Tikvah-Ethiopia

Tikvah-Ethiopia


🇪🇹የፓለቲካ ፓርቲዎች ምን ይላሉ?🇪🇹

“ ሁለት ወራት ከ18 ቀን ነው መተከል የቆየሁት አንድ ቀን መብራት አልበራም ” - ዶ/ር መብራቱ አለሙ

የኢትዮጵያ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ፣ የቦሮ ዲሞክራሲ ፓርቲ የውጪና ዓለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊ፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር መብራቱ አለሙ የቦሮ ዲሞክራሲ ፓርቲን ወክለው ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።


Q. ህዝቡ ስጋት እንዳለበት ሲገልጽ ይስተዋላል። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሁንም የታጠቁ ኃይሎች ይንቀሳቀሳሉ እንዴ ? 

ዶ/ር መብራቱ አለሙ ፦

“ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በየጊዜው ‘የታጠቁ ኃይሎች አሉ’ ይባላል በየቦታው። 

በዬጊዜው የክልሉ መንግስት ከእነርሱ ጋር ‘ድርድር አድርጌአለሁ’ እያለ መግለጫ ሲሰጥ እናያለን። አሁንም ግን የጸጥታ ስጋት ያለባቸው ቦታዎች አሉ። 

ምርጫ ያልተደረገባቸው ቢያንስ ወደ 40 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ። የሥጋት ቀጠናዎች አሉ የታጠቁ ኃይሎች ያሉባቸው።

አሁንም በዚያ ዙሪያ ሰፊ ሥራ መስራት ያስፈልጋል። ከድሮው ግን መሻሻል ታይቶበታል። 

ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ዘላቂ ሰላም ሰፍኗል ማለት አይቻልም። መተከል ዞን ከአማራ፣ ከሱዳን ድንበር፣ ከወለጋ ጋር ሰፊ ድንበር ይዋሰናል። 

ስለዚህ በተለይ በሰላምና ጸጥታ ላይ 

የሚሰሩ ብዙ ፕሮጀክቶች ያስፈልጉታል። መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት።”


Q. በክልሉ ከዚህ ቀደም ታጣቂዎች ዘርፈ ብዙ ውድመት ማድረሳቸው ይታወሳል። ለመሆኑ የወደሙ መሠረተ ልማት ለማህበረሰቡ ተሟልተውለት ይሆን ?

ዶ/ር መብራቱ አለሙ ፦

“ በዚህ ምርጫ ህዝባችን በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ለማየት ሞክረናል። ሁለት ወራት ከ18 ቀናት ነው መተከል የቆየሁት አንድም ቀን መብራት አልበራም።

ኤሌክትሪክ ከተዘረጋ ወደ 10 ዓመታት ይሆነዋል፤ ግን ከግጭቱ በኋላ መሠረተ ልማቶች ተመልሰው አልተገነቡም። ጨለማ ውስጥ ነው መተከል ያለው።

ገዢው ፓርቲ (ብልጽግና) ደግሞ የሚበራ አምፓል ነው ያቀረበው ለምርጫ እንኳ ምልክት አድርጎ። 

‘የቆመ ፓል እንጂ የሚበራ አምፓል የለም’ እያሉ መፈክር ያሰሙ ነበር የኛ የፓርቲ ደጋፊዎች።

የሚጠጣ ንጹህ ውሃ የለም፤ መንገድ የለም። መተከል ዞን ማለት የህዳሴው ግድብ፣ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሰፋፊ መሬት፣ ከሱዳን ጋር ረጅም ድንበር ያሉበት ዞን ነው።

ይህ ዞን እንግዲህ የመልካም አስተዳር፣ የመንገድ እጦት አይገባውም። የተማረ የሰው ኃይል አለው። ይሄ ማለት በክልሉ የLeadership ክፍተት አለ። 

ይሄን ደግሞ የገዢው ፓርቲም ቢሆን አይቶ እልባት እንዲሰጠው እንደ ፓርቲ ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን። የክልሉ መንግስት በተለይ መሠረተ ልማት ላይ ኮሚቴ አቋቁሞ በደንብ መስራት እንዳለበት ይሰማኛል።

በተረፈ ብዙ ችግሮች አሉ። በመልካም አስተዳደር፣ በሙስና (በተለይ ማዕድን ያለበት አካባቢ ላይ)፣ የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድ በጣም ከፍተኛ ነው። ይሄ ሁሉ ችግር ተደማምሮ ህዝቡ ችግር ላይ ነው።”


Q. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ሰሞኑን የተደረገው ምርጫ ሂደት ምን ይመስል ነበር ? ማንስ አሸነፈ ?

ዶ/ር መብራቱ አለሙ ፦

“ 2013 ዓ/ም ላይ በነበረው ምርጫ እንወዳደራለን ብለን እንቅስቃሴ አድርገን ነበር፤ በወቅቱ ብዙ አመራሮች እስር ቤት ነበሩ።

አስፈትተን ወደ ምርጫ ልንገባ ቅስቀሳ ላይ እያለን የመተከል የጸጥታ ችግር ተከሰተ። ብዙ ሰዎች ተጎዱ ንብረት ወደመ። 

አሶሳ ብቻ ተካሂዶ ከሚሽና መተከል ምርጫው ሳይካሄድ ቀረ። እኛም እንደ ፓርቲ ምርጫ እንዲደረግ ምርጫ ቦርድን ጎትጉተን ፓርላማውም፣ ምርጫ ቦርድም ፈቀዱ።

አዳራሽ ክልከላ፣ አባላትን ማስፈራራት ነበር። የምርጫው ቀን ጫናዎች ነበሩ። እኔ የተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ምርጫ ክልል ላይ እንዲሁም፤

3 የፓርቲያችን እጩዎች ለክልል ምክር ቤት ጊዚያዊ ውጤት የሚያሳይ እንደዚያ ነው የተለጠፈው። እኔ እንደተወካዮች ምክር ቤት አለፍኩኝ።”


Q. ከምርጫ መልስ በጉዞ ላይ እያሉ ስለደረሰብዎ ገጠመኝ ትንሽ ቢሉና ለሌሎች ጥንቃቄ እንዲሆን ሀሳብ ቢያጋሩ?

ዶ/ር መብራቱ አለሙ ፦

“ እኛ ጋር ሲወዳደሩ የነበሩ ብዙ የክልሉ አመራሮች ማሸነፌ አላስደሰታቸውም። በፍጹም ሊቀበሉ ያልቻሉ የዚያው አካባቢ የእኛው ልጆች አሴሩብኝ።

ወደ አርባ ምንጭ ለማስተማር መመለስ ነበረብኝ። ከዞኑ ወደ አሶሳ ለመሄድ አንድ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን መኪና ሹፌር ተባበረኝ።

ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ጉዞ ወደ አሶሳ ጀመርን። ማንኩሻ ከተማ ለቁርስ ደረስን። ምርጫ ላይ የወደቀ ባስልጣን የሚሄድበት መኪና ካለሁበት ተከታታይ ይጓዝ ነበር። 

እየሄድን እያለ የህዳሴው ግድብ መግቢያ አካባቢ ‘አለቃዬ ደውሎ እንዴት ዶክተርን ጭነህ ትመጣለህ? እርምጃ እንወስድብሃለን፤ ከሥራ እናባርራለን’ ተብያለሁ እባክዎ ይውረዱ አለኝ ሹፌሩ።

እዚህማ እንዴት እወርዳለሁ አልኩኝ፤ ወደ 9፣ 10 ጋዜጠኞች አብረውን ነበሩ አገዙኝ። ሹፌሩም ተባበረኝና የህዳሴ ግድብ ጽህፈት ቤት ባለበት ቦታ ጣለኝ።

ወደ የህዳሴ ግድቡ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር በላቸው፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሀሰን ደወልኩ አዘኑ። ታዲያ ሁለቱም ተደዋውለው ጭቃ ስለነበር እንዳልቸገር ጠንካራ መኪና ላኩልኝ።

እኔ ላይ ያሴሩ ሰዎች ጭቃ ይዟቸው አገኘኋቸው። እንደነሱ ክፋት ማሳዬት የለብኝም፤ ለእኔ የተሰጠኝ መኪና ጎትቶ አወጣቸው። በኋላም ሰላም አላሉኝም። እኔም በሰላም ገባሁ። ” ብ

ዶ/ር መብራቱ አገራዊ ጉዳይ እንደ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡት ማብራሪያ በቀጣይ ይቀርባል።

#የፓለቲካፓርቲዎችምንይላሉ? #ቦዴፓ

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia

Report Page