Tikvah-Ethiopia

Tikvah-Ethiopia


ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምን ተፈጠረ ?

በትላንትናው ዕለት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የተፈጠረው ጉዳይን በተመለከተ በርካታ ተማሪዎች እንዲሁም የተቋሙ ሰራተኞች መልዕክታቸውን በመላክ ጉዳዩን አብራርተዋል።

በግቢው የተፈጠረው ጉዳይ መነጋገሪያ ሊሆን የቻለው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተማሪዎች ያሰራጩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ናቸው።

ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ የፀጥታ ኃይሎች በተማሪዎች ላይ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች የሚያሳዩ ናቸው።


ከሁሉም በፊት በግቢው ውስጥ ለተፈጠረው ነገር መነሻው ምንድነው ?

ትላንት ከመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ " ጥያቄ አለን " ያሉ ተመራቂ ተማሪዎች ተቃውሞ ለማድረግ መነሳታቸውን ለማቀው ችለናል።

ተመራቂ ተማሪዎቹ ጥያቄ ያላቸው የመመረቂያ ሁኔታው ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመውጫ ፈተና በኃላ ለሚካሄደው ምርቃት " ምርቃቱ ላይ ለመገኘት የወደቀ ያለፈ መባል የለበትም ፤ አንድ ላይ መመረቅ አለብን ፤ ለ16 አመት ያክል የለፋንበት ፣ ቤተሰብም ብዙ የደከመበት ነገር ነው ይሄ ጉዳይ መልስ ያሻዋል " በሚል ነድ ተቃውሞ ለማሰማት የወጡት።


ከዚህ በኃላ ምን ተፈጠረ ?

ሁኔታውን ተመልክተናል ያሉ #ተማሪዎች ተከታዩን ብለዋል።

ተማሪ አንድ ፦

" እኛ ጥያቄያችንን በሠላማዊ መንገድ ለማሠማት ነው የወጣነው። ግን በፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው እርምጃ በቪድዮው እንደታየው ነው። "

ተማሪ ሁለት ፦

" ትላንት ጥዋት የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተመራቂዎች ተሰባስበው ጥያቄዋቸውን ለማቅረብ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ ጀመሩ።

ተማሪዎች የተሰባሰቡት በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ አቅጣጫ ሲሆን በግቢው ካፌ በኩል ተቃውሞ እያሰሙ ማለፍ ጀመሩ። በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ደህንነት የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎችን ይጠራል። የመጡ የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎችም ተማሪዎችን ለመበተን ይሞክራል ፤ አስለቃሽ ጭስም ይተኩሳል ፤ በዚህም ተማሪዎችን ይበትናል።

ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች የተበተኑ ተማሪዎች ግን ጩኸታቸውን ማሰማት አላቆሙም ፤ በኃላ የተማሪዎቹ ተቃውሞ ሲቀጥል ተጨማሪ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ግቢ ውስጥ ገቡ። ሁኔታውን ለማስቆምም ተኩስ ከፈቱ።

ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን ጥያቄ በህጋዊ መንገድ መስማት ባለመቻሉ ተማሪዎች ለኮንስትራክሽን ስራ በተቀመጡ ድንጋዎች መንገድ መዝጋት ይጀምራሉ። በዚህ ወቅት ነው የፀጥታ ኃይሎች ወደ ዶርምተሪ በመግባት ከተቃውሞው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ተማሪዎች ጭምር ዶርም በመስበር የመቱት፤ የገቡት ወደ ወንዶች ዶርም ብቻ ሳይሆን ወደ ሴቶችም ነው።

ይህ ሁሉ በሚሆን ሰዓት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ምንም ለማለት አልፈለገም፤ ይልቅም ከፀጥታ ኃይሎቹ ጎን ነበር። ከሰዓታት በኃላ ግን አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ምንም ነገር እንዳላደረጉ አመልክተዋል።

የተመቱ ተማሪዎች አሉ ፣ ይህ ብቻ ሳይሆን በተፈጠረው ሁኔታ ስልክ፣ ኮምፒዩተር፣ የግል ንብረቶች ተሰርቀዋል። "

ተማሪ ሶስት ፦

" ትላንት ተማሪዎች ያደረግነው ሰላማዊ ሰልፍ ነው ፤ ነገር ግን የፀጥታ ኃይሎች ተማሪዎችን መምታት ጀመሩ።

ፖሊስ ከተማሪ ጋር በፈጠረው ፀብ ጥዋት የተነሳው ፀብ የቆመው ከሠዓት ነው። ፖሊስ የተማሪ ዶርም ድረስ በመምጣት አስለቃሽ ጪስ ተማሪ ላይ ለቋል። ተማሪዎችም ተመተዋል።

የሴቶችና ወንዶች ዶርም ጎን ለጎን ነው ወንዶች ሲደበደቡ ሴቶች ጮሀው ስያስቸግሩ ሴቶች ዶርምም ገብተዋል። "

ተማሪ አራት ፦

" የፀጥታ ሀይሎች ተማሪዎች ላይ የወሰዱት እርምጀ ፍፁም ህግን ያልተከተለ እና ኢ-ሰብአዊ ነው። አስለቃሽ ጭስ ሲተኩሱ፣ ያገኙትን ሲደበድቡ ነበር። በሰልፉ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸውን ተማሪዎች ዶርም ድረስ ሰብረው ገብተው ደብድበዋል። "

ተማሪ አምስት ፦

" እኔም በመስኮት እያየሁ ነበር። የሁለተኛ አመት የዋቸሞ ተማሪ ነኝ። ተማሪ በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብት አለው።

እኔን የገረመኝ ገና ተማሪዎች ወደሰልፉ ከመውጣታቸው በተኩስና በአስለቃሽ ጭስ ግፉ ሲልም እንደሚታየው በድብደባ መለሱን።

እኔ የወንዶቹ ሲገርመኝ የሴቶች መመታት አሳዝኖኛል። ሴት እንዴት በፍልጥ ትመታለች ? ደሞ ሁሉንም ተማሪወች ከዶርማቸው እየሰበሩ ነው ጸጥታ ሀይሎች ያወጧቸው። ተማሪ በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ ሲወጣ እንደዚ ያለ ጭካኔ ማየቴ አሳዝኖኛል። "

ተማሪ ስድስት ፦

" ፌደራሎቹ ወደ መማታት የገቡት

ተማሪዎቹ መስኮት መሰባበር ሲጀምሩ ነው። "

ተማሪ ሰባት ፦

" ተማሪ ድንጋይ አልወረወረም ፤ ተማሪ ያደረሰው ጥፋት የለም ፤ ላይብረሪ

ቢሮው መስታወት አልተነካም። ከፈለጋችሁ ግቢው ፈቃደኛ ከሆነ ጠይቃቹ ማረጋገጥ ትችላላችሁ። በእርግጥ መንገድ ዘግተዋል መንገድ የዘጉበት ምክንያት ፖሊስ ተማሪን መምታት ሲጀመር የፖሊስ መኪና እንዳይንቀሳቀስ መንገድ ተዘግቷል። "

ሌሎች በርካታ ተማሪዎችም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ለማቅረብ በወጡ ተማሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ መውሰዳቸውን ፤ ተቋሙም ከውይይት ይልቅ ኃያልን አማራጭ ማድረጉን ገልጸዋል።


የተቋሙ ሰራተኞች ምን አሉ ?

አንድ የተቋሙ ሰራተኛ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተፈጠረውን ነገር ሙሉ ገጽታ የሚያሳዩ አይደሉም ብለዋል።

በሰዓቱ እሳቸውም ጊቢ ውስጥ የሳምንት መጨረሻ ተማሪዎችን ለማስተማር ተገኝተው እንደነበር ጠቁመዋል።

" ተማሪዎቹ ተሰብስበው በከፍተኛ ጩሀት እየመጡ ነበር ፤ የሚጠይቁት ጥያቄ አግባብ ያለ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡም ለማድረግ የጊቢውም ማህበረሰብ እኔንም ጨምሮ በጣም ለምነን ነበር። " ያሉ ሲሆን " ሆኖም ግን ተማሪዎቹ በቀጥ የግቢውን ዋናውን መንገድ በትልልቅ ድንጋይ በመዝጋት እና ጸጥታ ሀይሉ ላይ ድንጋይ በመወርወር ቢሮዎችን ቤተመጽሐፍት እና ዶርሞችን ለማውደም ሲጀምሩ ነው የጸጥታ ሀይሉ እርምጃ የወሰደው። " ብለዋል።

" ለማስተማር የገባን መምህራን እና የweekend ተማሪዎች final exam ሊወስዱ የገቡትም ምሳ እንኳን ሳይበሉ 9 ሰዓት አካባቢ ነው ከጊቢ የወጣነው። " ሲሉ ገልጸዋል።

" ተማሪዎቹን ንጹሕ ሌላውን የጸጥታ ሀይል በመወንጀል የሚሰራ ዜና ሚዛናዊነት የጎደለው እና የክስተቱን ሙሉ ገጽታ የማያሳይ የተቋቋሙ ሀላፊዎች ጉዳዩን ለማርገብ የሄዱበትን ርቀት ያላገገናዘበ ሆኖ አግኝቸዋለሁ መታረም አለበት " ብለዋል።

" ተማሪ ጥያቄ አለኝ ብሎ " ቢሮ መስበር አለባቸው ? ቤተመጻሕፍት ማውደም ? መንገድ መዝጋት አለባቸው ? " ሲሉ የጠየቁት እኚሁ መምህር " እንዲህ አይነት ያልተገባ ነገርም ማውገዝ በሁለቱም አካላት የተፈፀመድን በማውገዝ ሚዛናዊ መረጃ መስጠት ይገባል " ሲሉ አስገንዝበዋል።

የተቋሙን ሰላማዊ ሁኔታ ለመረበሽ የሞከሩ ተማሪዎችንም በተማሪዎች ላይ ድብደባ የፈፀሙ የፀጥታ ኃይሎችንም በእኩል ማውገዝ ይገባል ሲሉ መምህሩ አክለዋል።

ሌላ አንድ የተቋሙ ሰራተኛ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሰላማዊ እንዲሆን ጥረት መደረጉን እና ነገሩ እንዲረግብ ለማድረግ ቢሞከርም አንደንድ ተማሪዎች ሁኔታው ወደ ግጭት እንዲገባ ድንጋይ ሲወራወሩ እንዲሁም ግቢውን ለመረበሽ ሲሞክሩ የፀጥታ ኃይሎች የተቋሙን ሰላም ለማስከበር ወደ እንቅስቃሴ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በተቋሙ በኩል የሚሰጥ ማብራሪያ ካለ ተከታትለን እናሳውቃለን።

@tikvahethiopia

Report Page