Tikvah Ethiopia

Tikvah Ethiopia


ረቡዕ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ/ም


በሀገር ዓቀፍ የምክክር ጉባዔው አዲስ አበባን ማን ይወክላታል?


የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ደረጃ ለ7 ቀናት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደትን ትላንት ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በ12ቱም ክልሎችም ተመሳሳይ ተግባራትን እንደሚያከናውን አስታውቋል።


ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ለመሆኑ ለሚጠበቀውና ለዋናው ሀገር ዓቀፍ የምክክር ጉባዔ ለመሳተፍ ከሚጠበቁት 3,500 ተወካዮች መካከል አዲስ አበባን እንዲወክሉ የተመረጡት እነማን ናቸው? ሲል ኮሚሽኑን ጠይቋል።


የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን፦


“በአዲስ አበባ ደረጃ ሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ነበሩ። 

አንደኛው ከወረዳ የመጡት የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ነበሩ። (አነዚህም ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ መምህራን፣ እድሮች…ተብለው 11 የማህበረሰብ ክፍሎችን የወከሉ ናቸው) 


ሁለተኛው ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የመጡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ነበሩ። (ባለድርሻ አካላት ደግሞ ሲቪክ ማህበራት፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስት የሚባሉት ናቸው)


እነዚህ ሁለት ቡድኖች አንድ ላይ ተሰባስበው አጀንዳ ሲያሰባስቡ ነበር። ስለዚህ ከወረዳ የመጡት ለዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ተመርጠዋል።”


Q ስንት ናቸው የተመረጡት?


“ከ11 የህብረተሰብ ክፍሎች ከእያንዳንዳቸው 11፣ 11 በአጠቃላይ 121 ተወካዮች ማለት ነው።”


Q ባለድርሻ አካላትስ በሀገር ዓቀፍ የምክክር ጉባዔው ከተመረጡት ከ121 ተወካዮች መካከል ተካተዋል?


“ባለድርሻ አካላት በዬክልሉ ቢገኙም አንድ ተቋማ ናቸው። እና የተቋማዊ ውክልና ይዘው ነው የመጡት።


ስለዚህ እነርሱን አሁን አልወከልንም። እርስ በእርሳችሁ ተመራረጡ የምንላቸው አይደሉም። 


ተቋማዊ ውክልና ስለሆነ እዚህ ያላችሁት ብቻ ተወካከሉ ብንላቸው ተቋሙ ውስጥ ያሉ ሰዎችን Exclude እናደርጋለን ማለት ነው።


ስለዚህ የእነርሱ ገና ወደፊት ነው የሚወከሉት። አሁን ለአጀንዳ ማሰባሰቡ እንዲሳተፉ ነው የመጡት። ስለዚህ ወደ ተቋማቸው ተመልሰው ነው የሚወካከሉት” ሲሉ አስረድተዋል።


በመጨረሻ በሚደረገው በሀገር ዓቀፍ የምክክር ጉባዔው የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን የሚመረምረው ማነው?


የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።


በመጨረሻውና በዋናው ሀገር ዓቀፍ የምክክር ጉባዔ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን የሚመረምሩትን አካላት ማንነት በገለጹበት አውድ፣ “የሚመረምረውና መጨረሻ የሚያወጣው ኮሚሽኑ ነው” ብለዋል።


“11ዳችን የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ነን በዋናነት” ነው ያሉት።


Q ታዲያ በሀገር ዓቀፍ ምክክሩ ይሳተፋሉ ተብለው የሚጠበቁት 3,500 ተወካዮቾ ተግባራቸው ምንድን ነው?


ዶክተር ዮናስ፦


“3,500ዎቹ ተወካዮች ተግባራቸው በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አጀንዳዎችን ማቅረብና መመካከር ነው። 


ከዚያ ከእነርሱ የሚቀርበውን ግብዓት አጠቃለን እንደ Recommendation የምናቀርበው እኛ ኮሚሽነሮች ነን። በዐዋጁ መሠረት ነው እየተናገርኩ ያለሁት።”


Q 3,500ዎቹ ተወካዮች ሁሉ ተመርጠዋል? ወይስ ገና ናቸው?


ዶክተር ዮናስ፦


“አሁን በዬወረዳው የተመረጡ ሰዎች አሉ። 121 ተወካዮች በአዲስ አበባ ደረጃ እንደተመረጡት።

ተጨማሪም ይኖራል፤ በየማህበረሰብ ክፍል። ለምሳሌ ከወረዳ ሳይመረጡ የገቡ አሉ ከአዲስ አበባ ላይ።


ለምሳሌ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉት፦

₀የቀድሞ ሰራዊት አባላት፣

₀ባለፉት ዘመናት አገርን ሲያገለግሉ የቆዩ ታላላቅ አዛውንቶች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችን በቀጥታ ነው ያስገባናቸው።”


Q በአዲስ አበባ ደረጃ በነበረው ሰሞንኛው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ለሀገር ዓቀፍ ምክክር ጉባዔው አዲስ አበባን የሚወክሏት ከወረዳዎች የተመረጡ 121 ተወካዮች መሆናቸውን ገልጻችኋል።


ታዲያ ከ5ቱ ቡድኖች ተውጣጥተው የተመረጡት 25 ተወካዮችስ ተግባራቸው ምን ነበር? 


ዶክተር ዮናስ፦


“በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች ማቅረብ ነበር። አቅርበዋል። ይሄም በቀጣዮቹ ሂደቶች የምናደርገው አሰራር ነው።


በሀገር ዓቀፉ የምክክር ጉባዔ የሚሳተፉት አጀንዳ ያቀረቡት 25 ተወካዮች ሳይሆኑ ከየወረዳው የተመረጡት 121 ተወካዮች ናቸው።


Q በአዲስ አበባ ደረጃ የተመረጡት 25 ተወካዮች የወከሏቸውን የማህበረብ ክፍሎች ፍላጎትና ሀሳብ የማንጸባረቅ ብቃቱ እንዴት ይኖራቸል? በሚል ለሚነሱ ጥያቄ አዘል ትችቶች ኮሚሽኑ ምን ይላል? 


ዶክተር ዮናስ፦


“ትችቶቹን እናከብራቸዋለን። ተችዎቹ በራሳቸው አመለካከት ልክ ናቸው። እኛ ግን በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ብለን ያቀድነው 3,500 ሰዎችን ነው በአጠቃላይ።


25 ተመረጡ የተባሉት አጀንዳውን የሚያቀርቡልን እንጂ ተመርጠው ወደ National dialogue የሚሄዱ አይደሉም።


አንደበተ ርቱዕ ናቸው? የህብሰተሰቡን ጥያቄ ያንጸባርቃሉ? ለሚለው ጥያቄ ህዝቡ ‘በአንጻራዊነት እነዚህ ይሻሉኛል’ ብሎ ከመረጣቸው መቀበል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።


#TikvahEthiopiaFamilyAA


@tikvahethiopia

Report Page