Tikvah Tigray Report

Tikvah Tigray Report

Tikvah-Ethiopia

WFP ለትግራይ ክልል የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል መግለፁ :

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢስሊ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የገለጹት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ አጋር መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በትግራይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሁሉም ወገኖች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚደረግና ይህንን ለማድረግ 107 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸው ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡


ወ/ሮ ሙፈሪያት ከተመድ ተቋማት ጋር ያደረጉት ውይይት :

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ዛሬ ከተባበሩት መንግስታት ተቋማት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በበይነመረብ ውይይት አካሂደዋል።

ሚኒስትሯ በውይይቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከሕግ ማስከበር ሂደት ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ ስርጭትን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው የእርዳታ ስርጭቱ መጠን በየወቅቱ እያደገ መምጣቱንና በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ወደ መልሶ ማቋቋም የሚያመራበትን ሂደት ከማስጀመር አኳያ የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህዝቡን ማገልገል እየጀመሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ይሁን እንጂ አንዳንድ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ይህንን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ከማስረዳት አኳያ በቂ ስራ እየሰሩ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ዓለም አቀፍ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በመሬት ላይ ያሉትን እውነታዎች ሳያዛቡ፣ ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እንዲታወቅ ያደርጉ ዘንድ አሳስበዋል።


ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ከዶ/ር አብይ ጋር መወያየታቸው :

የአሜሪካው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ መወያየታቸውን በቲዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

መንግስት ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርጉ ክፍት ማድረጉ ክልሉን በማረጋጋት ሂደት መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑንና ግልፀኝነት እንደሚያሰፍን ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ገልፀዋል።

ሴናተሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ለውጦችን እያስመዘገቡ እንዳሉም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደፊትም ለቀጠናው መረጋጋትና ብልፅግና መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ባለሙሉ ተስፋነኝ ብለዋል ኢንሆፍ ።

በቀጣይም በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ከጠቅላ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር የሚያደርጉት ምክክር እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።


የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቋም ፦

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፅ/ቤት የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አንድ አይነት አቋም መያዙን አሳውቋል።

ይህን ያሳወቁት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል ካሳ ሲሆኑ "የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ አለ ፥ በክልሉ ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል። ወንጀሎችንም ፈጽመዋል" ሲሉ ከሰዋል።

የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ መኖራቸውን በተመለከተ "ሕዝቡ በዓይኑ ያየው እውነታ ነው" ያሉት አቶ ገብረ መስቀል፤ "ስለዚህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ወታደሮቹ ከክልሉ መውጣት አለባቸው ሲል አቋም ይዟል" በማለት በአንድ ድምጽ መወሰናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪ አቶ ገብረመስቀል ፥ በአማራ ክልል ኃይሎች የትግራይ ግዛት መያዛቸውን ገልጸው፤ ይህንን በተመለከተ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግልጽ አቋም እንዳለው አመልክተዋል "አስተዳደሩ ህወሓት ያስተዳድረው ከነበረው ግዛት በሴንቲሜትር የቀነሰ ክልልን አያስተዳድርም" ብለዋል።

አቶ ገብረ መስቀል እንዳሉት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተገለጸውን የትግራይ ክልልን እንደሚያስተዳድር ገልጸው፤ "እነዚህን ቦታዎች ከሕግ ውጪ የያዙ ኃይሎች የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እየተጻረሩ ነው" ብለዋል።

አጠቃላዩ ምዕራባዊ የትግራይ ክፍል እንዲሁም በደቡብ አላማጣ፣ ኮረምና ሌሎች የገጠር አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ስር መሆናቸውን አመልክተው፤ ይህንንም ለፌደራል መንግሥቱ ሪፖርት ተደርጎ ኃይሎቹ ከአካባቢዎቹ እንዲወጡ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

"ግፊት የምናደርገው የተሰማራው ኃይል እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን በአካባቢዎቹ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲቆሙና ፈጻሚዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ ነው" ሲሉ አቶ ገብረ መስቀል ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ቀደም ሲል በተካሄደው የክልል አወቃቀር ወቅት ያለአግባብ ከግዛቱ ተወስደው ወደ ትግራይ የተካለሉ አካባቢዎች መኖራቸውን ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአድዋ ድል በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ መድረክ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ አገኘሁ ተሻገር ባደረጉት ንግግር "በወልቃይት ጠገዴ የተደረገው ውጊያ ማንነትን ለማረጋገጥ እንጂ መሬት ለመውረር አይደለም፤ ከዚህ በኋላ ነፃ ወጥተናል" ሲሉ ተናግረው ነበር።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ርዕሰ መስተዳደሩን ጠቅሶ እንደዘገበው "በማይካድራ፣ በሁመራ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በዳንሻ፣ በራያ፣ በአላማጣ፣ በኮረም እና በሌሎች አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ" በህወሓት አማካኝነት ተፈናቅለዋል ሲሉ ለሚቀርበው ክስ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ገብረመስቀል በትግራይ ክልል ያጋጠመውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ተፈጽመዋል ከተባሉ ጥቃቶች መካከል በሴቶች ላይ የደረሰውን ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በተመለከተ መረጃዎችን እያሰባሰበ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን "ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው መካከል በርካቶቹ ወደ ህክምና ተቋማት አልመጡም" ብለዋል።

አቶ ገብረመስቀል ካሳ አክለውም "ሕግ ማስከበር የተባለው ወታደራዊ ዘመቻ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሏል" በሰዎች ላይ ሁሉም አይነት ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብለዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ካለው የአስቸኳይ አዋጅ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ አደጋዎችና ወንጀሎችን እንዲያስቆሙ ከፌደራል መንግሥቱና የፌደሬሽን ምክር ቤትን መጠየቁን ገልጸዋል።


የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቀጠሮ :

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር ለዛሬ ሀሙስ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ይህ የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ጥሪ ያቀረበችው አየርላንድ መሆኗን አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ዲፕሎማት ነግረውኛል ሲል የዘገበው AFP ነው፡፡


የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳምንታዊ መግለጫ :

በትግራይ ተፈፅመወል በሚባሉ የመብት ጥሰቶች ዙሪያ ገልልተኛ ማጣራት እንዲደረግ ተደጋጋሚ ጥያቄ በተለያዩ ተቋማት እንደተጠየቀ ይታወቃል።

በኤርትራ ጦርም ሆነ በሀገር ውስጥ የፀጥታ ሀይሎች በትግራይ ክልል ተፈፅመዋል የተባሉት የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል ይጠራል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከሰሞኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠ/ሚ አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት የኤርትራ ጦርና የአማራ ልዩ ሀይል ከትግራይ ክልል በአፋጣኝ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትላንት የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ ተደርጎለት፣ እውቅና አግኝቶ እንዳልተሳተፈ አረጋግጠዋል፡፡

ይሁንና ከሁለቱ ሀገራት የድንበር ሁኔታና ከህወሓት በኩል ሲሰነዘሩ ከነበሩ ሚሳኤልን ጭምር ካካተቱ ጥቃቶች አኳያ ወታደሮች ሲገቡና ሲወጡ ሊስተዋል ይችላል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ልዩ ሀይልን በተመለከተ ግን የሀገር ውስጥ የፀጥታ ሀይል እንደመሆኑ መጠን ጥያቄው ተቀባይነት የለውም ሲሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡


የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፦

በትግራይ ግጭት የተሳተፉ አካላት "ከጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ እንደተፈጸሙ ወንጀሎች ሊቆጠሩ የሚችሉ" ከባድ ጥሰቶችን እንደፈጸሙ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት ገልፀዋል።

ኮሚሽነሯ እንዳሉት ከትግራይ የሚወጡ ያልተቋረጡና ተአማኒ ሪፖርቶች በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ የተለያዩ ወገኖች የሚፈጸሙ ከባድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ እርዳታ ሕጎች ጥሰት ማመልከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉትንና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ሪፖርት የተደረጉ የጅምላ ግድያዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመመርመር እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ሚሸል ባሽሌት እንዳሉት የተፈፀሙት የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር ወንጀል እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ገልፀው በዚህም ውስጥ የተለያዩ አካላት ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በተጠቀሱት ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል ያሏቸውን አካላት በስም የጠቀሱ ሲሆን እነዚህም የመከላከያ ሠራዊት፣ ህወሓት፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ሚሊሻዎች ናቸው ብለዋል።

"በግጭቱ ላይ በርካታ አካላት መሳተፋቸውን ጨምሮ፤ ጥሰቶቹን መካድ እንዲሁም ጣት መጠቆም ይታያል። የጥሰቶቹን ሪፖርት በተመለከተ ግልፅ፣ ነፃ የሆነ ግምገማና ምርመራ ያስፈልጋል። የጥቃቱ ሰለባና ተራፊዎች የዕውነትና የፍትህ ጥያቄያቸው ሊካድ አይገባም" ብለዋል ኮሚሽነሯ።

አክለውም "የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቢሮና ሌሎች ነፃ መርማሪዎች ወደ ትግራይ ገብተው ያለውን ሁኔታ እንዲገመግሙና እንዲመረምሩ ፍቃድ እንዲሰጠን እንጠይቃለን። የትኛውም አካል ይፈፅመው እውነታው መታወቅ አለበት፤ ፈጻሚዎቹም ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።


ትግራይ ነባር እና አዳዲስ ፖሊሶችን እያሰለጠነች ነው ፦

የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በዳሰሳ የተመሰረተ ግምገማ ባማካሄድ ነባር እንዲሁም አዲስ ህዝባዊ ፖሊሶችን በማሰልጠን እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማይ ካህሳይ ፥ "...አጋጥሞ የነበረውን አጠቃላይ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት መጀመሪያ ያደረግነው ያለውን እንቅስቃሴ መገምገም ነው። ስንት ፖሊስ አለ ? የሌለውስ ስንት ነው ? ምን እየተሰራ ነው የሚለውን ሁሉ በአጭር ቀናት ዳሰሳ እና ግምገማ አድርገናል፤ በመቀጠልም ህብረተሰቡን ማገልገል ለሚፈልጉ ህዝባዊ ፖሊስ የስራ ጥሪ አድርገናል፤ ፖሊስ ከማንኛውም የፓርቲ አስተሳሰብ ነፃ መሆኑ ግልፅ ስለሆነ" ብለዋል።

ነባር እና አዲስ ህዝባዊ ፖሊስ ስልጠና እየተሰጠ ነው ሲሉ ያሳወቁት ኮሚሽነር ግርማይ ወንጀልን የመከላከል ስራ ከህዝቡ ጋር እንዲሰሩ በ6 ዞኖች በሚገኙ 15 ወረዳዎች ማሰማራታቸውን ገልፀዋል።

ኮሚሽነር ግርማይ፥ "የነበረውን ኃይል ለመልሰን በማሰልጠን መልሰን ወደስራ የምናስገባበት መንገድ አቅደን በጀትም ተመድቦልን እየሰራን ነው፤ በተጨማሪ የሚጎድል የፖሊድ ኃይል ካለ አዲስ ኃይል መልምለን ለማሰልጠን የቅድመ ዝግጅት ስራ ጨርሰናልም። ከፌዴራል ፖሊስ ያመጣናቸው ተጋሩ የፖሊስ አባላት አደራጅተን በ6ቱ ዞኖች መደበኛ 15 መሃል ወረዳዎች በመምረጥ መድበን ህዝቡ ጋር ወርዶ የፀጥታውን ዘርፍ ከህብረተሰቡ ጋር የሚሰራበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው" ሲሉ ገልፀዋል።

የትግራይ ፖሊስ አባላት ፀጥታውን ለማስከበር የተመደቡ ህዝባዊ ፖሊስ ከመሆናቸው አኳያ ወንጀልን ለመከላከል የሚመጥን ትጥቅ ተፈቅዶላቸዋል።

የትጥቅ መፈቀድን በተመለከተ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማይ ካህሳይ ፥ "እየተሰማራ ያለው ህዝባዊ ፖሊስ ነው በከተማ ሆነ በገጠር ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ነው። ስለዚህ ወንጀል ለመከላከል የሚያስፈልግ ትጥቅ እንደየአስፈላጊነቱ እየተሰጠ ነው። የሚያስፈልግ ትጥቅ ጠይቀን ተፈቅዶልን ለፖሊስ አባላት እየሰጠን እያሰማራን እንገኛለን" ብለዋል።


[Ministry Of Peace , Ministry Of Foreign , Office Of PM , EBC, Al Jazeera ,BBC , Tigray TV , UN Human Rights, Ahadu FM 94.3]

Compiled By : Tikvah-Ethiopia

Report Page