Tikvah-Family

Tikvah-Family


" ችግር በተፈጠረ እና ጥያቄ በተነሳ ቁጥር አጋጣሚውን በመጠቀም የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና ትንኮሳዎችን መንግስት ሊከላከል እና የዜጎችን ደህንነት ሊያስጠብቅ ይገባል " - የቲክቫህ ጂንካ አባላት

ከሰሞኑን በደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጅንካ እና አካባቢው አለመረጋጋት መፈጠሩ ይታወቃል። 

ትላንት በላክንላችሁ መልዕክት ፥ አለመረጋጋቱ የተፈጠረው በአሪ የመዋቅር ጥያቄ ምክንያት ነው።

ከጥቂት ቀናት በፊት በነበረው የደ/ኦሞ ዞን ም/ቤት ጉባኤ ላይ የአሪ በዞን የመደራጀት ጥያቄ በአጀንዳነት አለመያዙ ህዝቡን አስቆጥቶሃል በዚህም ምክንያት ለተፈጠረው ሁኔታ የዞኑ አስተዳደሪ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፤ ውይይቶችም ተደርጓል።

ምንም እንኳን ይህ ቢደረግም አለመረጋጋቱ ተባብሶ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ እስከመጣል ደርሷል። 

በዚህ የአለመረጋጋት ሁኔታ ውስጥ ሁሉም ዜጋ ከጫፍ እስከ ጫፍ የኢትዮጵያ ምድር ባለቤት እንዳልሆነ ሁሉ በአንዳንድ አካላት " ከዚህ አካባቢ አይደላችሁም፤ ከሌላ ቦታ ናችሁ ፤ ማንነታችሁ እንዲህ ነው " በሚል የተሳሳተ አደገኛ አመለካከት የነዋሪዎችን መብት ለመጣስ ተሞክሯል።

ይህ ነገር ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችም የታየ ግን እስካሁን ያልታረመ በየትም ቦታ የመኖር መብትን አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ቀጥሏል።

ችግር በተፈጠረ ቁጥር አይልም ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ከማህበረሰቡ በሚወጡ አንዳንድ አካላት ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ዜጎችን አደጋ ላይ መጣል፣ አጋጣሚውን በመጠቀምም ዜጎች በላባቸው ያፈሩትን ንብረት መዝረፍ ፣ ሰዎችን ማጥቃት ፣ ማፈናቀል የመሳሰሉ ድርጊቶች ከዚህ በፊትም በተለያየ ቦታ ታይቷል።

ከሰሞኑን በጂንካ እና አካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ይኸው ተስተውሏል። ንብረቶች ተዘረፈዋል፤ እሳት ጋይተዋል፤ ሰው ላይም ጥቃት ተፈፅሟል ፤ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለው በመጠላ እንዲያርፉ ሆነዋል።

የሰሞኑን ውጥረት ለማርገብ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ተሰማርቷል።

ከሰሞኑን ሁኔታ ጋር የደቡብ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ፥ የክልሉ መንግስት የአሪን የመዋቅር ጥያቄ ከህልውና ዘመቻው፣ ከሀገር አቀፉ ምርጫ እና ከሌሎች ሀገራዊ ጥሪዎች በኋላ የመፍታት እቅድ አስቀምጦ እንደነበር ገልፀወል።

ይህ የስራ አቅጣጫ ጥያቄዎቹን ካቀረቡት አካላት ጋር ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የአሪ ማህበረሰብ ጥያቄው አሁኑኑ ይፈታ ሲል ክልሉ ደግሞ ቆይ ሲል ጥያቄውን በሀይል ለመፍታት በተደረገ እንቅስቃሴ ምክንያት በጅንካ ከተማ እና ሌሎች አራት ከተሞች ላይ የጸጥታ መደፍረስ ማጋጠሙን አስረድተዋል።

የአሪ ወረዳ ወደ ዞን ማደግ አለበት በሚል የተጀመረው የሀይል እንቅስቃሴ በጅንካ፣ ቶልታ ፣ሜጼር፣ ጋዘር እና ወብ አሪ ከተሞች ላይ የጸጥታ መደፍረስ መከሰቱን ፤ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸዋል።

በተወሰኑ አካባቢዎች በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን እና የሕዝብ መጓጓዣ መንገዶችን ለመዝጋት መሞከሩን ነገር ግን አሁን ላይ ሁከቱን መቆጣጠር መቻሉን ገልፀዋል።

በአካካቢው ያለውን አለመረጋጋ ለመቆጣጠር የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የደቡብ ክልል ልዩ ሀይል እና ፖሊስ ወደ አካባቢዎቹ መግባቱንም አሳውቀዋል።

በአካባቢዎቹ በሚኖሩ በሌሎች የማህበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ ነው ስለሚባለው ጉዳይ “በጅንካ ፣በቶልታ እና በሜጸር ከተሞች የቡድን ጸቦችን ለማስነሳት ተሞክሮ ነበር ይሁንና ጉዳዩን በቁጥጥር ስራ ማዋል ተችሏል” ብለዋል።

በዞኑ በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ በሰዎች ላይ እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ቢገልፁም በቁጥር ያስቀመጡት ነገር እንደሌለ ከአል ዓይን ኒውስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የጂንካ እና አካባቢው የቲክቫህ አባላት አሁንም በአካባቢው ያለው ሁኔታ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው አስገንዝበው አጋጣሚውን በመጠቀም በዜጎች ላይ የሚፈፀምን ማንኛውም ጥቃት ሆነ ትንኮሳ መንግስት እንደመንግስትነቱ መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።

የቦታው ችግር በተፈጠረ ቁጥር ከዚህ አይደለህም በሚል ስርዓት የሌለው አመለካከት ዜጎች ተንቀሳቅሰው የመኖር እና የመስራት መብታቸው መገደብ የለበትም ይህን በማያደርጉት ላይም አስፈላጊው ማስተካከያ መደረገግ አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል።

@tikvahethiopia

Report Page