Tikvah Ethiopia
የሀገር መከላከያው ጄነራል ምን አሉ ?
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ለብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ እና ለመከላከያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ቃለመጠይቅ ሰጥተዋል።
ይኸው ቃለመጠይቃቸው ዛሬ ምሽት ለህዝብ ተሰራጭቷል።
ጄነራሉ ምን አሉ ? በተለይም ስለ ልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ጉዳይ ምን ሃሳቦችን አንስተው ተናገሩ ?
ጄነራል አበባው ታደሰ ፦
- የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን የምንፈልገው በሀገሪቱ የፀጥታ ኃይል እንዲገነባ ህገመንግስቱ የሚፈቅደው #መከላከያ_ሰራዊት እና #ፌዴራል_ፖሊስን ነው።
- በየክልሉ ያለው ልዩ ኃይል በሳይዙ ልክ አለው፤ በሌላ አነጋገር ሀገር በሚመስል ደረጃ 14 እና 15 ሬንጀር አለው ይሄ ፈፅሞ አይቻልም።
- አሁን ያለው የክልል ልዩ ኃይልን መልሶ የማደራጀት ስራ ዛሬ የተጀመረ / በሞራል የተገባበት ሳይሆን ከዚህ ቀደም ለረጅም ጊዜ ጥናት ተደርጎበት ነው።
በተደረገው የረጅም ጊዜ ሰፊ ጥናት የክልል ልዩ ኃይል የነበረው ጥንካሬ እና ጉድለት / እጥረት በግልፅ ተለይቶ ተቀምጧል።
ጥንካሬን በመለከተ ፦
የክልል ልዩ ኃይሎች የክልል ፀጥታን ይጠብቁ ነበር፣ ከእኛ (ከመከላከያ) ጋር ሆነው ይሞቱ ነበር ህይወታቸውን አሳልፈዋል ፣ ቆስለዋል ደምተዋል። ይሄ ኃይል ይሄን የመሰለ ትልቅ ኳሊቲ ነበረው ግን ይሄን ሁሉ እኛ ነበረ ስንመራቸው የነበረው መከላከያ ነው የሚመራቸው የሚያስተባብራቸው ፤ በክልልም በሀገር ፀጥታ ጉዳይም።
ጉድለት/እጥረትን በተመለከተ ፦
• ዋናው ትልቁ እጥረት ህገመንግስት ነው ከህገመንግስት አንፃር ስናየው እነዚህ ኃይሎች ህጋዊ አይደሉም ህገመንግስቱ እውቅና አይሰጣቸውም። ለክልል ኃይል የሚሰጠው መደበኛ ፖሊስን ብቻ ነው። ህገመንግስቱ የታጠቀ ኃይል የሚያውቀው አንደኛ መከላከያ፣ ሁለተኛ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሶስተኛ መደበኛ ፖሊስ ነው ከዚህ ውጭ ህገመንግስቱ አይልም። አወቃቀሩ ህጋዊ ስላልሆነ ወደህጋዊ መስመር እናሲዘዋለን። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ ውስጥ 14 ሬንጀር አይቻልም ፤ ሁለት ሬንጀር ነው የሚፈቀደው አይደለም ለህዝቡ ለኛ ለወታደሮቹ መለየት አቅቶናል ሬንጀሩን።
• የኃይል አገነባቡ ብሔር ተኮር ነው ፤ ምን ማለት ነው የተባለ እንደሆነ ለኦሮሞ ህዝብ እሞታለሁ ብሎ ቃል ይገባል አማራውስ ጉዳዩ አይደለም ማለት ነው በግልፅ አማርኛ ጉዳዩ አይደለም ፤ አማራው ደግሞ ይመጣና ለአማራ ህዝብ እሞታለሁ ይላል ኦሮሞውስ ጉዳዩ አይደለም ብሄር ተኮር ስለሆነ ሀገር አቀፍ የሆነውን አብሮነት የመኖር የህዝቦችን አንድነት ይሸረሽረዋል።
• ይህ ኃይል የሀገሪቱን የፖለቲካ መፍቻ መንገድ አበላሽቷል። በየትም ሀገር በእኛ ህገመንግስትም ፖለቲካ እና ጉልበት አብረው አይሄዱም። በእኛ ሀገር ፖለቲካ እና ጉልበትን የሰጠው ህገመንግስቱ በህዝብ ለተመረጠ ብቻ ነው። ስለዚህ ፖለቲከኛው በሃሳብ ማሸነፍ ሲያቅተው ሌላ በትር አለው የታጠቀውን ኃይል ያነሳል። ሶስት አመት ሙሉ ጦርነት ውስጥ የቆየነው ለምንድነው ? ፖለቲከኛ እና ኃይል ተገናኘ ትግራይ ላይ ፖለቲካውን ያዙ ወታደር ፈጠሩ አርፈህ ተቀመጥ ኢትዮጵያን እንበትናታለን እንዲህ እናደርጋታለን መጣ ፤ መፍቻ መንገዱን አበላሸው።
• ለሀገር እና ለሁሉም ህዝብ የሚሞተውን ኃይል መገዳደር ቻለ፤ ተገዳዳሪ ኃይል ተፈጠረ ፤ አንተም ተው አንተም ተው ለማለት ጉልበት አለኝ ማለት ጀመረ ይሄን በማን አየነው ሶስት አመት ጦርነት የቆየነው በዚህ ነው።
ስለዚህ በጥናቱ መሰረት ህገመንግስቱ ወደሚለው እናምጣው ነው ፤ ህዝቡም ይሄ ኃይል ልክ አይደለም ማለት ከጀመረ 3 ዓመት 4 አመት አልፏል።
ለምን በጊዜው በሰዓቱ አልተደረግም ለሚለው የነበረው ስርዓት ሌላ ችግር ስለነበር ነው። አሁን ያለው ደግሞ ደረጃ ሰጠ። መጀመሪያ ይሄ ኃይል የኛ የራሳችን ኃይል ነው እንጠቀምበት ፣ ሁለተኛ ትልቁን ኃይል ወደ ትክክለኛው ቦታው ልኬቱ እናምጣው ነው።
የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል፣ የሲዳማ፣ የደቡብ ሶስቱም ፣ የሶማሌ ፣ የአፋር ሁሉም ልዩ ኃይል አለው ይሄ ኃይል ከኛ ጋር የሞተ የተሰዋ ነው፣ ይሄን ኃይል እንደገና ሪፎርም እናድርገው ፣ ሪፎርም አድርገን እናደራጀው የሚል ውሳኔ ነው የተወሰነው። እንበትነው አላለም፣ ትጥቁን እናስፈታው አልተባለም።
ሪፎርሙን እንዴት ነው የምናደርገው የሚለው መከላከያ መግባት ያለበት መከላከያ እናስገባው፣ ፌዴራል ፖሊስ የሚገባው ፌዴራል ፖሊስ እናስገባው ፣ መደበኛ ፖሊስ መሆን የሚፈልገውን መደበኛ ፖሊስ እናድርገው ይሄ ምን ክፋት አለው ? ህግ ማስያዝ ፤ ይሄ የክፋት ጉዳይ አይደለም ይሄ የህገመንግስት ጉዳይ ነው፤ ጊዜ የሰጠነውም ስላልደረስንበት ነው ሌላ ችግር ስለነበረው ነው ሀገሩ ፤ ይሄንን ኃይል ተጠቅመን ወደ ህጋዊ መስመር እናስገባው ነው።
- የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት ፕሮግራሙ ወደ መከላከያ ማስገባት፣ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ማስገባት፣ ወደ መደበኛ ፖሊስ ማስገባት ነው። በማን በራሱ ምርጫ፣ በምን ? ክብሩን ሞራሉን ፣ ጥቅሙን በማይነካ ሁኔታ።
- አፈፃፀሙ በተመለከተ እኩል እደራጀዋለን፣ በጥንቃቄም ይሰራል። ለእኛ ወታደሮቹ ደስተኞች ነን፣ ለህዝቡ ደግሞ የበለጠ ደስታ ነው፤ ብሄርን የማያይ፣ ዘርን የማይመርጥ፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ የፀጥታ መዋቅር መገንባቱ ከማንም በላይ ደህንነቱን የሚጠብቅለት ኃይል መኖሩ ህዝቡ ከማንም በላይ ይፈልገዋል። እኛም በየመንደሩ፣ በየክልሉ ከሚደራጀው ኃይል ጋር ፖለቲከኛው ባመፀ ቁጥር ከእሱ ጋር መጋጨት ሰለቸን። እኛ መዋጋት ያለብን ከኢትዮጵያ ውጭ ላለው ነው።
ስለዚህ አፈፃፀሙ ላይ ጥናት ቀርቦ፣ መንግሥት ወስኖ፣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እኩል በጋራ ነው እየተፈፀመ ያለው።
እዚህ ላይ መጠንቀቅ አለብን አንደኛ ' ትጥቅ ይፈታል ' ለማን ነው የሚፈታው ? ሁለተኛ ' ማን ፍታ አለው ? ' ከየት መጣ ? ያለው የለም እንደውም ሌላ ትጥቅ እንሰጠዋለን ፤ አሁን ከክላሽን ሌላ ብረት ይታጠቅ ነው እያልን ያለነው እንጂ ትጥቁን ይፍታ አይደለም እያልን ያለነው ፤ በእኛ ጋር ነው የሞተውና ወደ ህጋዊ መስመር እናስገባው ነው ያልነው እንጂ እንበትነው አላልንም።
አንደኛውን ክልል ኃይል እንዲኖረው ሌላውን ክልል ኃይል እንዳይኖረው አናድረግም። ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ አይታሰብም። ክልሎች ሊይዙት የሚችሉት የፀጥታ ኃይል አንድ ብቻ ነው እሱም መደበኛ ፖሊስ ነው፤ ከዚህ ውጭ አይዝም። ከዚህ ውጭ ክልል አይፈቀድለትም። ህጉም አይፈቅድም። ሌላው ኃይል ወደ ትክክለኛውን የፀጥታ ኃይል መግባት አለበት። አፈፃፀሙ እኩል ነው እያደረግን ያለነው። አንደኛውን የምናሳብጥበት አይደለም። የከተማ ቀልደኛ የሚያወራው ወሬ ነው ፤ ለእኛ ይሄ አይሰራም ትልቅ ኃላፊነት ያለብን ሰዎች ነን። ኢትዮጵያን እኩል የምናይ ኢትዮጵያን የምንጠብቅ ነን።
የታጠቁ ኃይሎች መፍታት አለባቸው ለምሳሌ የትግራይ የትግራይ ክልል እንደማንኛውም ክልል መደበኛ ፖሊስ ብቻ ነው የሚኖረው ፣ የታጠቀ ልዩ ኃይል የሚባል በፍፁም አይኖረውም ፤ ይሄን እካ ሶስት አመት ሙሉ ታገልነው፤ በሰላም ስምምነቱ እና ማዕቀፉ እየሄደነው ያለው ከባድ መሳሪያ እየተቀበልን ነው ፣ ሌላውን ትጥቅ ይፈታል።
በህገመንግስቱ መከላከያ ፤ ፌዴራል ፖሊስ ብቻ ይኖራል። በክልል መደበኛ ፖሊስ ይኖራል። የኢትዮጵያ ህዝብ 3 ሬንጀር ብቻ ያያል። 30 ሬንጀር አያይም ይሄ ነው እውነቱ።
በፕሮግራማችን መሰረት አፈፃፀሙ ላይ በሁሉም ክልል ይሄንን ውይይት በየደረጃ ያለው አመራር ተወያይቶበታል፣ ተቀብሎታል፣ ደስተኛም ነው። በአንዳንድ የአማራ አካባቢ እና ዩኒቶች ካልሆነ በስተቀር አማራ ልዩ ኃይል የሚባለው በአብዛኛው ተቀብሎታል፣ ይሄ በኮሚኒኬሽን ያለ ችግር ነው ይሄን የኮሚኒኬሽን ችግር እየፈታን ነው ያለነው። አፈፃፀሙ ላይ የታየው ጉድለት ይሄ ነው እንዲህ አይነት ነገር ሊኖር እንደሚችል እንጠብቃለን አስበንም ነው የገባነው ከዛ ውጭ ባወጣነው ፕሮግራም መሰረት ይሄን ኃይል ወደምንለው ፕሮግራም እናስገባዋለን ሁሉንም እኩል አድርገን።
(Tikvah Ethiopia)
@tikvahethiopia