Tikvah-Ethiopia

Tikvah-Ethiopia


#ሎምባርዲያ

ስለ ሎሞቦርዲያ ሕንፃ መፍረስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌውን ጠይቋል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሕገ ወጥ ነው የሚልን ውሳኔን ውድቅ ያደረገበት፣ የቅርስነት መስፈርት በማሟላት ተመዝግቦ ቆይቶ ነበር የተባለው፣ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው የ90 ዓመቱ ሎሞባርዲያ ሕንፃ ‘ለልማት ይፈለጋል’ በሚል ሰሞኑን በግብረ ኃይሎች መፍረሱ ብዙዎችን ቅር አሰኝቶ ተስተውሏል።

ቅርስ ባለአደራ እንዳይፈርስ በፍርድ ቤትም ጭምር ሲሞግትለት ነበር የተባለው ሎሞቦርዲያ ከመፍረሱ ባሻገር በቦታው በነበረ ስቶራቸው የነበራቸውን መፅሐፍ ለማውጣት ሲገቡ ኮሎን መትቷቸው ሞቱ የተባሉት አቶ ጌትነት ክፍሌ ጉዳይ ቤተሰብንና ወዳጅ ዘመዶችን ለከፍተኛ ሀዘን ዳርጓል።

ሕንጻው ሳይፈርስ እንዲቆይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ካስተላለፈ ለምን እንዲፈርስ እንደተደረገ ማብራሪያ እንዲሰጡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ ለቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬኮተር አቶ አበባው አያሌውን የጠየቀ ሲሆን፣ በፍርድ ሂደቱ ጉዳይ በተቋማቸው ነገረ ፈጅ በኩል ስህተት እንደነበር፣ ሎሞቦርዲያ በተደረገለት ምዘና እንዳይፈርስ የማያደርገው ውጤት እንዳላመጣ ተናግረዋል።

አቶ አበባው፣ ሕንጻው የፈረሰው በቅርስነት መመዘኛ መስፈርቶች መሠረት ከ100 ቢያንስ 50ና ከዚያ በላይ ውጤት ባለማምጣቱ መሆኑን አክለዋል።

ከ100/38 ነጥብ ያስገኙት መመዘኛ መስፈርቶች ምን ምን ናቸው? በእያንዳንዱ መመዘኛ የተሰጡት ውጤቶችስ ስንት ናቸው? ተብሎ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ዋና ዳይሬክተሩ በዝርዝር ምን አሉ?

* ወደ ነጥቦቹ ስንገባ ሦስት ደረጃዎች ናቸው የሚኖሩት። ደረጃ ሀ፣ ደረጃ ለ እና ደረጃ ሐ። 

1ኛ) ደረጃ ሀ ማለት ከ100 እስከ 65 ያመጣ ነው። ከ100 እስከ 65 ውጤት ከመጣ ምንም አይነት አልትሬሽን አይደረግበትም። ለሙዚየም፣ ለባህል ማዕከል ሊደረግ ይችላል። ግን ውጫዊውንም፣ ውስጣዊውንም ገጽታ መቀየር አይቻልም።

2ኛ) ደረጃ ለ ማለት ከ64 እስከ 50 ነው። ይሄ ደግሞ የሚይዘው ውስጥ ላይ Reinnovataion ሊሰራ ይችላል። ግን ቅርስ አይፈርስም የሚል ነው።

3ኛ) 49ና ከ49 በታች ደረጃ ሐ ነው። ይሄን ምዘና ያገኘ ደግሞ ቅርስ አይሆንም፣ መስፈርት አያሟላም የሚል ነው የሚይዘው ብለዋል።

በእነዚህ ደረጃዎች መሠረት ሎሞባርዲያ የተሰጠው ነጥብ ከስንት ስንት እንደሆነ በዝርዝር ይግለጹ?

* “ስታይል 7 ነጥብ ነው የሚይዘው። 3 ነጥብ ነው ያገኘው። ኮንስትራክሽን ማተሪያልን ጨምሮ 6 ነጥብ ነው የሚይዘው። 2 ነጥብ ነው ያገኘው። ዕድሜ 5 ነጥብ ነው የሚይዘው። 3 ተሰጥቶታል።

* አርክቴክት 3 ነጥብ ነው የሚይዘው። ከ3 ዜሮ ነው ያገኘው። ኢንተርየር ከ3/1 (ከሦስት አንድ) ነው ያገኘው። ታሪኩ ሲወሰድ ኢርሌር ትሬደር ነው በሚል 10 ነጥብ ነው የሚይዘው። 7 አግኝቷል።

* ኢቨንት 10 ነጥብ ነው የሚይዘው። 3 ነው ያገኘው። ኮንቴክስት ከ10/3 (ከአሥር ሦስት) አግኝቷል። አካባቢውን ጨምሮ ኮንቲኒዩቲ የሚለው 0/3 (ዜሮ ከሦስት ነው) ያገኘው። Land mark ነው የሚለው፣ ከ4/1 (ከአራት አንድ) ነው ያገኘው። 

* Usabilityን በተመለከተ Comparability አለ፣ 5 ነጥብ ነው ያለው። ዜሮ ነው ያገኘው። አዳፕታቢሊቲ ከአምስት አንድ ነው ያገኘው። ቦታው ፐብሊክ ነው ወይ? በሚለው አይደለም። ከአራት አንድ ነው ያገኘው። 

*Service (አገልግሎት) የሚሰጥበት ምኝታ ቤቶችና ሌሎች ናቸው። ታችም ሱቆች ናቸው። ከሦስት ዜሮ ነው ያገኘው። ቢቆይ፣ አዲስ ቢሰራ በሚል ሦስት ሦስት (3/3) ነጥብ ነው ያገኘው። ኢንተግሪቲ (ያለበት ሁኔታ) አልትሬሽን ብዙ አልተደረገም። ከአምስት ሦስት ነው፡ ያገኘው ብለዋል” አቶ አበባው።

አክለውም፣ “Condition, in good condition ነው አምስት ነው ያገኘው ከሰባት ማለት ነው። እንደዚህ ሆኖ 38 ነጥብ ይመጣል አጠቃላይ። በዚያ መሠረት ኢቫሉየት ከተደረገ በኋላ ነው እኛ የሰረዝነው” ሲሉ ተናግረዋል።


ፍርድ ቤት ሳይፈርስ እንዲቆይ ውሳኔ ካሳለፈ ለምን ፈረሰ? ያለዎት ምላሽ ምንድን ነው?


አቶ አበባው ይህንን ጥያቄ በተመለከተ በተቋማቸው ነገረ ፈጂ በኩል ስህተት እንደነበር የሰጡንን ምላሾች የዘገብን ሲሆን፣ ከዚያ በተጨማሪም ተከታዮቹን አክለው ነግረውን ነበር።

* ፍርድ ቤት ወሰነ፣ አልወሰነ የሌላ ጉዳይ ነው። በራሳችን በኩል ግን ውሳኔአችን አስቀድሞ ነው። ትላንት ወይም ከትላንት በስቲያ አይደለም ከዓመታት አልፎታል።

* ይህን ውሳኔ ኦልሞስት የዛሬ በደብዳቤ ያሳወቅነው የዛሬ ዓመት አካባቢ ነው። ለአዲስ አበባም ለቤቶች ኮርፓሬሽንም የፃፍነው። ያሳወቅናቸው በእኛ በኩል መዝነን የቅርስ መስፈርት አላሟልም የሚል ነው።

* እሱ ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ሊዮን አዲስ አለ አንበሳ ፋርማሲ አጠገብ ያለው። እሱም እንደዚሁ ውሳኔ የተሰጠበት ነው። አንበሳ ፋርማሲ እንደዚሁ ውሳኔ የተሰጠበት ነው በእኛ በኩል ማለት ነው።

* የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ቤት ቤላ አካባቢ የሚገኘው፣ የኮሪያ ቃኘሁ ሻለቃ ሆቴል፣ የሎምቦርዲያ ይህን ሁሉ ቼክ አደረግን። ስለዚህ እስካሁን የተደረገው ምዝገባ ዝም ብሎ ግምታዊ ነው።

* አንደኛው ነገር ከመጀመሪያው በስታንዳርድ መሰራት ነበረበት ዝም ብሎ አይደለም። መስፈርቶቹን መሠረት ተደርጎ ስለሆነ የሚካሄደው ዝም ብሎ እንደድሮው “

አይ’ ይሄ የእንትና ቤት ስለሆነ’ የሚል ነገር አይኖርም።

* በዛ መሠረት ይሄም በእኛም፣ በከተማ አስተዳደሩም፣ በክልሎችም በኩል መወሰድ ያለበት ነው። ህብረተሰቡ አብዛኛው #ከመቆርቆርና ይህንን ካለመገንዘብ ነው። እሱን በእርግጥ እኛም #እየተነጋገርን ነው፣ ይሄ፣ ይሄ ነው የሚሆነው የሚለውን።

* እንዲያው ይሄን የወቅቱን የፖለቲካ ንፋስ በመከተል የሚሄድ ደግሞ አለ። እሱን እንግዲህ እግዚአብሔር ይመልሰው እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም።


ስንት የተመዘገቡ ቅርሶች አሉ? ገና አከራካሪ የሆኑስ ምን ያህል ናቸው?

* “አይ አሁን ተመዝግቧል። የድሮው ምዝገባ የምንሄድበት አይደለም። እንደገና እንደ አዲስ ነው የምንሄደው። ወደ 300 በላይ ታሪካዊ ሥነ ሕንፃ ቅርሶች አሉ አዲስ አበባ ውስጥ። በተለይ አራዳ፣ ጉለሌ፣ አዲስ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች። በተቋማትም የተያያዙ ናቸው።

* የእምነት ተቋማትም ይበዛሉ። በዛ አይነት 50፣ እንደዛ ናቸው። በግለሰብ እጅ ያሉም አሉ። ሌሎችም አሉ። አሁን ደፍረን ይሄ ነው ልንለው የማንችለው አሁን ናሽናል ኢንቬንተሪ እየሰራን ነው።

* አሁን ዳታ ቤዙም ኦልሞስት እያላቀ ነው፣ ሶፎትዌሩም ለምቷል። አሁን የከተማን ቅርስ በተመለከተ ሐውልቶች አጨቃጫቂ አይደሉም። የእምነት ቤቶችም አጨቃጫቂ አይደሉም። 

* እነዚህ የከተማ ሥነ ሕንፃ ቅርሶች የምንላቸው ናቸው። በመመሪያው መሠረት ይካሄዳል። የተመዘገበ ዳታ ቤዝ ይባል። ያ ደግሞ ለሚመለከተው አካል ሸር ይደረጋል። ያ ሲሆን አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከተሞችም ይሰራል ማለት ነው።

* ናሽናል ኢንቨንተሪአችን ውስጥ ይህን የሚያክል ቅርስ አለን፣ ከዚያ ውስጥ የከተማ ቅርስ ብለን የያዝነው አዲስ አበባ ውስጥ ይሄ ነው፣ ጅማ ውስጥ ይሄ ነው፣ ይህነ ያክል ብቻ ሳይሆን ይሄ፣ ይሄ ነው እየተባለ ይታወቃል። እና አሁን ዝም ብዬ ከባለፈው ተነስቼ ይሄ ነው ልልህ አልችልም” ብለዋል።


ስለሎሞቦርዲያ ሕንፃ መፍረስ ያላቸውን ሀሳብ እንዲገልጹ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ወደ ቅርስ ባላደራ ያደረገው ሙከራ ስልክ ለማንሳት፣ የጽሑፍ መልክትም ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።

ሳይፈርስ እንዲቆይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ያሳለፈበት 

ሎሞቦርዲያ ሕንፃ ከመፍረሱ በሻገር በቦታው የመፅሐፍ ስቶር የነበራቸው የ8 ዓመት ልጅ አባት ናቸው የተባሉ አቶ ጌትነት ክፍሌ በፈረሳው ወቅት መፅሐፍ ሊያወጡ ገብተው ኮለን ወድቆባቸው ሕይወታቸው ማለፉን ወንድማቸው አቶ ሚሊዮን ክፍሌ መግለጻቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

ዘገባውን የላከው የአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ነው።

Report Page