Tikvah Ethiopia

Tikvah Ethiopia

Tikvah Ethiopia Family Addis AbabaJuly 11, 2024

" ሚዲያዎች የመንግስት ፣ በተለይ የኔ ደጋፊ መሆን አይጠበቅባችሁም " - ጠቅላይ ሚኒስትሩ

ትላንትና በኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ለሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ተቋማት የእውቅና መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር።

በዚህም በሀገሪቱ ውስጥ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ሁሉም አይነት የሚዲያ አካላት በስነርዓቱ ላይ ታድመዋል።

አዘጋጅቶት የነበረው የመንግስት የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሲሆን በመድረኩ የተለያዩ ሚዲያዎችን " አውጥቼዋለሁ " ባለው መስፈርት ሸልሟቸዋል።

ስለሽልማቱ ማብራሪያ የሰጡት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ፈቃድ ኖሯቸው ከሁለት ዓመት በላይ የሰሩና የምዘናውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ 69 የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች መሳተፋቸውን አንስተዋል።

" ከ69ኙ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች 11ዱ መስፈርቱን አሟልተው ተገኝተዋል። ቀሪዎቹ ከመስፈርት #በጣም_የወረደ ደረጃን ይዘዋል። " ሲሉ ከሽልማቱ በፊት ባደረጉት ንግግር ተናግረዋል።

በመንግስት ከተሸለሙት ውስጥ ኢቢሲ፣ ፋና ፣ ኢፕድ ፣ አሚኮ ፣ ኦቢኤን ፣ ዋልታ ፣ ኢዜአ ፣ አዲስ ሚዲያ፣ EBS  በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ሽልማታቸውንም ከጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እጅ ተቀብለዋል።

ከሽልማቱ መገባደጃ በኋላ ሸገር ኤፍ ኤም፣ ፎርቹን ጋዜጣ፣ " ሽልማቱ ባሉበት ይደርሳቸዋል " በሚል ስማቸው በመድረኩ ተነስቷል። ቲክቫህ እና ድሬ ትዩብ በበየነ መረብ ከሚሰሩ ተቋማት መካከል እንደሆነ ስማቸው ተነስቶ በስም ደረጃ እውቅና ቀርቦላቸዋል።

በዚሁ ስነስርዓት ላይ የተገኙት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያዎች በሀገር ጉደይ ላይ መስራት እንዳለባቸው ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስቀድሙ ፣ በመከባበር ሰላምንና ፍቅርን ላይ እንዲተጉ ጠይቀዋል።

" ሚዲያዎች የመንግስታት ደጋፊ መሆን አይጠበቅባችሁም ፤ በተለይም የኔ ደጋፊ መሆን አይጠበቅባችሁም የሚጠበቅባችሁ እውነትን ብቻ መግለጥ ነው " ብለዋል።

" የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም እውነትን መግለጥ ከቻላችሁ ሚናችሁን በደምብ ተወጣችሁ ማለት ነው " ሲሉ አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሽልማቱ ላይ ሊሸለሙ ይገባቸዋል ብለው የሚጠብቋቸው ተቋማት እንደነበሩ ግን እንዳልተሸለሙ ገልጸዋል። 

ከነዚህም አንዱ ' የኪንግ ኦፍ አባይ ' የዩትዩብ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል እንደሆነ ተናግረዋል።

" ኡስታዝ ጀማል ልክ ደመወዝ እንደሚፈላቸው ጋዜጠኞች ነጋ ጠባ በአረብኛ ኢትዮጵያ ላይ የሚሰራጨውን መርዝ በአማርኛ እየተረጎመ ስለ ኢትዮጵያ የሚጣበቅ ጀግና ነው " ብለውታል።

" ግለሰቡ ብቻውን ለእኔ EBC ነው " ሲሉ አወድሰውታል።

እንዲህ አይነት ስለ መንግስት ሳይሆን ስለ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ብቻ ቆመው የሚታገሉ ሚዲያዎችን ማበረታታት ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ " የኢትዮጵያ ሚዲያዎች አንዳንዶቹ ሆን ብለው ሌሎች ደግሞ ሳይገባቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የቆመን ሀሳብ ያራምዳሉ " ሲሉ ገልጸዋል።

የአጀንዳው ምንጭም ግራ እንደሚያጋባ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሚተላለፉ መረጃዎች " ብሔራዊ ጥቅምን ታሳቢ ማድረግ አለባቸው ፤ የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ የማይከቱ መሆን አለባቸው " ብለዋል።

" ያደገ ሀገር ሲኖር ነው ያደገ ሚዲያ የሚኖረው በሀገር ጉዳይና እድገት ላይ በጋራ ፣ በትብብርና በስምምነት መስራት ይገባናል " ሲሉ ገልጸዋል።

" የእውቅና መርሀ ግብሩ ሙሉ ላይሆን ይችላል " ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ " ለሚዲያ እውቅና ሰጥተን ስለማናውቅ ባልተገባ መንገድ እውቅና ሰጥተን ሊሆን ይችላል የቀራችሁ ሚዲያዎች መጀመራችን በራሱ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ተገንዘቡልን " ሲሉ ተደምጠዋል።

" በቀጣይ እየታረመ ይሄዳል "ም ብለዋል።


በማህበራዊ ሚዲያ ከሽልማቱ በኋላ በርካቶች አስተያየታቸው ሲሰጡ ታይተዋል። 

ሽልማቱ የመንግስት ልሳን የሆኑትን ሚዲያዎች መርጦ የሸለመ ነው በሚል ኮንነዋል።

" መንግስት እንዴት የመንግስትን ድምፅ ብቻ ቀን ሙሉ የሚያሰሙ ሚዲያዎችን መርጦ ይሸልማል ? ተቃራኒ ሃሳብ የማያስተናግዱ፣ የህዝቡን ችግር አውጥተው የማይናገሩ ሚዲያዎችን በምን መስፈርት ተሸለሙ ? ለህዝብ ድምጽ የሆኑ ሚዲያዎች ለምን ሽልማትና እውቅና ተነፈጋቸው ? " የሚሉት ከአስተያየቶቹ መካከል ናቸው። 

ሌሎች ከዚህ በተቃራኒ አስተያየት ሰጪዎች " በመርሀግብሩ እንደተደሰቱ፣ መሰል መርሀግብር መለመድ እንዳለበት ለሀገር ጥቅም መቆም እንደሚገባና ይህም ክብር የሚያሰጥ እንደሆነ ለሌላው ማስተማሪያ እንደሚሆን ፣ ስለ ሀገግ ጉዳይ መስራት ማለት የመንግስት አፍ መሆን እንዳልሆነ " ጽፈው ተመልክተናል።

#TikvahEthiopiaAA

@tikvahethiopia


Report Page