Tarik Adugna

Tarik Adugna


ዓቃቢህግ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው ጥላሁን ያሚ በሞት ይቀጣልኝ አለ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ ሽብር እና የህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ለመስማት የተሰየመ ሲሆን ፡በዚህ ጊዜ ዓቃቢህግ ተከሳሹ የቀደመ ባህሪው 2 የወንጀል ሪከርድ እንዳለበት አስረድቷል፡፡

በዚህም ሀጫሉን የመግደል ወንጀል ከመፈፀሙ አስቀድሞ የባቡር ብረት በመስረቅ ወንጀል ተይዞ በአቃቂ ቃሊቲ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደነበረ በዋስ መፈታቱን ጠቅሷል፡፡

 2ኛ ደግሞ ባጃጅ ኮንትራት ይዞ ሀ/ጎርጊስ ከሚባል ምስክር ጋር ባለባጃጁን አስፈራርቶ አስገድዶ አቅጣጫ አስቀይሮ ወደ አካባቢው በመውሰድ ባጃጁን ቀምቶ ጭድ ከምሮበት ሽፍኖ መያዙን እና በአቃቂ ቂሊቲ ምድብ ክስ ተመስርቶበት እንደነበርና ክርክሩ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት መቋረጡን ዓቃቢህግ አብራርቷል፡፡

 በተጨማሪም በሚኖርበት አካባቢ በማህበረሰቡ መሀል በመጥፎ አመልና በአዋኪነት እንደሚታወቅ ዓቃቢህግ በቅጣት ማክበጃ አስተያየቱ ጠቅሷል፡፡

 ሀጫሉን በመግደል ወንጀሉን በፈፀመበት ዕለት ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን ከዚሁ 2ኛ ተከሳሽ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ወስዶ መጠጥ ሲጠጣበት ከነበረበት ቤት ተጠርቶ ሄዶ ወንጀሉን ፈፅሟል ያለው ዓቃቢህግ ለወንጀሉን እንዲፈፅም ተልኮ የሰጡት አካላት ከአንድም ሁለት ጊዜ አስብበት ብለውት እንደነበር እራሱ ተናግሮ እንደነበር አስትውሷል፡ ፡

ስለዚህ አስቦበት ነው ወንጀሉን የፈፀመው ሲል የቅጣት ማክበጃው ከቅጣት አወሳሰን መመሪያ ውጪ እንዲያዝለት እና በሞት እንዲቀጣለት ዓቃቢህግ ጠይቋል፡፡

2ኛ ተከሳሽን ከበደ ገመቹን በተመለከተ ደግሞ ዓቃቢህግ የተከሳሹ እናት ቤት እንዲሰራ የሰጡትን ብር ፍቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ መግዛቱን አረጋግጠዋል ብሏል፡፡

ይህ የሚያሳየው ህግ ተላልፎ ፍቃድ የሌለው መሳሪያ ገዞቶ ለ1ኛ ተከሳሽ በመስጠት በዕለቱ መጠጥ ቤት አምሽተው ወንጀሉን ፈፅመው እሱ ከህግ ሸሽቶ ከገላን አዳአ ድሬ ድረስ ሄዶ የተያዘ በመሆኑ አስቦበት እንጂ በየዋህነት የተፈፀመ ነው ተብሎ ሊያዝ ስለማይገባ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቀጥር 2/2006 መሰረት እንዲቀጣለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ ስለ ቅጣት ማቅለያ ከጠበቃ ጋር አለመነጋገራቸውን የገለጸ ሲሆን ከዕለቱ የችሎት ጉዳይ ውጪ አስተያየት ለመስጠት ሲሞክር ችሎቱ አስቁሞታል፡፡

የቅጣት አስተያየትን በተመለከተ ብቻ ሀሳብ እንዲያቀርቡ የተጠየቁ ሲሆን ተከሽ ጥላሁን ያሚ በቀጣይ ማቅለያ አስተያየት ካለን እናቀርባለን ሲል ምላሽ ሰቷል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ የተከሳሽ ቤተሰቦች የቅጣት ማቅለያ እንደሌላቸው ስለገለፁልኝ በራሳችን የቀደመ መልካም ባህሪያቸው በወንጀል ህግ 82 /1 ሀ መሰረት የቅጣት ማቅለያ እንዲያዝለት አንድ ገፅ ማቅለያ አስተያየት ማቅረቡን አብራርቷል፡፡

1ኛ ተከሳሽ በወንጀል መጠርጠሩ ብቻ መልካም ባህሪ የለውም አያስብልም ተከሶ ውሳኔ ላይ ያልደረሰ 2 የወንጀል ሪከርድ መዝገብ ቀርቦ በማክበጃ መጠቀሱ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብቱን የሚጎዳ በመሆኑ ዓቃቢህግ ያቀረበው መከራከሪያ የተከሰሰበትን አንቀፅ ጣሪያ የማይመጥን ስለሆነ በሞት እንዲቀጣ የቀረበው ማክበጃ ውድቅ ይደረግልን ሲል ተከራክሯል፡፡

2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ፍቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ በመያዙ ብቻ ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የቀድሞ ባህሪው እንደሌለ ተደርጎ የቀረበው ማክበጃ ውድቅ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

 ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ እናቀርባለን የሚሉት አስተያየት ካለ ከቀጠሮ በፊት በፅ/ቤት ማቅረብ እንደሚችሉ በመግለፅ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሀምሌ 20 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል፡፡

 (ታሪክ አዱኛ)

Report Page