#TIKVAH

#TIKVAH


በደቡብ ክልል በሚገኙት የኮንሶ ዞን፣ የአሌ ልዮ ወረዳ፣ የቡርጂና የደራሼ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ አከባቢዎች ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት መኖሩን የቲክቫህ ቤተሰቦች ጠቁመዋል።

ግጭቶቹ እየተከሰቱ የሚገኙት ከአስተዳደርና ወሰን ጥያቄ ጋር ተያይዞ ሲሆን ቀጠናው በዚህ ጉዳይ ሰላም ካጣ ሰንብቷል። ባለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ በኮንሶ ዞን እና በአለ ልዮ ወረዳ በኩል ተመሣሣይ ግጭት ተፈጥሮ በመከላከያ ሀይል ትንሽ ጋብ ያለ ቢሆንም ባለፉት 8 ቀናት ውስጥ ስጋቱ አይሎ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም ነው ጥቆማ ያደረሱን ቤተሰቦቻችን የገለጹት።

መነሻው የአስተዳደርና ወሰን ጥያቄ ይሁን እንጂ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የጉማይደ፣ ፉጩጫ፣ ቱሮ ና ኮልሜ አከባቢ ነዋሪዎች ገልጸዋል። ብዙዎችም የፀጥታ መደፍረሱን እና የቤቶች ቃጠሎውን ሸሽተው ወደ ሌሎች አከባቢዎች እየተሰደዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሚመለከተው የጸጥታና የአስተዳደር አካል ማረጋገጫ ባናገኝም መረጃውን ያደረሱን የቤተሰባችን አባላት በቀጠናው ባለፉት 8ቀናት ብቻ በኮንሶ ዞን ስር የሚገኙ 17 ቀበሌዎች ተቃጥለዋል። ከዚህ ወስጥ 10ሩ ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገዱ ናቸው ተብሏል።

ግጭቱ በሰዎች ህይወት ላይም ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ቁጥሩ ማረጋገጫ ባይገኝበትም ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ያገኘናቸው ጥቆማዎች ያመለክታሉ።

በቂ የጸጥታ ሃይል አለመመደብ፣ የፓለቲካ ፍላጎት ያላቸው አካላት መሳተፍ፣ ውግንና የተላበሰ የጸጥታና የመዋቅር አደረጃጀት፣ የክልሉ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠትና የህብረተሰቡ መዋቅራዊ ጥያቄ በተፈለገው መልኩ አለመመለስ፣ በተሳተፉ የፓለትካ አመራሮች ላይ ተገቢውን እርምጃ አለውሰድ ለችግሮቹ መንስኤና መባባስ ምክንያት ናቸው ተብሏል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የቤተሰቦቻችን አባላት በአስቸኳይ ጉዳዩን የፈደራሉም መንግስት በቂ ትኩረት እንዲሰጠውና የህብረተሰቡን ደኅንነት እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዴ በአካባቢዎቹ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ያረጋገጡ ሲሆን በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን እየተለየ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑወቅት መንግስት ጥቃቱ ወደ ተፈጸመባቸው ቀበሌያት የፀጥታ አባላትን ያሰማራ ሲሆን የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለይቶ ለመያዝም ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል።

(ቲክቫህ ኢትዮጵያ)

Report Page