Tikvah-Ethiopia
“ከ10,000 በላይ የተለያዬ እንስሳት በውሃና በመኖ እጥረት ሞተዋል” - አቶ ምህረት መላኩ
በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ሰሃላ ሰየምትን ጨምሮ ድርቅ በተከሰተባቸው ሌሎች ወረዳዎች እንስሳት በመኖ እጥረት እየሞቱ፣ አካባቢያቸውን ለቀው እየተፈናቀሉ መሆኑን ዞኑ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጧል።
የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ማብራሪያ፣ “ከ10,000 በላይ የተለያዬ እንስሳት በውሃና በመኖ እጥረት ሞተዋል” ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም፣ “አበርገሌ፣ ሮቢና፣ በለቃ በላይኛው ተከዜ ተፋሰስ በተለይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ነጻ ያልወጡ፣ መንግሥት የማይቆጣጠራቸው ቀበሌዎች ላይ ሰፋ ያለ ችግር እንዳለና በሪፖርቱ #ከ10,000 በላይ የተለያዩ እንስሳት በውሃና በመኖ እጥረት ሞቱ የሚል ሪፖርት እንዳለ ነው የሚያሳየው” ብለዋል።
ይህ የሞት መጠን በየትኞቹ የእንስሳት አይነት እንደሆነ ተጠይቀው ባስረዱበት አውድ ኃላፊው፣ “በሁሉም የእንስሳት አይነት ማለት ነው። በእያንዳንዱ ዝርያ ከፍ፣ ዝቅ ሊል ይችላል፣ ድርቅ የመቋቋም አቅሙም እንደዝርያውም ስለሚለያይ” ሲሉ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በድርቁ ቀጥተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ እንስሳት ስንት ናቸው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ “በሦስቱም ወረዳዎች (ሰሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ፣ አበርገሌ) በጣም የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለን የለየናቸው ወደ 791,000 አካባቢ ናቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ከ791,000ዎቹ ውስጥ ደግሞ በተለይ ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ላይ ያሉት ክርቲካሊ የዕለትም አቅርቦት ስላጡ 171,000 ወደ ደሃና ወረዳ ተፈናቅለው እንዲሄዱና ተጠግተው ለጊዜው እንዲቆዩ አድርገናል። ይህን ይህል ተፈናቅሎ ከሄደ ቀሪው #(620,000) ደግሞ ከዚያው #እየተላወሰ ነው ያለው” ሲሉ አክለዋል።
በድርቁ ምክንያት ሰዎች ሞተው እንደሆነና እንዳልሆነ ባስረዱበት አውድም አቶ ምህረት፣ ምንም እንኳ ለተጋላጮች የሚመጣው ድጋፍ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ተደራሽ ለማድረግ መዘግየት ቢኖርሞ የተጀመረው ሰብዓዊ ድጋፍ ጥሩ እንደሆነና ቀጣይነት እንዲኖረው አሳስበዋል።
ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከተለዩ 180,580 ተጋላጭ ሰዎች በመጀመሪያው ዙር ድጋፍ ማዳረስ የተቻለው ለ112,000ዎቹ ብቻ እንደነበር፣ ከዚያ ወዲህ ተገኘ በተባለ 20,162 ኩንታል እህልና 240.9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከጠቅላላ ተጋላጮቹ መካከል 175,000 ለሚሆኑት ማሰራጨት እንደተቻለ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሰሞኑን ከፌደራል አደጋ ስጋትና ከአመልድ ተገኘ የተባለውን ድጋፍ ለመስጠት ድልድል እየተደረገ መሆኑን፣ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚሰራጭ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ በተለይ ድርቅ በተከሰተባቸው ክልሎች ከ4 ሚሊዮን በላይ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸው፣ ኮሌራን ጨምሮ የሌሎቾ ወረርሽኞች ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑን የፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ኦቻ ሰሞኑን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በሰሀላ ሰየምት ወረዳ ብቻ ከ4,000 በላይ የዳልጋ ከብቶች በመኖ እጥረት መሞታቸውን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ መኖ ወዳለባቸው አጎራባች ቦታዎች ለመሰደድ መገደዳቸውን፣ ተማሪዎችም ከብቶቹን ጥበቃ ትምህርት አቋርጠው አብረው ለመሄድ መገደዳቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።
ዘገባውን የላከው የአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ነው።
@tikvahethiopia