Tigray Interim Administration
Tikvah-Ethiopiaየትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች በቅርቡ ነባሩን የትግራይ አስተዳደር ወሰን በመረከብ ማስተዳደር እንደሚጀምሩ ገለፁ!

የትግራይ ክልል ወሰን እና አስተዳደር ወደነበረበት በመመለስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አካባቢውን በቅርቡ ማስተዳደር እንደሚጀምር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ምላሽ መስጠታቸውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ገለፁ።
የምዕራብ ትግራይ ዞን ሙሉውን እንዲሁም የደቡብ ትግራይ ዞን 2 ሰፋፊ ወረዳዎች በአማራ ክልል ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር መሆናቸው ጊዜያዊ አስተዳደር ተገቢውን ስራ እንዳይሰራ እንቅፋት መሆኑን በቅርቡ ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ውይይት ማሳወቃቸውን ገልፀዋል።

የትግራይ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ንጉሰ የክልሉ የወሰን እና አስተዳደር ጉዳይ በትግራይ ክልል ህዝብ ዘንድ ቁልፍ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ መቀጠሉን ገልፀዋል።
አቶ አበራ ፥ "...እኛ አስተዳድሩ ተብለን የተላክነው ያ ከሆነ አሁን በተጨባጭ ያለው ቦታ ያን አይገልፅም ብቻ ሳይሆን ከግማሽ በላይ በአስተዳደሩ ስር አይደለም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩንም ማቋቋም አልቻንም" ብለዋል።
አክለውም ጦርነቱ የህግ ማስከበር ነው ? ወይስ ግዛትን ማስፋፋት ነው ? አንዱ በአንዱ ላይ ንጥቂያ ለማድረግ ነው ወይ ? የሚል የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ጠይቋል ሲሉ ተደምጠዋል።
ያለው ሁኔታ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በሙሉ አቅሙ እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኗል ሲሉም ገልፀዋል።

አቶ አበራ ፥ "ይህ አሁን በትግራይ ህዝብ ዘንድ እየተጠየቀ ያለው ጥያቄ መመለስ ካልተቻለ የትግራይን ህዝብ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ማሰለፍ አይቻልም፤ ህዝቡን ከአስተዳደሩ ጋር ማሰለፍ ካልተቻለ ደግሞ እኛ አስተዳደር አይደለንም የገዢዎች ተልዕኮ ነው የሚኖረን ስለዚህ ህዝብና መንግስትን እንድናሸጋግር ትግራይን በጊዜያዊነት እንዳናስተዳደር የተሰጠን እድል እውነተኛ ከሆነ ህጉና ህገመንግስቱ በሚደነግገው መሰረት ግዛቱ በጊዜያዊ አስተዳደር ስር መሆን አለበት ብለን በተደጋጋሚ ጠይቀናል" ብለዋል።

ይህ አሁን በትግራይ ህዝብ ዘንድ እየተጠየቀ ያለውን የፖለቲካ ጥያቄ መመለስ ካልተቻለ ክልሉ ከኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ እንዳይቀጥል ሊያደርገው የሚችል ስጋት እንዳላቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ተናግረዋል።
አቶ አበራ ፤ "ይሄን የትግራይ ህዝብ የፖለቲካ ጥያቄ አለመመለስ ማለት ቀጣይ ክልሉ እንዳይረጋጋ፣ ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር ምናልባትም ከኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ጋር ከነአካቴው አብሮ እንዳይቀጥል ሊያደርገው ይችላል። ሌላ ፖለቲካዊ ጥያቄ ሌላ የትግል ስልት ይዞ መጥቶ ምናልባትም የኤርትራ ዕጣ ፈንታ ይዞ ሊመጣ ይችላል" ሲሉ ገልፀዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ አበበ ገ/ህይወት ፥ የትግራይ ካቢኔ ሁሉም አባላት በክልሉ የወሰን እና አስተዳደር ጉዳይ ተመሳሳይ እና ወጥ አቋም እንዳላቸው ገልፀዋል።
አቶ አበበ ፥ የትግራይ ወሰን እና አስተዳደርን በሚመለከት ከዶ/ር አብይ አህመድ የተሰጣቸው ምላሽ በቅርቡ ነባሩን የአስተዳደር ወሰን በመመለስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አካባቢውን ማስተዳደር እንደሚጀምር የሚገልፅ መሆኑን ተናግረዋል።
Compiled By : Tikvah-Ethiopia
@tikvahethiopiaBot @tikvahethiopia