Tikvah-Ethiopia

Tikvah-Ethiopia

Eyob Tekuye

የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ፦

" የፕሪቶሪያው ስምምነት ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ አይችልም። የማይችልበት ዋናው ምክንያት አሳታፊ ስላልነበረ ነው " - አቶ ታደለ ደርሰህ

" የፕሪቶሪያው ስምምነት ህጸጾች ቢኖሩበትም ዘላቂ ሰላም ያመጣል " - አቶ አበበ ገ/ህይወት


የፕሪቶሪያው ስምምነት ዘላቂ ሰላም አስተዋፅኦ ያደርጋል ? ወይስ አያደርግም ? በሚሉት ነጥቦች ክርክርና ውይይት እንዲደረግ ከUSAID በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ " ሀበጋር " (የደበበ ኃ/ገብርኤል የህግ ክርክር ፕሮግራም) ባለፈው ቅዳሜ አንድ የውይይት እና ክርክር ዝግጅት አዘጋጅቶት ነበር።

በመድረኩ የተጋበዙ ምሁራን፣ የሕግና የፖለቲካ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች በየፊናቸው ሀሳብ ሲሰጡ፣ የተለያዩ ጥያቄዎችንም ሲሰነዝሩ ተስተውለዋል።

የታሪክ ምሁርና የቀድም የአብን ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) የፕሪቶሪያው ስምምነት " ዘላቂ ሰላም አያመጣም " በማለት፣ እንዲሁም የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበበ ገ/ህይወት " ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም ያመጣል " በማለት ክርክር አድርገዋል።

ተሳታፊዎችም በየፊናቸው በአንድ ወገን ያሉት ስምምነቱ ከነችግሩም ቢሆን ዘላቂ ሰላም ያመጣል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ስምምነቱ አሳታፊና ግልፅኝት፣ ተጠያቄነት መርሆችን ካላሟላ ዘላቂ ሰላም ሊመያመጣ አይችልም፣ ቀድሞውንም አሳታፊነትና ግልጸኝነት የጎደለው ነው በማለት ሀሳባቸውን አቅርበዋል።


ቲክቫህ ኢትዮጵያ በበኩሉ የፕሪቶሪያው ስምምነት በእስካሁኑ አካሄዱ ዘላቂ ሰላም ያመጣል? ወይስ አያመጣም? መፍትሄውስ ምንድነው? በሚሉትን ጥያቄዎች ምን ምላሽ እንዳላቸው ምሁራንን አነጋግሯል።

የቪዢን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ ፦


- የፕሪቶሪያው ስምምነት ዘላቂ ሰላም #ሊያመጣ አይችልም። የማይችልበት ዋናው ምክንያትም አሳታፊ ስላልነበረ ነው።

- የፕሪቶሪያው ስምምነት፣ በሁለቱም ወገን ያሉ ተደራዳሪዎች የሚደራደሩበት ነገር ግለፅነትን፣ ተጠያቂነትን፣ ሕዝብን አሳታፊነትን፣ ፍላጎትና ቁርጠኝነትን መሠረት ያደረገ መሆን መቻል ነበረበት። 

- ሕዝብ አለመስማቱን እያየነው ነው፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመካሄዱ በፊት ሕወሓትና የኢትዮጵያ መንግሥት #በስውር ይወያዩ ነበር። ይሄ ለምን አስፈለገ ? የምንወያየው ኢትዮጵያ ለሞትባል ለአንዲት አገር ሕዝብ ነው አይደል ? ከሆነ በስውር የሚካሄድ ውይይት ለምን አስፈለገ ? ከሕዝብ #መደበቅ የለበትም ነበር።


የታሪክ ምሁርና የቀድም የአብን ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) ፦

- የፕሪቶሪያው ስምምነት ዘላቂ ሰላም አያመጣ። ለዚህም የሚከተሉትን አምስት ምክንያቶችን እጠቅሳለሁ ፦

* አንደኛ የተራዳሪዎችንና የአደራዳሪዎች #የተዓማኒነት ችግር ጥላ አጥሎበታል፣ በሂደትም፣ በውጤትም፣ በአፈጻጸምም።

* ሁለተኛ የድርድሩ #አካታች አለመሆን በተለይ ደግሞ ዋና የጦርነት ተዋናይ የሆኑ ኃይሎችን፣ የራሳቸው የደህንነት ጥያቄና ስጋት ያላቸውን ሳያካትት በሁለት ወገኖች ብቻ የተደረገ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ መሰናክል ይሆናል።

* በሦስተኛ ደረጃ መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን ለምሳሌ፣ #ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ፣ የአከራካሪ #ግዛቶች ጉዳይ፣ እንዲሁም የፍትህና የሕግን ጉዳይ በስርዓቱ ያልዳሰሰ ወይም #አግበስብሶ ያለፈ በመሆኑ ችግሮ ይፈጥራል።

* አራተኛ አፈጻጸምና አወሳሰድን በተመለከተ ግልፅ የሆነ ስርዓት ያላስቀመጠ በመሆኑ ይሄም አሁን እንደምናየው ሁሉ ነገር እየተጓተተ፣ አንዳንዴም ጭራሽ እስከነአካቴው #የማስፈጸሚያ መንገድ ስለሌለው አንዱ ችግር ነው።

* አምስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ #የጋራ ብሔራዊ ራዕይ የሌለው ወይም ያንን የሚያመላክት አይነት #የሁለት ወገኖች ብቻ ድርድር በመሆኑ ለዘላቂ ሰላም እምብዛም ፋይዳ የለውም ብለዋል።


የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜአዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበበ ገ/ህይወት ለኢንተርቪው ፈቃደለኛ ባይሆኑም፣ ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ የፕሪቶሪያው ስምምነት በትግራይ ክልል የነበረውን #ጦርነት እንዳስቆመ፣ ስምምነቱ ችግሮች ቢኖሩበትም ጦርነት በነበረበት ወቅት በችኮላ እየተደረገ እንደመሆኑ መጠን መፍትሄ እንዳስገኘ አስረድተዋል።


አማራ ክልል ስላለው ወቅታዊ ጦርነት ምን ተባለ?

ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)፥

- ኢንተረስቲንግ የሆነው ነገር የፕሪቶሪያውን ስምምነት የተጠቀሙበትን በግልፅ ጀነራል ፃድቃን አንድ ኢንተርቪው ላይ ' ይሄ የሰላም ስምምነት ለእናንተ ያስገኛችሁ ጥቅም ምንድን ነው?' ሲባሉ፣ 'የኃይል መዛባት ይፈጥርልናል' ብለው ነበር።

- እንዳሉትም ይሄ የኃይል መዛባት ተፈጠረና ጥምር ኃይሎች የነበሩት እርስ በእርሳቸው እንዲዋጉ የተደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የአማራ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥት ጋር ጦርነት የገጠሙት የኃይል ማዛባት ሥራ ስለተካሄደበት ነው። አንዱ ግልፅ የሆነ ሸፍጥ የተካሄደበት ስምምነት ነው። 

- ሁለተኛው ሸፍጥ የናይሮቢው መግለጫ የሚባለው ነው። የናይሮቢው መግለጫ በመሠረቱ ከዋናው ስምምነት ያልተቀዳ ነው።


አቶ ኃይለልዑል ምስጋናው (ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት)

- የአማራ ክልሉን ጦርነት በትክክል ፕሪቶሪይው ስምምነት የወለደው ነው። ምንም የሚያሻማ ነገር የለውም።

- ለዚህ መረጃ የምናስቀምጠው የፌደራሉ መንግሥት 'ልዩ ኃይል ይፍረስ' የሚለውን አስተሳሰብ ያመጣው ወይም ደግሞ ለማድረግ የተነሳው መቼ ነው ብለን ስናስብ በሕወሓት በኩል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ነው። 'ክልሎቾ እርስ በእርስ ተገዳዳሪ እየሆኑ ነው' የሚል ሽፋን ነው እየተሰጠው ያለው።

- ለዚህ 'ከተለያዬ አቅጣጫዎች የደህንነት ስጋት አሉብኝ' ያለው የአማራ ኃይል 'የደህንነት ስጋት ሳይቀረፍ ትጥቅ አልፈታም' ነው እያለ ያለው። 

- ስለዚህ የፕሪቶሪያው ስምምነት የሕወሓትን ጦርነት ለማስቆም ከመሄዱ ባለፈ የፌደራሉ መንግሥት ቀጣይ ሊገቡኝ ይችላሉ ያላቸውን ስጋቶች ሕወሓት ላይ ተመስርቶ ያመጣው አዲስ ልዩ ኃይልን የማፍረስ አ ጋጣሚ የተፈጠረ ችግር ነው።


አቶ ኪሩቤል ሀሳብ (ከሳልሳይ ወያነ ፖርቲ)፦ 

- 'ለሰሜኑ ጦርነት ሕገ መንግሥቱ ነው መነሻው ይላሉ' በሌላ በኩል ደግሞ 'የትግራይ ጦርነት በመቆሙ አማራ ላይ ጦርነት ቀስቅሷል' ይላሉ በመሠረቱ ሰሜኑ ላይ ጦርነት የተነሳው ፌደራል መንግሥት ካስቀመጠው አኳኋን እንዴት ነው የሚያዩት?

- ሕገ መንግሥቱ ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ የትኛው ሕገ መንግሥት? የትኛው ድንጋጌ ስለተሻረ? ስለዚህ ይሄ ጦርነቶ መቆም የነበረበት በየትኛው ሕግ አግባብ ነው?

- ካልሆነ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት እንዲቆም ካልተደረገስ በየትኛው ማዕቀፍ ነው ታዲያ ይሄ ጦርነት ሊቆም የሚችለው? በሌላ አነጋገር የትግራይ ጦርነት ቆሞ የአማራ ጦርነት ቀጠለ የሚባልበት የሕግ አግባብ በየትኛው አመክንዮ ነው? ከምን አነሰጻር ነው የሚገናኙትስ? ሲሉ ጠይቀዋል። 


የትግራይ ክልል ጊዜአዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበበ ገ/ህይወት ፦

J

- አንድ ምሳሌ ልንገራችለሁ ትጥቅ መፍታትን በተመለከተ ትግራይ ውስጥ በየደረጃው እየተገመገመ ነው። ዛሬም ላይ እየተነሳ ነው ያለው። ይሄ እኮነው ዲሞክራሲን ማዕከል ያደረገን ጥያቄ ማንሳት የሚያስከትለው።

- ትጥቅ ካልፈቱ መፍታት አለበት የሚለው ነገር አፅንኦት ተሰጥቶበት፣ ሕዝብም አምኖበት እንዲሄድ ማድረግ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ነው።

- ጦርነትን ማስቆም ነበር የፕሪቶሪያው ስምምነት አላማ ተሳክቷል። ሆት የሆነ ጦርነት ነው ያስቆመው። ትግራይ ስለተሳካ እዚህ የሚቆጨን ሰዎች አለን?

- የፕሪቶሪያው ስምምነት የአማራን ጦርነት ወለደ የሚል አመለካከት በጣም ከባድ ማጠቃለያ ነው። አማራ ክልል የተፈጠረውን ሁኔታ መተንተን ያስፈልጋል። አማራ ክልል ያለውን የፖለቲካ ጥያቄ ማየት ያስፈልጋል።

- የፕሪቶሪያው ስምምነት ኮንስቲቱሽናል ኦርደርን ሪስቶር ማድረግ ነው።


ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) (የታሪክ ምሁር እና የቀድም የአብን ብሔራዊ ጽ/ቤት ኃላፊ)፦


- የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነት አላስቆመም። ትግራይ ላይ ጦርነት ቢቆምም አማራ ክልል አሁንም ጦርነት አለ። ያ የፕሪቶሪያው ስምምነት ቀጥተኛ ውጤት ነው። ምክንያቱም የትጥቅ ማስፈታት ጉዳይ TDF ትጥቅ ሳይፈታ 'የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ይበተን' ማለት ከጋሪው ኋላ እንደማድረግ ማለት ነው። ስለዚህ ይሄ ትክክል አይደለም። 

- ዋናው ነገር የደህንነት ስጋቶችን አልቀረፈም። አሁን የምናየው በሁለተኛው ደረጃ የተነሳው የአማራ ክልል ጦርነት አንድም ስርዓቱ እውነተኛ የሆነ የሰላም ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ ቀጥታ ሰላምን የሚያደፈርስና ጦርነትን የሚያጭር ነገር ከመግባባት ይልቅ ቁጭ አድርጎ ሁሉንም ወገኖች አወያይቶ አስፈላጊውን የደህነት ዋስትና መስራት ይቻል ነበር።

- ነገር ግን አሁን የተደረገው ነገር ትግራይ ላይም በኃይል፣ አማራ ላይም በኃይል ማስፈጸም ነው። አሁንም የኃይል ማስፈጸም ስልት አልቀረም ማለት ነው። ስለዚህ አሁን አማራ ላይ ያለው ጦርነት የዛ ቀጥተኛ ውጤት ነው።

- የፕሪቶሪያው ስምምነት ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ አካታች፣ ሰላም ፈላጊ እንዲሆን በድጋሚ መቃኘትን ይሻል።


የራያና ወልቃይት ጉዳይ ተፈናቃዮች ፦

ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)

- የራያና የወልቃይት አካባቢዎችን ተፈናቃዮችን በተመለከተ የራያንም ጉዳይ በቅርበት እከታተላለሁ። አብዛኛዎቹ ተመልሰዋል። እንዲመለሱም በሩ ክፍት ነው። የአካባቢው አስተዳደርም እንዲመለሱ ግፊት እያደረገ እንደሆነ አውቃለሁ።

- የተቀሩት መያዣ ሆነው ነው የቀሩት። አንዱ ትልቁ ችግሩ የሰላም ስምምነቱ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው እንዳይመለሱ መያዣ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። ይሄ በውል መታወቅ መቻል አለበት። 

- በሰላም ስምሞነቱ የተገቡ ግዴታዎች በሁለቱም ወገኖች እየተፈጸሙ አይደለም። ያ ባለበት እንዴት ሆኖ ነው ሰላም ሊመጣ የሚችለው? በትግራይም በአማራም ድጋፍ ደርሷል ወይ? ራሳቸው ካድሬዎች፣ በአካባቢው ያሉ ባለስልጣናት ዘርፈውት ድጋፉ አልቆመም ወይ? 

- በስምምነቱ መሠረት ራሱ ጊዜያዊ አስተዳደሩ መቋቋም የነበረበት ከሁሉም ያገባኛል ከሚሉ ወገኖች የተውጣጣ ነው መሆን የነበረበት። ነገር ግን አሁን ሁሉንም ትህነግ ተቆጣጥሮት ሰላማዊ ሰልፍ እንኳ የማይፈቀድበት ሁኔታ ተፈጥሮ የባሰ ችግር እየሰፋ አይደለም ወይ? የሚለው ታሳቢ መደረግ አለበት።


የቀድሞ ትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አበበ ገ/ህይወት ፦

- ዘረፋዎች ታይተዋል። አሁንም መንገዳገዶች አሉ። እነዚህን መንገዳዶች ግን ለማስተካከል ነው መሞከር ያለብን።

- ሌቦች አሉ። ከተራበ ሰው የሚዘርፉ ሌቦች ተጠያቂ መደረግ አለባቸው። ችግሩ ስላለ ግን የፕሪቶሪያው ስምምነት ያመጣው ነው በሚል አልረዳውም።

- ስምምነቱ ሲፈጸም የሪከቨሪ ሥራ፣ የሪካውንስሌሽን ሥራ እንዲሰራ በጀት ተመድቧል። (የፌደራል መንግሥት 20 ሚሊዮን ብር አሎኬት አድርጓል፤ 300 ሚሊዮን ዶላር ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ) እሱን እያስተባበርን ርዳታ የማይደርስባቸው የነበሩ የዋግኽምራ ሰቆጣ አካባቢዎች እንዲሄድ የማድረግ ሥራዎች ሲሰሩ ነበር። ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም።

- ዋስትና መስጠት፣ ማረጋገጥ ይጠይቃል። ምክንያቱም የሰላም ስምምነት ከሆነ የዋስተና ማምጣት ሥርዓቱ ምን መሆን አለበት? ሕዝቦች ወደ ቄያቸው የሚመለሱ ከሆነ ዋስትናው ምንድን ነው? ሥጋቶች ስላሉ እዚህም እዛም ሥጋትን አቮይድ ለማድረግ ደግሞ ሞኖፖሊ ኦፍ ፖወር ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

- አንድ አገር ውስጥ ኃይል መያዝ ያለበት መንግሥት ብቻ ነው። ሌላ አካል ኃይልን በማዕከላዊነት እይዛለሁ የሚል ከሆነ ይሄ መስተካከል አለበት። ማረጋገጥ ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነት ነው።


መረጃው በአ/አው የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ኢዮብ ትኩዬ የተዘጋጀ ነው።

Report Page