Tikvah-Ethiopia

Tikvah-Ethiopia


በሕዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውና መንግሥት "ሸኔ" ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አማካኝነት ከአምስት ዓመታት በላይ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች በሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ወደ አማራ ክልል በመሸሽ ተጠልለው የሚገኙና ገና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተፈናቃዮችን ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ቄየዎቻቸው የመመለስ ሥራ ለመስራት ሰሞኑን ባህር ዳር ከተማ ላይ ተደረገ በተባለ የጋራ ውይይት ስምምነት ላይ መደረሱን የሁለቱም ክልሎች የኮሚዩኒኬሽን ቢሮዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ማብራሪያ፣ "የታሰበው በጸጥታ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ከክልላችን ተፈናቅለው አማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን መልሦ የማቋቋም ሥራ ነው" ብለዋል።

አክለውም፣ "በጸጥታ ምክንያት ከኦሮሚያ ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመመለስ አብይ ኮሚቴው በሚቀጥለው ሳምንት ተገናኝቶ መሪ ዕቅዱን ያወጣል" ሲሉ አስረድተዋል።

የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን አሰፋ በበኩላቸው፣ "ሁለታችን ተቀናጅተን ለመስራት የሚቀጥለው ሰኞ ቀጠሮ ይዘናል። በዛ መሰረት ታይም ቴብሉን እናስቀምጣለን መቼ ይመለሱ? መቼ ወደዛ እናጓጉዝ ? የሚለው በቅዳችን ነው የሚመለሰው" ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለአብነትም በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከአሥር በላይ ቀበሌዎች፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ታጣቂ ቡድኑ በንጹሐን ላይ ግድያ እየፈጸመ መሆኑን ነዋሪዎች እንደገለጹ፣ ይህ በእንዲህ እንያለ ተፈናቃዮች ቢመለሱ ለደኅንነታቸው ምን ዋስትና ይኖራቸዋል? የሚል ጥያቄ ቲክቫህ ኢትዮጵያ አቅርቧል።

አቶ ወንድወሰን ለዚሁ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ "የጸጥታ ችግር እያለ እኛም እዲመለሱ አናደርግም። በኦሮሚያ ክልል በኩልም የጸጥታ ችግሩ አስተማማኝ ደረጃ ሳይዘልቅ ተመላሾቹ ለዳግም ችግር የሚጋለጡበትን መገድ ሁለታችንም አንሰራም" ብለዋል።

አክለውም፣ "ሰሜን ሸዋ አካባቢ ያለው የጸጥታ ችግር ወጣ ገባ የሚል ነው እናተም እደምታውቁት አማራ ክልልም የጸጥታ ችግር አለ። ይህን በዘላቂ መፍትሔ ይሰጠዋል ብለን ነው የምናስበው፣። ሆሮ ጉድሩ ያለውም ቢሆን አሸባሪው ሸኔ ወጣ ገባ እያለ ችግር ሊፈጥር ይችላል" ብለው፣ በቅድሚያ የጸጥታውን ችግር የምረጋግጥ ሥር እንደሚከናወን አስረድተዋል።

አቶ ሀይሉ አዱኛ በበኩላቸው፣ "የጸጥታው ችግር በተረጋገጠባቸው አካባቢዎች የማስፈሩም መልሶ የማቋቋሙም ሥራ ይሰራል። የጸጥታ ችግር ያልተረጋገጠበት አካባቢዎች ደግሞ እያረጋገጥን ነው መልሰን የምናቋቁመው፣ ዛሬ መልሰን ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን ነው የሚሰራው" ሲሉ ተናግረዋል።

የሁለቱም ክልሎች ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለስልጣናት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በገለጹት መሠረት፣ ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት ኦሮሚያ ክልል ከመመለስ በፊት ይህን ሥራ ለማስኬድ የተዋቀረው አብይ ኮሚቴ መረጃዎችን ያጠራል።

የሁለቱም ክልሎች ባለድርሻ አካላት በቀጣዩ ሳምንት ተገናኝተው በሚያወጡት ዕቅድ መሠረት፣ ተፈናቃዮችን ከመቼ እስከመቸ ወደ ቦታው እንዲደርሱ ይደረጋል? እነሱን ከማጓጓዛችን በፊት በኮሚቴው ደረጃ የት ቀበሌ? የት ወረዳ? የት ጎጥ ተፈናቀሉ? ሥራ መለየት፣ ማጓጓዝ ከመጀመሩ በፊት አስተማማኝ መጠለያ እዲኖራቸው፣ መሬታቸው በሌላ አካላት ተይዞ ከሆነ የያዘው አካል በህግ አግባብ ተጠይቆ እንዲመለስ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ እንዲሰራ ይደረጋል ተብሏል።

አቶ ወንድወሰን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ "ከለውጡ ማግስት ከኦሮሚያ ክልል ባሸባሪው ሸኔ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች አሉ። ለረጅም ዓመታት የኖሩ፣ እዛው ተወልደው እዛው ያደጉ፣ ቋንቋቸው ኦሮምኛ የሆነ በማንነታቸው ብቻ የማፈናቀል ሥራ ሰርቷል" ብለዋል።

"መንግሥት አጥፊዎችን በሕግ መጠየቅ አለበት። ከየትኛውም አቅጣጫ ማንም ይሁን ማን አጥፊን በሕግ የመጠይቅ ሥራ ከሰራ ሰላም ማምጣት እንችላለን" ብለዋል።

ከሞት ሸሽተው ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ኦሮሚያ ለመመልስ ፈቃደኛ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል ወይ? በመንግሥት ከታጣቂ ቡድኑ መካከል ተጀምሮ የተቋረጠው ድርድር መቅደም አልነበረበትም ወይ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አቶ ወንደሰን፣ ሥራ በሂድት የሚረጋገጥ እንደሆነ፣ ተፈናቃዮቹ ለመመለስ ፈቃደኛ እንደሚሆኑ፣ ድርድሩ የበላይ አካላትን እንደሚመለከት ገልጸዋል።

ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላችው አቶ ሀይሉ በበኩላቸው፣ ከቄያቸው፣ከንብረቱ ተፈናቅሎ ያለ ሰው ዳግም ወደቄየው መመለስ ይፈልጋል የሚል እምነት አለኝ። ተቸግሮ እንጅ ፈልጎ የመፅዋች እጅ ለመጥበቅ የሚፈልግ ይኖራል ብለን አናስብም" ነው ያሉት።

ጥንቅሩ በአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።

@tikvahethiopia

Report Page