Tikvah-Family

Tikvah-Family


የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ይፋ ከተደረገ በኃላ ቅሬታ አለን የሚሉ ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጥያቄ እያቀረቡ/የቲክቫህ አባላትም ቅሬታቸውን ልከዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዛሬ በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ፊት ለፊት በሰልፍ ጥያቄ እንዳቀረቡ አሳውቀውናል።

ተማሪዎች ጥያቄ ?

በተማሪዎች በኩል የሚመጡት ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው "የማለፊያ ነጥብ ይነስልን" የሚል ነው። ተማሪዎቹ ለዚህ ምክንያት የሚሉት በሀገሪቱ የነበረው ሁኔታ ታሳቢ ሊደረግ ይገባ ነበር የሚል ነው። ተማሪዎቹ ነባራዊ ሁኔታ እያሉ የገለፁት ፥ "በሀገሪቱ የነበረ አለመረጋጋት፣ ኮሮና፣ የትምህርት ቤት ዝግጅት እጥረት፣ የተማሪዎች አእምሮ ቀውስ" የሚሉትን ነው።

ቅሬታ አቅራቢዎች የግል ተቋማት ማለፊያ ነጥብ እንዲቀንስልን ብለው ጠይቀዋል።

በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት ስለፈተናው አፈታተን ቁጥጥር ይፈትሹልን ሲሉም ቅሬታ አቅርበዋል፤ ይህም የፈተና ስርቆት፣ አስተማሪ ለተማሪ መልስ መስጠቱ፣ ተማሪ መኮራረጁ፣ ስልክ ይዞ መግባቱ፣ ቸልተኝነት የነበረው ፍተሻ፣ በገንዘብ ስልክ ማስገባት፤ ኢንተርኔት አለመዘጋቱ" የሚሉት ናቸው።

ተማሪዎቹ በየትኞቹ ትምህርት ቤቶች ወእኚህ ጉዳዮች እንደተፈፀሙ ወይም ደግሞ በመላው ሀገሪቱ መፈፀሙን የሚጋፅ ነገር ያላሳፈሩ ሲሆን ነገር ግን ዳግም ፍተሻ እንዲደረግ እንደሚጠይቁ በሚፅፏቸው መልዕክቶች አሳውቀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከቤተሰቦቹ በርካታ የቅሬታ መልዕክት ያገኘ ቢሆንም አጠቃላይ ቅሬታ አቅራቢዎቹን ቁጥር ማወቅ አልተቻለም።

ከሚነሱት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸውን ከፍተኛ አካላት ለማነጋገር ጥረት ስናደርግ የቆየን ቢሆንም ማግኘት አልቻልንም። 

ነገር ግን በምደባ እና መቁረጫ ነጥብ ጋር በተያያዘ አንድ ያገኘናቸው ግለሰብ፤ ምደባ የሚካሄደው፣ መቁረጫ ነጥብ ተቆርጦ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሚገባው ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የመቀበል አቅማቸውን አይተው ነው ብለዋል።

ይህም በጥንቃቄ እንደሚካሄድ እና የዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅም እና ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት በአግባቡ ታይቶ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት የትምህርት ሚኒስትቴር በሰጠው መግለጫ የ2012 ፈተና ያለስርቆት መጠናቀቁን ገልፆ ፥ ኩረጃዎች ግን እንደነበሩ መግለፁ አይዘነጋም።

ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ስርቆትን ለማስቀረት 8 ፈተናዎች በ32 ስብጥር በማድረግ ኩረጃ እንዳይኖር ለመከላከል መሰራቱን መግለፁ አይዘነጋም።

በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ "የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና በፍፁም እንዳልተሰረቀ አረጋግጣለሁ" ማለታቸው ይታወሳል። በአንዳንድ የፈተና ጣቢያዎች ስልክ ይዘው የገቡ በጣም ጥቂት ተማሪዎች መኖራቸውን ግን ገልፀው ፤ ይህ ሁኔታ ከፈተና ኩረጃ ጋር የሚያያዝ እንጂ የፈተና ስርቆት ነው ማለት አያስችልም ብለው ነበር።

ሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶ/ር ዲለሞ ኦቶሬም ፈተናው እና የማረም ስራው በስኬት እና በፍጥነት መጠናቀቁ ገልፀው ነበር።

ለፈተናው ታርሞ በፍጥነት መጠናቀቀም ፤ ዋነኛው ምክንያት በሰላም መጠናቀቁ ነው፤ ፈተናው በሰላም ባይጠናቀቅ ኖሮ የሚጣራ ጉዳይ፣ በፖሊስ የተያዘ ጉዳይ፣ የዝርፊያ ሁኔታ ስለሚኖር የእርማቱ ጊዜ እንዲዘገይ ያደርገዋል ብለው ነበር።

በ2012 ፈተና ወስደው በ2013 ዓ/ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በተፈጥሮ ሳይንስ በመደበኛ እና ማታ ወንዶች 380 እና ከዚያ በላይ ፤ ሴቶች 368 እና ከዛ በላይ እንዲሆን መወሰኑ፤ በማህበራዊ ሳይንስ መደበኛ እና ማታ ወንዶች 370 እና ከዚያ በላይ ሴቶች 358 እና ከዛ በላይ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።

በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛ ባልሆነ ፕሮግራም (በማታ፣ ክረምት፣ ሳምንት መጨረሻ፣ ርቀት፣ በኦን ላይ) እና በግል ትምህርት ተቋም በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ አማራጮች ለመማር ወንዶች 330 እና ከዚያ በላይ ሴቶች ፣320 እና ከዚያ በላይ ማስመዝገብ አለባቸው።

* በዚህ የተማሪዎች ጉዳይ ኃላፊዎችን አናግረን ማብራሪያ እንዲሰጡ እናደርጋለን።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

@tikvahethiopia

Report Page