Tikvah-Ethiopia

Tikvah-Ethiopia


የሀገር አቀፍ ፈተናን ያስተጓጎለው የመዋቅር ጥያቄ ፦

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የሚገኘው የእነሞር እና ኤነር ወረዳ ለሁለት እንዲከፈል መወሰኑን ተከትሎ የተነሳው የአስተዳደር ጥያቄ አመታትን አስቆጥሯል።

ይሄንን ችግር ለመፍታት ጥረቶች ቢደረጉም ሀገር አቀፍ ፈተና ጭምር በዚሁ ጥያቄ ምክንያት ተስተጓጉሏል።

በዞኑ መገር ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የሚኖሩ የህብረተሰቡ ክፍሎች ችግራቸውን ሲያስረዱ ''ህብረተሰቡ ባልፈለግነው ወረዳ ሥር እንድንተዳደር ተደርጓል፤ ወሳኔው ከመወሰኑ አስቀድሞ ተገቢው ውይይት አልተደረገም፤ ጥያቄያችንን በማቅረባችን በደል ደርሶብናል'' ሲሉ ይገልጻሉ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በተለይ የዘንድሮ የሀገር አቀፍና የክልል ፈተናዎች መስተጓጎላቸውን አስመልክቶ ባደረገው ማጣራት በመገር አከባቢ ያሉ አብዛኞቹ የ8ኛ ክፍልና የ12 ክፍል ተፈታኞች የመመዘኛ ፈተናቸውን አለመውሰዳቸውን ማረጋገጥ ችሏል።

በአከባቢው 11 ት/ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታም የመማር ማስተማር ሂደታቸውን አቋርጠው እንደሚገኙ አንድ የዞኑ የትምህርት ቢሮ ባለሞያ በስልክ ለቲክቫህ ተናግረዋል።

ወይራ በምትባል ከተማ ባለ መገር ወይራ በሚባል የመሰናዶ ትምህርት ቤት 15 ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተና መውሰድ የነበረባቸው ቢሆንም ፈተናውን መስጠት አልተቻለም። በመገር አንድነት በተሰኘው የመሰናዶ ትምህርት ቤት ግን የፈተና መመሪያ (ኦረንቴሽን) ከወሰዱ 4 ተማሪዎች ሦስቱ ፈተናውን መውሰዳቸውን ከባለሞያው መስማት ችለናል።

በተጨማሪም በቁጥር ወደ 500 የመሚጠጉ የ8ኛ ክፍል ተፈታኞች ሙሉ ለሙሉ በዚህ አከባቢ ፈተናውን አልወሰዱም።

ይህንን ጉዳይ ትምህርት ሚኒስቴር ያውቀው እንደሆን ለባለሞያው ጥያቄ ያቀረብንላቸው ሲሆን ባለሞያውም ጉዳዩ ከዞን አስተዳደር እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ የሚታወቅ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ለተማሪዎቹ አለመፈተን እንዲሁም ለትምህርት መስተጓጎሉ የመዋቅር ጥያቄ ያነሱ በተለይ የአከባቢው ወጣቶች የፈጠሩት መደበኛ ያልሆነ አደረጃጀት የሚያደርገው የማስፈራራት፤ የዛቻ አልፎም የማጥቃት ተግባሮችን በምክንያትነት በመጥቀስ ተማሪዎቹም በእነሱና በቤተሰባቻቸው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ፍራቻ ከፈተናው መቅረታቸውን ያነሳሉ።

በአንጻሩ ግን የማህበረሰቡን ጥያቄ ከፌደራል እስከ ዞን ያለው የመንግስት አስተዳደር ምላሽ ባለመስጠቱ እንዲሁም የተለያዩ በደሎችን እያደረሰ በመሆኑ በአከባቢው ለሚስተዋለው አለመረጋጋት በምክንያትነት ጠቅሰው መንግሥትን የሚከሱ አካላትም አሉ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለጉራጌ ዞን ት/ቢሮ ኃላፊ ስልክ ቢደውልም ''በአካል ካልሆነ መረጃ መስጠት አልችልም'' በማለት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ከዞኑን አስተዳደርም ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

አመታትን ያስቆጠረው ጥያቄ ከትምህርት ዘርፉ በተጨማሪ የጤናና የተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶችን መስጠት እስካለመቻል አድርሶታል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተደጋጋሚ ምክክሮች ቢደረጉም አስካሁን መግባባቶች ላይ ተደርሶ ችግሮች አልተቀረፉም። 

የአከባቢው ማህበረሰብ ወደ አጎራባች ወረዳዎች እየተሰደደ እንደሚገኝና ማኅበራዊ ችግሮች በስፋት እየተስተዋሉ እንደሆነ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ከሚደርሱ መረጃዎች መመልከት ችለናል። አብዛኞቹም ይህ ችግር እንዲያበቃና እየተፈጸሙ ያሉ በደሎች እንዲቆሙ የሚጠይቁ ናቸው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ/ም

ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ

@tikvahethiopiaBot @tikvahethiopia

Report Page