#TigrayRegion

#TigrayRegion


በትግራይ ኤርትራ ሰራዊት ጉዳይ ?

ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በትግራይ ክልል ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች ንብረት ዘርፈው ወደ ኤርትራ መውሰዳቸውን /ድንበር ተሻግረድ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው መግባታቸውን ሲገልፁ ነበር።

በቅርቡ እንኳን የትግራይ ክልል የመንገድና ኮንስትራክሽን ቢሮ በርካታ የኮንስትራክሽን ንብረት ተዘርፎ ወደ ኤርትራ መወሰዱን ይህን ለማስመለስም ከፌዴራል መንግስት ጋር ንግግር እንደሚደረግ ገፆ ነበር።

ከዚህ ባለፍ የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካ መንግስት፣ የUK መንግስት የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ መግባታቸውን እና ግጭት እያባባሱ መሆኑን በመግለፅ በአስቸኳይ የኢትዮጵያ ትግራይን ምድር ለቀው እንዲወጡ ሲያሳስቡ ነበር።

በተጨማሪ የትግራይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በትግራይ የኤርትራ ወታደሮች መኖራቸውን በመግለፅ ይህ ሀገራዊ ድፍረት በመሆኑ ምድሪቱን ለቀው እንዲወጡ ሲጠይቁ ነበር። በአካል ወደትግራይ የሄዱ ሰዎችም የኤርትራ ወታደሮችን እንደተመለከቱ ሲገልፁ ነበር።

በዛሬው ዕለት ደግሞ በትግራይ ክልል የሰሜናዊ ዞን ጊዜያዊ አስተዳደር የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ ለብሰው የህዝቡን ንብረት የሚዘርፉና ሴቶችን የሚደፍሩት ህወሓት የፈጠራቸው ወንበዴዎች ናቸው ብሏል።

በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ስለትግራይ ክልል የሚሰራጨው መረጃ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በትክክል እንደማያሳይ ነው የትግራይ ክልል የሰሜናዊ ዞን ጊዜያዊ አስተዳደር መግለፁን ኢዜአ ያስነበበው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰሜናዊ ዞን ጊዜያዊ አስተዳደር ም/አስተዳዳሪ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሉ “የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ ለብሰው የህዝቡን ንብረት የሚዘርፉትና ሴቶችን የሚደፍሩት የህወሓት ስርዓት የፈጠራቸው ወንበዴዎች እንጂ የኤርትራ ወታደሮች አይደሉም” ብለዋል።

አቶ ሙሉ ብርሃን ፥ “ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በእብሪተኝነት በለኮሰው እሳት ራሱም ተለብልቦ ለበርካታ ዜጎች ሞትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል” ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ በውጭ አገር ያሉና በእግራቸው ጫካ ለጫካ የሚኳትኑ ቀሪ የህወሓት አባላት በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የትግራይን ህዝብ ለማታለል እየሞከሩ ነቅ ብለዋል።

 አቶ ሙሉብርሃን፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሰላማዊ እንቅስቃሴ አለ ያሉ ሲሆን የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በአካል ተገኝቶ መዘገብ ለሚፈልግ የመገናኛ ብዙሃን በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ሳይገኙ በርቀት ሆኖ የሀሰት መረጃ ማሰራጨት ተገቢ አይደለም ብለዋል።

አቶ ሙሉብርሃን ፥ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ሀብት እየዘረፉ ነው ሴቶችን እየደፈሩ ነው በሚል የሚሰራጨው የተሳሳተ መረጃ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ አያሳይም ሲሉ ነው የተናገሩት

“የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ አጸፋውን መቋቋም ሲሳነው በስርቆትና በተለያዩ ወንጀሎች ማረሚያ ቤት የነበሩ ወጣቶችን በመልቀቅ ለዘረፋ አሰማርቷቸዋል” ብለዋል።

ስርዓቱ የፈጠራቸውን ስራ አጥ ወጣቶች መሳሪያ በማስታጠቅና የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ በማልበስ ሴቶችን እንዲደፍሩ በማድረግ በኤርትራ ወታደሮች ላይ ለማሳበብ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

“የኤርትራ ወታደሮች ህወሓት ባሰማራቸው ዘራፊዎች ወደ ኤርትራ ድንበር ሄዶ የነበረ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ለትግራይ ህዝብ አስረከቡ እንጂ የትግራይን ህዝብ ንብረት አልዘረፉም” ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ ድርጊቱ በህዝቡ መካከል ልዩነት ለመፍጠር የተደረገ የህወሃት የተለመድ ሴራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ ከሁሉም ጋር በማጋጨት ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ለማድረግ ያደረገውን የ46 ዓመታት ስብከት ለማጥፋት ከአማራና ከኤርትራ ህዝብ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ውይይት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

አቶ ሙሉብርሃን እንደሚሉት፤ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ገመድ በሌሊት መቁረጥ ወይም አንድን ሰው በድንገት መግደል ህወሃት ዛሬም በትግራይ ምድር የፈለገውን ማድረግ ይችላል ማለት አይደለም።

“ህወሃት በትግራይ ክልል ጥቃት መፈጸም ቀርቶ ራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ ጫካ ለጫካ ራሱን ለማዳን የሚኳትን አካል ሆኗል” ብለዋል።


ምንጭ፦ ኢዜአ (የሰሜናዊ ዞንጊዜያዊ አስተዳደር ም/አስተዳዳሪ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሉ)

Compiled By : Tikvah-Ethiopia

@tikvahethiopia

Report Page