Tikvah-Ethiopia

Tikvah-Ethiopia


ዛሬ የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ፤ በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መምከሩን አሳውቋል።


ይህ ተከትሎ ዘለግ ያለ መግለጫ አውጥቷል።


በዚህ መግለጫ ፦

- ስለ ሀገራዊ ምክክር 

- ስለ ሽግግር ፍትሕ

- ከመንግሥት ውጭ ታጥቀው ስለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች 

- ስለ ተሃድሶ ኮሚሽን

- ስለ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት

- ስለ ህወሓት ታጣቂዎች

- ስለ ተፈናቃዮች መመለስ ጉዳይ (ራያና አላማጣን ጨምሮ) 


... ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተውበታል።


ምክር ቤቱ ፥ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሀገረዊ ምክክር ኮሚሽን በክልል ደረጃ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ ይጀምራል ብሏል። 


ሀገራዊው የምክክር ጉባኤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ተስፋ ይደረጋል ሲል ገልጿል።


ምክር ቤቱ ፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መፅደቁን አስታውሷል።


እንደ አግባብነቱ ፦

° የወንጀል ምርመራ እና ክስ፣ 

° እውነት ማፈላለግ፣ 

° ዕርቅ፣ 

° በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምሕረት፣ 

° ማካካሻ እና ተቋማዊ ማሻሻያ እንደ ሽግግር ፍትሕ ስልቶች በሀገራችን ተግባራዊ ይደረጋሉ ብሏል።


" የመንግሥት አንዱ መብት በብቸኝነት ኃይልን መጠቀም " መሆኑን ገልጾ በሀገራችን በተወረሰ የፖለቲካ ስብራት የተነሣ የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋል ብሏል።


የሀገሪቱን ሰላምን የጸና ለማድረግ፣ እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው፣ የተሐድሶ ሂደት ውስጥ መቀላቀል አለባቸው ብሏል። " የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውንም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በመሳተፍ መፍታት ይችላሉ " ሲል ገልጿል።


ለዚህም የተሐድሶ ኮሚሽን ተቋቁሟል። ዓላማውም ፦

° መሣሪያ ማስፈታት፣ 

° የትጥቅ ቡድኖችን ሰላማዊ ማድረግ

° የትጥቅ ቡድኖችን ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ነው ብሏል።


መንግሥት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበር ከሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ጋር የተናበበና የሚመጋገብ እንዲሆን ኃላፊነቱን ይወጣል ብሏል።


ምክር ቤቱ በመግለጫው ፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጦርነትን በፖለቲካዊ መፍትሔ የመቋጨት ባህል አምጥቷል ብሏል።


የሰላም ስምምነቱ ለትውልድ የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክትን ከቂም ጋር ላለማውረስ የተደረገ ውሳኔ እንደሆነ ገልጿል።


በዚህም ደም መፋሰስ እና ግጭትን ማቆም እንደተቻለ አመልክቷል።


የሰላም ስምምነቱ እስካሁን ብዙ ውጤት እና እፎይታ ቢያስገኝም ቀሪ ሥራዎችም አሉ ብሏል።


በተለይ በስምምነቱ መሠረት ፥ " የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው " ሲል ገልጿል።


የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ እልባት ለመስጠት እንዲቻል የተቀመጠው አቅጣጫ ተግባራዊ መደረግ አለበት ብሏል።


በጦርነቱ የተፈናቀሉትን ለመመለስና ለማቋቋም የተጀመረው ሥራ እልባት ማግኘት እንዳለበትም ገልጿል።


" ካለፈ ስሕተተ አለመማር የመጀመሪያውን ስሕተት ከመሥራት የባሰ ነው " ያለው ም/ቤቱ ፤ ካለፈው ስሕተታቸው ሳይማሩ ዛሬም ተመሳሳይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉ እንዳሉ ጠቁሟል።


እነዚህን ሁሉም ተባብሮ አደብ ማስገዛት ይኖርበታል ብሏል።


" ከትዕግሥት በኋላ የሚከሠት ሕግ የማስከበር ሥራ የሚኖረውን አስከፊ ውጤት ከቅርቡ ታሪካችን ልንማር ይገባል " ሲል አሳስቧል።


ምክር ቤቱ ፤ መንግሥት በትግራይ ክልል አልፎ ቁስልን ለመሻር የሚያስችል ሥራ እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።


" ይሄ ግን መንግሥታዊ ኃላፊነት እንጂ ፍርሃት ተደርጎ መወሰድ የለበትም " ብሏል።


" በፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንደ ሀገር የሚኖረው አንድ የመከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው ክልሎች በክልል ከፖሊስ እና ሚሊሺያ ያለፈ የታጠቀ እና የተደራጀ ሠራዊት ሊኖራቸው አይችልም፤ አይገባምም " ብሏል።


በዚህ መሠረት ትጥቅ መፍታት እና ተያያዥ ሂደቶች በተሐድሶ ኮሚሽኑ ዕቅድ መሠረት በፍጥነት ሊተገበሩ እንደሚገባ አሳስቧል።


ምክር ቤቱ ፥ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ባጋጠመው ግጭት፤ እንዲሁም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች የተነሣ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉ አሳውቋል።


" እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እየሠራን ነው።" ብሏል።


የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች በጋራ ሠርተው ብዙዎችን ከመጠለያ ጣቢያ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጿል።


በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ፤ በራያ እና አላማጣ አካባቢ ከተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥትን ሳይጠብቁ በማኅበረሰባዊ መተሳሰብ ብቻ በርካታዎች ወደ ቤታቸው እንደገቡ አመልክቷል።


በዚህ ሂደት የተፈናቃዮችን ጉዳይ እንደ ፖለቲካ አጀንዳ አድርገው ሊጠቀሙ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸው ታይቷል ብሏል።


እነዚህ ኃይሎች ተፈናቃዮቹ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ፕሮፖጋንዳ እና ማስፈራሪያ ይደረድራሉ ሲል ገልጿል።


" አንዳንዴም በኃይል ጭምር የተፈናቃዮችን መመለስ ለማሰናከል ይቃጣቸዋል። መንግሥት ካለበት የሞራል እና የሕግ ኃላፊነት የተነሣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቤታቸውና ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ይቀጥላል። " ብሏል።


@tikvahethiopia

Report Page