Tikvah-Ethiopia
በጦርነቱ ምክንያት ከ70 ከመቶ በላይ ውድመት የደረሰበት የዓዲግራት አዲስ የመድሃኒት ፋብሪካ አግግሞ እስከ 110 የሚደርሱ የተለያዩ በሽታዎች የሚፈውሱ መድሃኒቶች በማምረት ላይ እንደሚገኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
የፋብሪካው ዋና ስራ አስፈፃሚ ሃይለ ገብረሚካኤል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፥ የመድሃኒት ፋብሪካው ጦርነቱ በጀመረ ማግስት በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
በእነዚህ የኤርትራ ወታደሮችም 7 ሰራተኞቹ በሞት መነጠቁንና በርካቶችም መቁሰላቸውን አስታውሰዋል፡፡
የመድሃኒት ፋብሪካው ከህዳር እስከ የካቲት 2013 ዓ.ም ባሉት ሶስት ወራት የኤርትራ ወታደሮች እንደ #ካምፕ ሲገለገሉበት እንደነበር ገልጸዋል።
" ወታደሮቹ ማሽነሪዎች ጨምሮ የተለያዩ የፅህፈት ቤት እቃዎች ዘርፈው መውሰዳቸውንና መውሰድ ያልቻሉት ፈንጅ በማጥመድ አጋይቶውታል " ብለዋል፡፡
ፋብሪካው በወርሃ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በተነፃፃሪ የጥበቃ ከለላ ስር የተወሰኑ የጥገና ስራዎች ጀምሮ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን በውቅቱ በነበረው የተወሳሰበ ውግያና የፀጥታ መድፍረስ ሳይሳካለት ቀርቶ 1500 ቀዋሚና ጊዚያዊ ሰራተኞቹ ለመበተን መገደዱን አመልክተዋል።
ፋብሪካው ከጥቅምት 2015 የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማግስት የጥገና ስራዎች በማካሄድ ከፌደራል የመድሃኒትና የምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን መልሶ ለማምረት የሚያስችለው የብቃት ማረጋገጫ ማግኘቱ አቶ ሃይለ ገልፀዋል፡፡
የመድሃኒት ፋብሪካው “ CAPITAL 54 “ ከተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ በጋራ ለመስራት በገባው ውል ፋብሪካው በሶስት እጥፍ ማሳደግ የሚያስችል የማስፋፍያ ፕሮጀክት ጀምሮ የስቪል ስራው ከ80 ከመቶ በላይ ተጠናቅቆ የነበረ ቢሆንም ፣ በኮሮና እና ኮሮና ተከትሎ በተከሰተው አስከፊውና አውዳሚው ጦርነት የማስፋፍያ ፕሮጀከት እስከ አሁን ተቋርጦ ይገኛል፡፡
የተቋረጠው የፋብሪካው የማስፋፍያ ፕሮጀከት ለማስቀጠል ከፌደራል የጤና ሚኒስቴር መግባባት ላይ ቢደረስም በአገሪቱ ባለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ወደ ተግባር መሸጋገር አልተቻለም ብለዋል አቶ ሃይለ ገብረሚካኤል፡፡
የአገሪቱ የመድሃኒት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ የሟሟላት አቅም ያለው ፋብሪካው ፣ ማምረት ያቆማቸው የፀረ ኤችአይቪ ፣ የቲበር ክሎሲስና የወባ ፈዋሽ መድሃኒቶችና ሌሎች መልሶ ማምረት ያለበት የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመፍታት በኩል አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት የበኩላችው እስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዋና ስራ አስፈፃሚው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በ14 ሄክታር መሬት የተገነባው ግዙፍ ፋብሪካው ከአዲስ አበባ በ900 ኪሎሜትር ፣ ከኤርትራ ድንበር በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ሲሆን ለ1500 ወገኖች ቀዋሚና ጊዚያዊ የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
በአገሪቱ ካሉ ከ12 በላይ የመድሃኒት ፋብሪካዎች በትልቅነቱ ተጠቃሽ የሆነው የዓዲግራት አዲስ የመድሃኒት ፋብሪካ በ2012 ዓ.ም የተሻለ ግብር ከፋይ በሚል በአገር አቀፍ ደረጃ መሸለሙ የፋብሪካው ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡
በ1984 ዓ.ም ግንባታው ጀመር በ1989 ዓ.ም ተጠናቅቆ ወደ ምርት የተሸጋገረው የዓዲግራት አዲስ የመድሃኒት ፋብሪካ ከትእምት (ከትግራይ መልሶ ግንባታ ድርጅቶች) እህት ኩባንያዎች አንዱ መሆኑ የዘገበው የመቐለ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤሰተሰብ አባል ነው፡፡
***
@tikvahethiopia