሻሸመኔ እና አሰቦት ተስፋፍቶ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ በኦሮሚያ ግድያ መታሰር እንዲቆም፣ በኦሮሚያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲያበቃ ሲጠየቅ ነበር።

በዛሬው ሰልፎች ላይ በአንዳንድ ቦታዎች እስካሁን ያልተረጋገጠ ጉዳት እንዲሁም አንድ የተረጋገጠ ሞት ሪፖርት ተደርጓል።

የሞት ሪፖርቱ የመጣው ከቦረና ዞን ያቤሎ ሲሆን ሟቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆኑ ተገልጿል።

አንድ በሰልፉ ላይ የነበረ የሃይስኩል ተማሪ ዛሬ ስለነበረው ሰልፍ ለአዲስ ስታንዳርድ ድረገፅ እንደተናገረው ከሆነ ከሟቹ በተጨማሪ 4 ሰዎች በጥይት ተመተው እና ተጎድተው ወደ ወላይታ ሶዶ ሆስፒታል ሪፈር ተደርገዋል። በተጨማሪ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠማቸው በዛው ባሉ ክሊኒኮች ተወስደዋል።

በአሰቦት ዛሬ ጥዋት ተማሪዎች ሰልፍ ወጥተው የነበረ ሲሆን በኃላም የአከባቢው ነሪዎች ተቀላቅለው ነበር። ሰልፉ በፖሊስ እስኪበተን ድረስ ጥያቄው የነበረው የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ነው። አንድ የሃይስኩል ተማሪ እንደተናገረው ከሆነ ከሰልፉ በኃላ ሰዎች ታስረዋል።

በተመሳሳይ በጊንቢ የጊንቢ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ፍትህ ለሃጫሉ፣ የፖለቲከኛ እስረኞች ይፈቱ፣ በኦሮምያ ግድያ ይቁም በሚል ሰልፍ አድርገው ነበር የሰልፉ አስተባባሪዎች፣ አንዳንድ መምህራን ለእስር መዳረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በረሃብ አድማ ላይ ስለሚገኙት እነአቶ ጃዋር ምን ብሎ ነበር ?

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እና በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማቆያ በመገኘት እስረኞችን ከጎበኘ በኃላ መግለጫ አውጥቶ ነበር።

በወቅቱ ከእነ አቶ ጃዋር መሐመድ በተጨማሪ፣ የኮሎኔል ገመቹ አያና እና የአቶ ጥላሁን ያሚ አያያዝ ላይ ክትትል ማድረጉን ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት እና ከቂሊንጦ ጊዜያዊ ማቆያ ቤት አስተዳደሮች እንዲሁም ከእስረኞቹ ጋር መነጋገሩን ገልጿል።

አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሀምዛ አዳነ (ቦረና) እና አቶ ሸምሰዲን ጣሃ ረሃብ አድማ ዓላማ “መንግስት በሕዝብ እና በፓርቲያቸው ላይ እያደረሰ ያለውን አፈና እና የመብት ጥሰት ለመቃወም፣ የኮሎኔል ገመቹ አያናን አላግባብ የሆነ አያያዝ እና እንግልት እንዲቆም ለመጠየቅ እና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ እና እነሱን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ” መሆኑን እስረኞቹ በወቅቱ ለኢሰመኮ ገልጸዋል። 

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ ለረሃብ አድማው በምክንያትነት የተጠቀሱ አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ማረሚያ ቤቱን የማይመለከቱ መሆኑንና እስረኞችን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች ላይ ወከባ እንደማይፈጽም ገልጿል።

በወቅቱ አስተዳደሩ የረሃብ አድማው በእስረኞቹ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል፣ በተለይም ከመካከላቸው ሁለቱ የጤና ችግር ስላለባቸው በቋሚነት መድኃኒት የሚወስዱ በመሆኑ ቅርብ የህክምና ክትትል እንደሚደረግላቸው አስረድቷል።

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙ እስረኞችን አስመልክቶ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የእስረኞቹ ጤንነትና ሕይወት የከፋ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ለታሳሪዎች ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የእስረኞችን ጠያቂዎች በማረሚያ ቤቱም ሆነ በፍርድ ቤቶች በአግባቡ ማስተናገድ ይገባል›› በማለት ገልጸዋል።

[Ethiopian Human Rights Commission , Oromo Prisoners Defense Team,BBC , Addis Standard]

Compiled By : Tikvah-Ethiopia

የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ/ም

አዲስ አበባ,ኢትዮጵያ


Report Page