Tikvah Family
" እኛ ሰሚ አጥተናል ፤ ነገስ ዋስታናችን ምንድነው ? " - የቲክቫህ አባላት ቄለም ወለጋ
ከሰሞኑ ጥቃት በተፈፀመበት የቄለም ወለጋ አካባቢ የሚኖሩ ወገኖች አሁን ላይ የፀጥታ ኃይል በአካባቢው ቢኖርም የነገ ዋስትናቸው እንደሚያሳችባቸው ገልፀዋል።
ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ጥቃት ተፈፅሞ ሌላ ሀዘን እንዳይከተል ፀጥታው መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
" እኛ ሰሚ አጠተናል፣ መፍትሄ እንፈልጋለን ፣ ፍትህን እንፈልጋለን ፣ ተጠናቂነት እንዲሰፍን እንፈልጋለን " ሲሉ በሀዘን ስሜት ውስጥ ሆነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ከጥቃት የተረፉት ወገኖች " የመግለጫ ጋጋታ አንፈልግም፣ በየጊዜው ንፁሃን ሰው ይጨፈጨፋል መግለጫ እንደጉድ ይወጣል በኃላም ይረሳል ተጎጂዎችን ዞር ብሎ እንኳን የሚያየ የለም " ብለዋል።
እኛ መግለጫ እና ወሬ ሳይሆን የሚታይ ተግባር፣ የመኖር ዋስትና መረጋገጥን ብቻ ነው የምንፈልገው ፤ ምንም ስለፖለቲካ የማያውቁ ህፃናት፣ ሴቶች እናቶች ያለሃጢያታቸው ለምን ይጨፈጨፋሉ ? መቼ ነው ይሄ የሚያበቃው ሲሉ ጠይቀዋል። የንፁሃንን ሞት ለፖለቲካ ንግድ እና በየሚዲያው ለገንዘብ የሚጠቀሙ በሀዘናችን ላይ ሀዘን እየደረቡ ነው ብለዋል።
ከትላንት ወዲያ በተፈፀመው ጭፍጨፋ ህይወታቸው ያለፉትን ሰዎች የመቅበር ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን እዛ አካባቢ ቤተሰቦቹ የሚኖሩ የቲክቫህ አባል አንድ የሚያውቀው ሰው ወንድሞቹ ከነቤተሰቦቹ መገደላቸውን ፤ ከዚህ ባለፈ የታገቱ ሰዎች መኖራቸውን አመልክቷል።
" ከዚህ በፊት የዛሬ አመት አካባቢ ምንም እንኳን ጉዳት ባይደርስም ትንኮሳዎች ነበሩ " ያሉት የቄለም ወለጋ ቤተሰቦች የተደራጁ ቡድኖች መጥተው ከአንድ ወጣት ከብት ሊውስዱ በነበረበት ወቅት በተፈጠረ ግርግር ወጣቱን በሰው ፊት ገድለው ፤ ከብቶቹን ይዘው ነው የሄዱት ፤ ከዛ በኃላ ማህበረሰቡ ፈርቶ ነው የቆየው ብለዋል።
" ታጣቂዎቹ የታጠቁት መሳሪያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠባቂዎች እራሱ የሚይዙት አይመስልም " የሚሉት እኚሁ የቤተሰብ አባላት " በጣም የታጠቁ፣ በአካልም ግዙፍ የሆኑ ፣ ለዚህ አላማ የተዘጋጁ ነው የሚመስለው " ሲሉ አስረድተዋል።
" እዛ ያለው ማህበረሰብ አቅመ ደካማ፣ ምስኪን ገበሬ ነው የዕለት ጉርሱን ዳፋ ቀና ብሎ የሚበላ ነው። መብራት እንኳን በቅጡ የሌለው አካባቢ ነው።
ከቦቀሎ እና ማሽላ እንጀራ በዘለለ የማይበላ ፤ በኑሮው የተጎሳቆለ ማህበረሰብ ነው እንኳን ጥይት እና ገጀራ ሊገባው ! እጅግ ምስኪን ማህበረሰብ ነው ።
ሰው ወዳድ ናቸው ፤ እንግዳም ተቀባይ ናቸው ፤ ያላቸውን አውጥተው የሚያስተናግዱ ናቸው። ፍርድ ከላይ ነው ፤ ፍርድ ከአላህ ነው ለዛ ማህበረሰብ ይሄ አይገባውም ነበር።
በሚያሳዝን ሁኔታን የማህበረሰቡን ሮሮ፣ ጩኸት ማን እንደሚሰማው አናውቅም። ጥቃት አድራሾቹን ማን ሃይ እንደሚላቸውም አናቅም።
ለማን አቤት እንደምንል ግራ የሚገባ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ባለፈው ከፍ ብሎ ጊምቢ አካባቢ በጣም ብዙ ሰው በተሰመሳሳይ ሁኔታ ተጨፍጭፏል። እዛም ወሎዎች ናቸው እዚህም ወሎዎች ናቸው።
ዘር እየተመረጠ ሰው የሚጨፈጨፍበት ጊዜ ላይ ደረስን ፤ ለማን አቤት እንደምንል አናውቅም። " ሲሉም ገልፀዋል።
የሰው ልጅ ደም እንደውሃ እየፈሠሰ ፣ ህፃናት እና ሴቶች፣ እናቶች እየተገደሉ በየጊዜው ተደጋጋሚ መግለጫ እና መሬት ላይ የማይወርድ የማይተገበቅ ቃል መግባት እጅግ የሚያሳዝን መሆኑን በመግለፅ ተጨማሪ ጭፍጨፋ እንዳይፈፀም የሚቻለው ሁሉ እንዲደረግ አሳስበዋል።
@tikvahethiopia